Search This Blog

Sep 1, 2020

የህግ ፍልስፍና ታሪክ (የምዕራባውያን የሥነ-ሕግ እና ሞራል ፍልስፍናዎች አጭር ዳሰሳ)

 


የህግ ፍልስፍና ታሪክ

(የምዕራባውያን የሥነ-ሕግ እና ሞራል ፍልስፍናዎች አጭር ዳሰሳ)

ክብር አቶ ---__________

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ 

ማውጫ

  • ጥንታዊ የግሪክ ፈላስፎች እና የሕግና ፍትሕ ፅንሰ ሃሳብ 
  • የህግጋቱ ድምጽ፡-  ሶቅራጥስ 
  • ሕግ ፍትህ እና ሪፐብሊክ፡- አፍላጦን 
  • የተፈጥሮ ሕግ ፅንሰት - አሪስጣጣሊስ 
  • ሕግ የሞራል ፈልስፍና እና ፍትህ 
  • ምግባራዊነት 
  • ጠቀሜታዊነት 
  • ግዴታዊነት 
  • ሕግ እና ፍትህ 
  • የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍና 
  • ሶፊስቶች እና አንጻራዊነት
  •  ስቶይኮች እና የተፈጥሮ ህግ
  • የአምላክ ከተማ ቅዱስ ኦግስቲን
  • መነኩሴው ፈላስፋ - ቶማስ አኩይናስ 
  • የአለምአቀፍ ሕግ አባት፡- ሁጎ ግሮቲየስ
  • ዘመናዊ የተፈጥሮ ሕግ - ጆን ፈኒስ
  • የሕገ ሰብ ፍልስፍና 
  • የሂዩም መቀስ - ዴቪድ ሂዩም
  • የሉዓላዊ አካል ትዕዛዝ - ጆን ኦስቲን
  • የሕግ ፅንሰ ሃሳብ፡- ኤች ኤል ኤ ሃርት 
  • ትርጉም እና መርህ፡- ሮናልድ ዶርኪን
  • ፍፁማዊ የሕግ ስርዓት- ሃንስ ኬልስን
  • የሕግ ውስጣዊ ውቅር - ሮን ፉለር 
  • ማህበረሰባዊ ውል እና የግለሰብ ነጻነት 
  • ሕገ-አራዊት ፡ ጆን ሆብስ 
  • ህዝባዊ ፍቃድ፤ ዣን ዣክ ሩሶ
  • ማህበረሰባዊ ውል ፡ ጆን ሎክ 
  • የፍትህ ቀመር፤ጆን ሮውልስ 
  • ስለነፃነት፤ ጆን ስቲዋርት ሚል
  • የገሃዳዊ ስነ-ሕግ ፍልስፍና 
  • ፈላስፋው ዳኛ፡- ኦሊቨር ዌንደል ሆልምስ
  • የህግ ጥርጣሬ፡- ፍራንክ ዥሮም
  • ማህበረሰባዊ የሕግ ፍልስፍና፡- ሮስኮ ፓውንድ 
  • ነቂሳዊ የሕግ ፍልስፍና 
  • ሴት- ተኮር የሕግ ፍልስፍና 
  • ድህረ-ዘመናዊ የሕግ ፍልስፍና 
  • ጆርገን ሃበርማስ- የተግባቦት አመክንዮ 

  • ልዩ ልዩ የህግ ፍልስፍናዎች አህጽሮት
  • 8.1 የምጣኔ ሃብት የሕግ ፍልስፍና 
  • 8.2 የኢማኑኤል ካንት የሕግ ፍልስፍና 
  • 8.3 ታሪካዊ የህግ ፍልስፍና
  • 8.4 ማርክሲስት የሕግ ፍልስፍና 
  • 8.5 የብዝሃ- ሕግ ፍልስፍና 
  • 8.6 ሕግ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕድገት አንፃር 


ዋቢ መፃሕፍት 

መግቢያ

ይህን አነስተኛ ድርሳን ለማዘጋጀት እንድነሳሳ ያደረጉኝ ገፊ ምክንያቶችን በጥቂቱም ቢሆን ለአንባቢዎቼ የማስረዳት ሞራላዊ ግዴታ አለብኝ፡፡ ቀዳሚው ምክንያት የሐገራችን ዘመናዊ የሕግ ስርዓት በአብዛኛው ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የተቀዳው ከሀገራችን ውጪ ካሉ የሕግ ምንጮች ነው፡፡ ሀገራችን ለዘመናት የተዳደረችበት ፍትሐነገስት ራሱ ከአረቦች የተወረሰ መሆኑ ሳያንስ በ1950 ዎቹ የፀደቁት የሕግ ድርሳናት ደግሞ ከአውሮፓ ሀገራት ተወስደው በሀገራችን የተተከሉ ናቸው፡፡ ይህ አካሄድ እንደ ባህል ከመወሰዱ የተነሳ በ1950ቹ ከተካሄደው ከፍተኛ የሕግ ንቅለ ተከላ ( Legal Transplantation) ጀምሮ እስካሁን ድረስ የሀገሪቱን ዋና ዋና አዋጆች እና መመሪያች ቃል በቃል በመተርጎም ወደ ሀገራችን የሕግ ስርዓት መደባለቅ የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ 

በመሆኑም የአሜሪካውያንን እና የአውሮፓውያንን ሕግጋት ቀስ በቀስ እየቀዳን በፓርላማዎቻችን ማፅደቅ እና ማስፀደቅ እንደ ባህል እና አስገዳጅ ሁኔታ መታየቱ ካልቀረ እነዚህ ሕግጋት የፈለቁበትን የፍልስፍና ምንጭ እና የፈሩበትን የአስተምህሮ ተክል ማወቅ የሕግጋቱን መሰረታዊ ባሀሪ እና ታሪክ ለመረዳት አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ የፈረንጅ ሕግጋትን ቆርጦ መቀጠል የሀገራችን የፍትህ ስርዓት ባህል መሆኑ እንዲቀየር ከልፈለግንም የህግጋቱን ፍልስፍናዊ መሰረት በቅድሚያ ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ ይሁን እንጂ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ስነ-ሕግ በጥልቀት ለማጥናት ከስፋቱ አንጻር አዳጋች በመሆኑ ይህ ስራ አመላካች እና አቅጣጫ ጠቋሚ በመሆን እንደሚያገለግል አምናለሁ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በሀገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕግ ፍልስፍና የተሰጠው ስፍራ አነስተኛና ከዘርፉ ግዝፈት አንጻር ሲተያይ አሳሳቢ ነው፡፡ 

በርግጥ ይህ የሆነበት ምክንያት ዋናው የፍልስፍና የትምህርት ክፍል ራሱ እንደ ትምህርት ዘርፍነት መቀጠል አቅቶት በተማሪ ማጣት ሰበብ የሚዘጋ እና የሚከፈት ህልውናውም በቋፍ ላይ ያለ መሀኑ ሲታይ ለህግ ፍልስፍና አነስተኛ ስፋራ መሰጠቱ ብዙም የሚገርም አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት በሕግ ትምህርት ቤቶቻችን የሕግ ፍልስፍና ብዙም ትኩረት አይሰጠውም ብቻ ሳይሆን ይህን ትምህርት እንዲያስተምሩ የሚፈቀድላቸው አስተማሪዎች በራሳቸው ምንም አይነት የፍልስፍና ትምህርት ቅድመ ስልጠናና እውቀት የሌላቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህ የሕግ ፍልስፍና አስተማሪዎች ትምህርቱን እንደ ፍልስፍና ሳይሆንን እንደ ሕግ የሚያስተምሩት በመሆኑ ተማሪዎቹ ላይ ትምህርቱ ማሳረፍ ያለበትን ተጽእኖ ሳያሳድር በከንቱ ያልፋል፡፡ የዚህ ችግር መሰረት ጥልቀት ከሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ውድቀት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ መፍትሔው ሰፊ እና ሁሉን ያሳተፈ መሆን እንዳለበት የሚያጠራጥር ባይሆንም የሕግ ፍልስፍናን ከእናት የትምህርት ዘርፍ ፍልስፍና ጋር ማቆራኘት ግን መሰረታዊ እና ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ 

ሶስተኛው ምክንያት በሀገራች ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሆኑ ባህላዊ የሕግ ሰርዓቶች መኖራቸው ይታወቃል፡ በብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ የተለመዱ ባህላዊ የሕግ ስርዓቶች የራሳቸው የሕግ ፍልስፍና ያላቸው ቢሆንም በሕዝቡና በባህል መሪዎቹ ሕሊና ውስጥ የሚኖሩ እንደመሆኑ በጽሁፍ አልሰፈሩም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአውሮፓ ከቀዳናቸው ሕግጋት ጋር ሳይቀላቃሉ እና ሳይደባለቁ የሚኖሩ እነደመሆናቸው በባህላዊ የሕግ ስርዓቶች እና በመጤ እና ዘመናዊ የህግ ሰርዓቶች መሃከል እስከ ዛሬም ያልተስተዋለ ትልቅ ገደል አለ፡፡ 

     ይህንን ገደል የሚሞላ ሀገር በቀል የስነ- ሕግ ፍልስፍና መፈጠሩ ለነገ የማያድር አስገዳጅ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ድርሳን የአውሮፓ የስነ ሕግ ፍልስፍናዎችን በሕግ ባለሙያዎች እና ለሕዝቡ በቀላል እና በሚረዳው ቋንቋ ማቅረቡ በሚቀጥሉት ጊዜያት ሀገር- በቀል የሕግ ፍልስፍና ለሚፈጥሩ ጥልቅ አሳቢዎች እንደመደላደል ያገለግላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እውቁ ፈላስፋ በተደጋጋሚ ጊዜ  “ፍለስፍና በሀገራችን ወንበር የላትም ” በማለት የሚያቀርበውን ቁጭት ወለድ ትችት መፍታት የምንችለው እንደዚህ ዓይነት ስራዎችን ከነግድፈታቸውም ቢሆን ለህዝብ መወያያነት ማቅረብ ስንችል ነው፡፡ 

     አራተኛው ምክንያት የአማርኛ ቋንቋ አብዛኛውን ጊዜ ለስነ-ጽሁፍ ለመንግስት ስራ ፣ ለታሪክ ሰነዶች ማዘጋጃነት እና ለስርዓተ አምልኮ ከሚውል ቀር ለፍልስፍና ሲውል ማየት የተለመደ አይደለም፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹን የአማርኛ የፍልስፍና ቃላት ከግዕዝና ሌሎች ሀገርኛ ቋንቋዎች ለመዋስ እየተገደድን እንገኛለን፡ የአማርኛ ቋንቋ ከህዝብ መግባቢያነት አልፎ ፍለስፍናን ማፍለቂ እና ማስተላለፊያ ቋንቋ ሲሆን ሰፊ ሀዝብ የሚጠቀመው እንደመሀኑ ፍለስፍናን ራሱን የሕዝብ መግባቢያ እና ማስተማሪያ ማድረግ ይቻላል፡፡ በመሆኑም በፈረንጅ አፍ ሳይሆን በአማርኛ ቋንቋ መፈላሰፍ ቀላልና የተለመደ ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡ 

ምዕራፍ አንድ

ጥንታዊ የግሪክ ፈላስፎች እና የሕግ ፅንሰ ሃሳቦቻቸው

የምዕራባዊ ሃገራት ስልጣኔ የተጠነሰሰው በግሪክ ፍልስፍና ውስጥ መሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ ባይሆንም የግሪክ ፍልስፍና ከየት የተወሰደ ነው የሚለው ሃሳብ ግን እስካሁን ድረስ እያከራከረ ይገኛል፡፡ የግሪክ ፍልስፍና ስንል በተለይም በእነሶቅራጥስ እና ድህረ ሶቅራጥስ ዘመን ያለውን መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ አብዛኞቹ የቅድመ ሶቅራጥስ አሳቢዎች እና ፈላስፎች ትኩረታቸው የምናየው ግኡዛዊ ዓለም ከየት መጣ፣ ከምን ተሰራ እና በመጨረሻስ ምን ይሆናል የሚሉት ሃሳቦች ነበሩ፡፡ ፈጽሞ አዲስ በሆነ መንገድ ሶቅራጥስ የሰው ልጆች የምርምር እና የፍልስፍና ጀማሬ እና መሰረት ግኡዛዊው ዓለም ሳይሆን ራሱ ሰው መሆን እንዳለበት አስረግጦ አስተምሯል፡፡ 

     በዚህም ምክንያት የቅድመ ሶቅራጥስ ፈላስፎች ምድር የተሰራቸው ከእሳት ፣ ከውሃ፣ ከአፈር ወይስ ከንፋስ እያሉ የሚጨቃጨቁበትን መድረክ ሙሉ ለሙሉ ለውጦ ሰዎች የፈጠሯቸው ሃሳቦች እና ልማዶች ራሳቸው እንዲመረመሩ እና እንዲፈተሹ አደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ሶቅራጥስ “ያልተመረመረ ሕይወት መኖር ያልተገባ ነው” በሚለው ሃሳቡ ይታወቃል፣ ሃሳቦችን መበየን እና መተርጎም የተጀመረው በራሱ በሶቅራጥስ ምልልስ (Socratic dialogue) ወቅት መሆኑ ይነገራል፡፡ ከሶቅራጥስ በኋላ ያሉ ፈላስፎችም ይህንኑ ባህል ቀጥለውበታል፡፡ የሶቅራጥስ ተማሪ የነበረው አፍላጦን በበኩሉ የሶቅራጥስ ሃሳቦችን እና የሕይወት ዘይቤ በተለያዩ ድርሳናት ከማዘጋጀት አልፎ የራሱን የፍልስፍና ትምህርት ቤት ከፍቶ ብዙ ፈለስፎችን አፍርቷል፡፡ ሶቅራጥስ ያሳለፈው ሕይወት እና ያስተማራቸው ፍለስፍናዎች አፍላጦን ለትውልድ ባያስተላልፋቸው በታሪክ ውስጥ ተቀብረው ይቀሩ ነበር፡፡ 

     አፍላጦን የተለያዩ “የሶቅራጥስ ምልልሶችን” በርዕስ እና በዓይነት ከፍፍሎ በተለያዩ ድርሳናት አስቀምጧቸዋል፡፡ እነዚህ ድርሳናት ሶቅራጥስ በተዘዋወረባቸው እና ባስተማረባቸው ቦታዎች በሰዎች መኖሪያ ቤት፣ በመንገድ ላይ፣ በገበያ ቦታ፣ በፍርድ አደባባይ፣ በእስር ቤት፤ ከአንድ ግለሰብ ጋር ወይም ከጥቂት ወይም ብዙ ሰዎች ጋር የተደረጉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የተደረጉባቸውም አርዕስቶች እና ምክንያቶች ስለሀገር፣ ፍቅር፣ መንግስት፣ ሕግጋት፣ አማልክት፣ ሕይወት፤ እምነት እና መሰል ጉዳዮ ናቸው፡፡ አፍላጦን እነዚህን ሁሉ የሶቅራጥስ ውይይቶች እና ምልልሶች ስዓላዊ በሆነ መንገድ ከማቅረቡ የነተሳ ብዙ ሰዎች አንዳንዶቹን ውይይቶች ራሱ አለፍላጦን በምናቡ ፈጥሯቸው ነው ወይስ የእውነት ሶቅራጥስ በሕይወት እያለ ያደረጋቸው ናቸው? እያሉ ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሶቅራጥስ ሃሳብ የቱ ጋር አብቅቶ የአፍላጦን ሃሳብ የቱ ጋር ይጀምራል የሚሉትን ጭብጦች እስካሁን እንዳከራከሩን ይገኛል፡፡ 

ከአፍላጦን ቀጥሎ የተነሳው ታላቁ ፈላስፋ “አሪስጣጣሊስ” /አሪስቶትል ሲሆን እሱም ቢሆን የአፍላጦን የፍልስፍና ትምህርት ቤት ተማሪ እና አፍላጦንን ለሃያ ዓመታት ተከትሎ የተማረ ፈላስፋ ነበር፡፡ አሪስቶትልም ቢሆን ሶቅራጥስ እና አፍላጦን የጀመሩትን የፍልስፍና አድማስ የማስፋት ስራ ወርሶ ከግብ እንዲደርስ ብዙ ልፋት እና ድካም የቀላቀለ ትግል አድርጓል፡፡ አስተማሪው የነበረውን የአፍላጦንን ዲበአካላዊ ፍልስፍና በመተቸት የራሱን የፍልስፍና ጉዞ የጀመረው አሪስጣጣሊስ ከቀደሙት ሁለቱ ፈላስፎች የበለጠ የፍልስፍና ሃሳቦችን እና ድርሳናትን እንዲሁም የረቀቁ አስተምህሮዎችን ለውጤት አብቅቷል፡፡ ከዚህም የተነሳ እስከ ዛሬ ድረስ በማበረሰባዊ እና ተፈጥሯዊ የጥናት መስኮች የምናውቃቸው ዋና ዋና የጥናት ዘርፎችን ለመጀመሪያ ጊዜ የከፋፈለው እርሱ ነው፡፡ እነዚህ ፈላስፎች ከብዙ ስራዎቻቸው ውስጥ ስለህግ እና ፍትህ አስተዳደር የነበራቸውን አመለካከት ባጭሩ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ 


የሕግጋቱ ድምጽ - ሶቅራጥስ

ለዘመናት የቆየን የህይወት ዘይቤ እና ስርዓት ለመቀየር መሞከር ከባድ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ሊሆን ይችላል፡፡ ሶቅራጥስ በዘመኑ የነበረውን የአኗኗር ስልትና ፍልስፍና የጠየቀ እና የተቸ እንደመሆኑ ብዙ ጠላቶች ተነስተውበት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት “የወጣቱን አዕምሮ አበላሽተሃል እና አማልክቱን ተሳድበሃል” የሚሉ ክሶች ቀርበውበት በአቴና አደባባይ ከአምስት መቶ በላይ አባላት ባሉት የፍርድ ሸንጎ ፊት ቀርቦ የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል እድል ተሰጥቶት ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ራሱን እና ፍልስፍናውን በሚገባ የተከላከለ ቢሆጅም ኢ- ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የሞት ፍርድ ተጥሎበታል፡፡ ሶቅራጥስ በእስር ቤት ሆኖ የሞት ፍርዱ የሚፈጽምበት ቀንን እየተጠባበቀ ሳለ ፍልስፍናውን በሚየስተምርበት ወቅት የሚያውቁት ባለሀብት ሰዎች ወደ ሌላ ከተማ ሊያስመልጡት ሴራ ጠንስሰው ፣ ይህንን ዕቅድ ክሪቶ የተባለ የሶቅራጥስ ወዳጅ ለሶቅራጥስ በመንገር አሳምኖት ከወህኒ ቤት እንዲያስመልጠው በማስብ ልከውት ነበር፡፡ 

በመሆኑም አንድ ቀን ክሪቶ እራሱ ሶቅራጥስ ወዳለበት የወህኒ ክፍል ከጥበቃው ጋር ተመሳጥሮ በመግባት ይህንን ሃሳብ ይነግረዋል፡፡ ሶቅራጥስ እና ክሪቶ በዚያች አነስተኛ ክፍል ውስጥ የሚያደርጉትን ውይይት አፍላጦን ክሪቶ በሚለው አስደናቂ ድርሳን በዝርዝር አስፍሮታል፡፡ ክሪቶ ያቀረበውን የማምለጥ ሃሳብ ሶቅራጥስ ሙሉ ለሙሉ ያልተቀበለው በመሆኑ ክሪቶ ሶቅራጠስን እስከመለመን ደረጃ ደርሶ ነበር፤ ሶቅራጥስ ሚስት እና ልጆች ስላሉት ለእነሱ እንኳ ብሎ ሕይወቱን እንዲያተርፍ፣ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የከሰሱት ሰዎችም በእኩይ ተግባራቸው ተደስተው እንዳይኖሩና የአቴንስ ሕዝብ ልብም እንዳይሰበር በማባበል ይጠይቀዋል፡፡ 

     ሶቅራጥስ የተላለፈበት የሞት ፍርድ ኢ-ፍትሃዊ መሆኑን ቢያውቅም ከእስር ቤት ማምለጡ ግን የባሰ ሕገወጥነት እና ኢ-ፍትሐዊ መሆኑን ለክሪቶ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ በአቴንስ ከተማ በኖረበት ሰባ ዓመታት የአቴንስ ህግጋት እንቅፋት ሆነውበት እንደማያውቁ እንዲያውም ራሱን በፍቃዱ አስገዝቶ የኖረ እንደነበር ያወሳል፡፡ ሕግጋቱ የተለያዩ ቢሆኑም በአንድ ስርዓት እና ስብእና የታቀፉ እንደመሆናቸው ድምጻቸውን ጥርት ባለ መንገድ እንደሚሰማና ከድቷቸው ቢሸሽ እንደሚወቅሱት ጭምር ይናገራል፡፡ በአቴንስ ከተማ ይህን ሁሉ ዓመታት ሲኖር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከሕግጋቱ ጋር ውል እንፈጸምና እስከ ዛሬ መብቱን እየጠበቁ እንዳኖሩት አሁን ግን በጥቂት ሰዎች ሴራ አማካኝነት ከሕግጋቱ ጋር የፈጽመውን ውል ሊያፈርስ እንደማይገባ እየደጋገመ ለክሪቶ ይነግረዋል፡፡

 በተጨማሪም የሕግጋቱ አንድነት የማይገረሰስ እና የማይነጣጠል እንደመሆኑ አንዱን አክብሬ አንዱን እጥሳለሁ ማለት ሁሉን እንደመጣስ እና እንዳለማክበር እንደሚቆጠር ተናግሯል፡፡ ሶቅራጥስ “የሕግጋቱ ድምጽ  ይወቅሰኛል” ያለውን እንደ ምሳሌ ልንወስደው እንችላለን፣ ሕግጋቱን በሰው ወክሎ እንደሚያናግሩት ማድረጉ ከእነርሱ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ያስረዳለታል፡፡ ይህ ስምምነት ወይም ውል በኋላ ላይ የተለያዩ ፈላስፎች አስፋፍተው በመንግስት እና በሕዝብ ፣ በመንግስት እና በግለሰብ መሀከል የሚደረግ ውል መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ሶቅራጥስ የተላለፈበትን የሞት ፍርድ ለመፈጸም የተዘጋጀለትን መርዝ ለመጠጣት ሲሰናዳ እንኳ አጠገቡ የነበረውን ክሪቶ  ህግጋቱን ስለማክበር እያስረማረውና ከሰዎች የተበደረውን እዳ በእርሱ ስም ሆኖ እዲከፍልለት እያሳሰበው ነበር፡፡ ለእርሱ ፍትሃዊ ሕግጋት በኢ-ፍትሃዊ ሰዎች እጅ ገብተው ፍርድ ቢሰጥባቸውም ለሕግጋቱ ክብር ስንል ኢ-ፍትሃዊውን ፍርድ መቀበል ይኖርብናል፡፡

 

ሕግ፤ ፍትህ እና ሪፐብሊክ - አፍላጦን

ቀደም ብለን እንዳነሳነው አፍላጦን የሶቅራጥስን ፍልስፍና በፅሑፍ ማስቀረቱ ለዓለም ያበረከተው ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሆነ አይተናል፡፡ ይሁን እንጂ ድርሳናቱ በሙሉ በሶቅራጥስ ንግግሮች ስለተሞሉ የእርሱ አስተዋጽኦ አልነበረም ማለት አንችልም፡፡ አንዳንዴ ሶቅራጥስን እና ጓደኞቹን እንደ ገፀ ባሕሪያት በመጠቀም በእነርሱ ውስጥ የራሱን ሃሳብ ይናገር እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡   

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁለት ስራዎች መሀከል ዋነኛ የሆነው (ሪፐብሊክ) የተሰኘ ስራው ከፍተኛ ተቀባይነት ከማግኘቱም አልፎ እስካሁን ድረስ የፖለቲካዊ ፍለስፍናዎቹ ሁሉ መሰረት ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይህ ድርሳን ብዙ ጉዳዮን የሚዳስስ ቢሆንም ስለፍትህ ጥልቅ ሃሳቦችን አንስቶ አብራርቷል፡፡ ድርሳኑ ሲጀምር የፍትህን ምንነት በመጠየቅ ነው፡፡ ሶቅራጥስ ከሁለት ወዳጆቹ ጋር እየተጓዘ ፍትህ ምን እንደሆነ ይጠይቃቸዋል፡፡ ይህ ውይይት የመፅሀፉ ምዕራፍ አንድ እና ሁለትን በሙሉ የሚሸፍን ሲሆን ሶቅራጥስ ስለፍትህ ምንነት ከወዳጆቹ ጋር የሚያደርገው ውይይት እና አንዳንዴም እሰጣ-ገባ ወዳጆቹ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ሲያስቀይራቸው እናያለን፡፡ በውይይታቸው ፍትህ ምንድነው፤ ፍትሃዊ የምንሆነው ለማን ጥቅም ብለን ነው? ፍትሃዊ ባንሆን ማን ይጎዳል?የሚሉ ጥያቄዎች እና ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት የሚደረግ ሲሆን ምዕራባዊ የሕግና የፖለቲካ ፈላስፎች ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ስለፍትህ የሚጽፉት ፣ የሚጠይቁት እና የሚያብራሩት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሶቅራጥስ ከወዳጆቹ ጋር በጥልቀት የተወያየበት አና የተጨቃጨቀበትን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ድርሳን ወይም በዚሁ ድርሳን ላይ የተጻፉ አናባቢ መጻህፍትን ማንበብ እና ማጥናት በህግ ወይም ፖለቲካ ላይ መመራመር ለሚፈልግ ሰው አስገዳጅነት ያለው ተግባር ነው፡፡ 

ሌላኛው የአፍላጦን ድርሳን “ሕግጋት” Laws ሲሆን ሶስት በእድሜ የገፉ ግሪካውያን ስለ ሕግጋት አመሰራረት፤ ህግጋቱን ማን ሊያወጣቸው ይገባል ? የሕግጋቱ ምንጭ ምንድነው? መለኮታዊ ህግጋት ምንድናቸው? የተፈጥሮ ህግ ምን ማለት ነው በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ሲያደርጉ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ድርሳን ሶቅራጥስ በገፀ ባሕሪነት አልተሳተፈም፡፡ እነዚህ ሶስት ሽማግሌዎች ማግኒዥያ ለምትባል  ሀገር ጥሩ ህገ መንግስት ለማርቀቅ በማሰብ ይነጋገራሉ፡፡ 

ሪፐብሊክ እና ሎውስ የተባሉት ሁለቱ ድርሳናት አንድነትና ልዩነት አላቸው ፡፡ ፊፐብሊክ በስነ-ፅሁፍ ውበቱ እና ሃሳብ ፍሰቱ ከሎውስ እጅግ የተሻለ ሲሆን ህግጋት የሚወጡበትን ጥቃቅን መስፈርቶች ከመለካት ይልቅ አጠቃላይ በሆነ ፖለቲካዊ ባህል እና ስነ-ምግባር ላይ ያተኩራል፡፡ ሎውስ የተሰኘው ድርሳንን አፍላጦን በእድሜ ከሸመገለ በኋላ ጽፎታል ተብሎ ስለሚታሰብ የቃላት አመራረጡም ሆነ የሃሳብ ፍሰቱ ብዙም አይስብም ፡፡ 

ሪፐብሊክ በተባለው ድርሳን ፍጹም የሆነች “ካሊፖሊስ” በተባለች ከተማ ሶስት ሕዝባዊ መደቦች ሲኖሩ እነዚህም ሰራተኛው መደብ ፤ የሪፐብሊኩ ጠባቂ ወታደሮች ና በፈላስፋ ንጉስ የሚመሩ ፈላስፋ ገዢ መደቦች ናቸው፡፡ በዚህ ድርሳን ይህ አይነቱ ክፍፍል የለም፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱም ድርሳናት ሆነ በሌሎቹ ሶቅራጥስ እንደተናገሪ አፍላጦን እንደ ጸሀፊ ሰፊ የሆኑ ጥያቄዎችን ስለህግና ፍትህ አንስተዋል፡፡ ምንም እንኳ የሚሰጡት መልስ አንዳንዴ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ማህበረሰብ የማይመጥኑ ቢመስሉም ያነሷቸው ጥያቄዎች ግን ዛሬም ድረስ ዕውቅ በሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወሱ ናቸው፡፡ አፍላጦን ከእነዚህ እና መሰል ዘመን አይሸሬ የፍልስፍና ስራዎቹ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ 


የተፈጥሮ ህግ ፅንሰት- አርስቶትል

አሪስቶትል ከአፍላጦን ተለይቶ የራሱን የፍልስፍና ትምህርት ቤት ከፍቶ ማስተማር ከጀመረ በኋላ ኒኮሚኪያን ስነ- ምግባር (Nichomichean Ethics)የሚል ድርሳን ጽፏል፡፡ በዚህ ድርሳኑ ረቂቅ የምግባራዊ ሞራል ፍልስፍና አቀንቃኝ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ሕግ ፍጹም ማህበረሰብን ለመገንባት እንደሚያገለግል በመጠቆም ጠቅላላ ፍትህንም ለሁለት ከፍሎታል፡፡ አንደኛው ተፈጥሮአዊ ፍትህ ሲሆን ሌላኛው መደበኛ ፍትህ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ፍትህ ለሰዎች የማይነጠል እና የማይገረሰስ መብትን የሚያጎናጽፍ ሲሆን መደበኛ ፍትህ ደግሞ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያወጡት ነው፡፡ ለአሪስቶትል በአንድ ሀገር ሰላም እና ስርዓት ለማስፈን ለአንባገነናዊ አገዛዝ እና ለዲሞክራሲ መሀከለኛ የሆነ ሚዛናዊ አስተዳደርን መገንባት ያስፈልጋል  ፡፡

አሪሰቶትል የዲበአካላዊነት ትምህርት ጠንሳሽ ነው፡፡ ሜታፊሲክስ የሚለው ድርሳን በዚህ የእውቀት ዘርፍ ቀዳሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሜታፊሲክስ የሚለውን ቃል ራሱ የተፈጠረው በአሪሰቶትል ሰበብ ነው፡፡  ይህ ጽሁፍ ስለ ፊሲክስ ከጻፈው መጽሃፍ ቀጥሎ ስለተገኘ በተለምዶ ከፊሲክስ ቀጥሎ ያለው መጽሃፍ ለማለት ሜታፊሲክስ የሚለው ቃል በሌሎች ሰዎች ተፈበረከ እንጂ በራሱ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ የምናየው ዓለው ከየት መጣ፤ ከምን ተሰራ ፤መጨረሻው ምንድነው፤ ደግሞስ በምን ይንቀሳቀሳል የሚሉትን ጥያቄዎች የሚመልስ የጥናት ዘርፍ ሲሆን አሪሰቶትል First Philosophy ወይም Theology በማለት ይጠራዋል፡፡

   አሪሰቶትል በመሀከለኛው ዘመን በተነሱ የካቶሊክ እምት ፍልስፍናዎች እና አሰተምህሮቶች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ ካቶሊኩ ፈላስፋ ቅዱስ ቶማስ አኩይናስ ይህንን የተፈጥሯዊ ፍትህ ሃሳብ ወስዶ በማዳበር የተብራራ የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍናን በተዋቂውና Summa Theological በተሰኘው ድርሳኑ በሰፊው ጽፎታል፡፡ በዚህም ምክንያት እንዳንዴ ጸሃፊያን አሪስቶትል የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍና ጠንሳሽ እንደሆነ ሲጽፉ ሌሎች በበኩላቸው ይህንኑ በመቃወም አሪስቶትል የዚህ ፍልስፍና ጀማሪ እንዳልሆነና እርሱ ለማብራራት የሞከረው ሌላ ጽንሰ ሃሳብ ነበር በማለት ይከራከራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከሕግ ፍልስፍና ውጪም ቢሆን የአሪስቶትል አሻራ በቀላሉ የሚደበዝዝ አይደለም፡፡














ምዕራፍ ሁለት

ሕግ እና የሞራል ፍልስፍና

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ግለሰባዊ ሞራል የማህበረሰባዊ ሞራል ነጸብራቅ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሁለትዮሽ ጉድኝት ስብስብ በድህረ ዘመናዊነት እየተዋጠች ባለችው ዓለማችን እየተቀየረ ይገኛል፡፡ ለዘመናት የግለሰቡ ማንነት የማበረሰባዊ እሴት ውጤት እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ያከበረውን ግለሰቡ ያከብራል፤ ማህበረሰቡ ያዋረደውን ግለሰቡም ይንቃል ያዋረዳል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ቡድናዊ የሞራል እሴት በአንድ ቦታ ብቻ ረግቶ አልያም በተለያየ ጊዜ የተለያየ መልኮችን ይዟል፡፡ ማህበረሰባዊ ሞራል በአንድ ቦታ ረግቶ በቆየባቸው ጊዜያቶች በሙሉ ግን ወደ ማህበረሰብ አቀፍ ሕግነት ተቀይሯል፡፡ በዘመነ ብሉይ የፍትሕ ተቋማት፣ የተጻፉ የሕግ ድርሳናት፣ የሰለጠኑ የሕግ ባለሙያዎች ፤ የሕግ ትምህርት ቤቶች እና መሰል ኩነቶች ባይኖሩም ልማዳዊ ሕግ እና ፍልስፍናዊ የእውነት ጥማት ነበር፡፡ 

በጊዜ ሂደት ውስጥ ዘመናዊ ሕግጋት ከማህበረሰባዊ ሞራል እና ልማዳዊ ሕግጋት መፍለቅ ጀመሩ፡ የተጻፉ ዘመናዊ ህግጋት ፅንሰት ሮማውያን የጠንካራ ውትድርና፣ ምህንድስናና የፖለቲካዊ ባህል መስራች ናቸው፡ በዚህ ዘመን የአብዛኛው አውሮፓ እና የኮንቲኔንታል የፍትህ አስተዳደር ስርዓት የሚከተሉ ሃገራት በሙሉ ስራ መሰረታቸው የጥንታዊ ሮማውያን ሕግ የፍትህ አስተዳደር፤ ባህልና ፍልስፍና ነው፡፡ 

    ዓለምአቀፍ ደረጃ ሕግና ሞራሊቲ የሚመነጩት ከማህበረሰቡ ባህል ወግና ታሪክ ውስጥ ነውለ፡፡ ይሁንና በህግና በማህበረሰባዊ ሞራል  መሃከል አንድነት እና ልዩነት አለ፡፡ መንግስታት በሚያወጧቸው ሕግጋት እና በማህበረሰባዊ የሞል ሕግ መሀከል ያሉትን መጠነኛ ልዩነቶች ማብራራት ይገባል፡፡ የመንግስታት ህግጋት በአብዛኛው የተጻፉ እና የታወጁ ናቸው፡፡ አዋጆች፤ ደንቦች እና መመሪያዎች በሙሉ በነገስታት ፣ በፓርላማዎች እና ካቢኔዎች ከጸደቁ በኋላ በወረቀት ታትመው ለሕዝብ ይሰራጫሉ፡፡ ዘመናት ካለፉ በኋላ ሲሻሩ እን ሲሻሻሉም እንዲሁም ታትሞ በሚሰራጭ ሕግ ነው፡፡ በማህበረሰባዊ የሞራል ሕግ በወረቀት ወይም ድርሳን ታትሞ ለሕዝቡ የሚራች አይደለም፡፡ 

    ማህበረሰባዊ የሞራል ሕግ በታሪክ ውስጥ ቀን በቀን አድጎ በህዝቡ ሕሊና እና ባህል ውስጥ የሚሰርጽ አስገዳጅነት ያው የሕይወት ዘይቤ ነው፡፡  ሌላው የመንግስት ሕግ ተቋማትን ይፈጥራል ፤ ሕጉን የማያስፈጽሙ፤ የሚያስተምሩ፤ የሚተረጉሙ፤ የሚረቅቁ፤ የሚያጸድቁ፤ የሚያሻሽሉ እና የሚሽሩ ሰዎች እና ተቋማት በግልጽ እና በዝርዝር ተለይተው በእነዚያው ህግጋት ይቀመጣሉ፡፡ በማህበረሰቡ የሞራል ሕግ ግን እነዚህ ሰዎች እና ተቋማት በዝርዝርና ግልጽ በሀነ መንገድ ተለይተው አይቀመጡም ፤ የሉም ማለት ግን አይደለም እንደ ሁኔታው ይቀያየራሉ፤ ይለዋወጣሉ ሆኖም ማህበረሰቡን ሞል ጠባቂ የሆኑትን ሰዎች እና ተማትን ግን ህዝቡ ለይቶ ያውቃቸዋል፡፡ ሌላው የምግስት ሕግ ሲጣስ የሚጣለው ቅጣት እና የቅጣት ዓይነት አስቀድሞ በሕግ የተደነገገ እና የታወቀ ነው፡፡ ቅጣቱን የሚያስፈጽሙ ተቋማት እና ግለሰቦችም ይታወቃሉ፡፡ በማህበረሰባዊ የሞራል ሕግ ግን የቅጣቱ አይነት እና ረጃ በግልጽ የተቀመጠ ባይሆንም ሊገመት የሚችል አይነት ነው፡፡ ቅጣቱን የሚጥሉት ሰዎችም አንዳንዴ የታወቁ እነዳንዴም የማይታወቁ በመሆኑ ግልጽ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድን ግለሰብ በድርጊቱ ምክንያት ከማህበረሰቡ ማግለል ቅጣት ከሆነ ፈጻሚው ማህበረሰቡ ራሱ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በርግጥ አንዳንድ የልማድ ህግጋት ዘመናዊ ከሚባለው የመንግስት ሕግ እኩል ተቋማትን መስርተውና ሕጎቻቸውን የሚያስፈጽሙ ሰዎች ሰይመው ይንቀሳቀሳሉ፤ ከመንግስት ሕግ የሚለያቸው ያልተጻፉ በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ 

ሆኖም ሕግ በመንግስታት ተረቅቆ እና ጸድቆ በመጽሐፍታትም ለህዝብ ከመድረሱ በፊት መሰረታዊ የሆነው ባህሪው አስቀድሞም ቢሆን ለማህበረሰቡ ልማድ እና የኑሮ ዘይቤ ውስጥ የሚገኝ ነበር፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ሞራል ሕግን የሚፈጥር ቢሆንም ሕግ ሞራልን አይፈጥርም ለማለት አይቻልም፡፡ በሁለቱ መሃከል ለዘመናት የቆየ የምክንያትና ውጤት ግንኙነት አለ፡፡ በዚህም ምክንያት በታሪክ ውስጥ የሕግ ፍልስፍናዎችን፤ አስተምህሮዎችን፤ መርሆዎች እና ጽንሰ  ሃሳቦችን ውልደት፣ እድገትና ሞት ከመመርመራችን በፊት ለእነዚህ የሕግ ፍልስፍናዎች መሰረት የሆኑትን የሞራል ፍልስፍናዎች በጥቂቱም ቢሆን መዳሰስ ይኖርብናል፡፡ 

ምግባራዊነት

ምግባራዊ የሞራል ፍልስፍና ከባህሪ ልዕቀት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ለጥንታዊ ግሪኮች የሰው ልጅ ዋንኛ የሕይወት ጥረት በጤና፤ በስልጣን፣ በእውቀት እና በሃብት ልዕቀትን ማግኘት ነበር፡፡ የሰው ልጅ በሌሎች የሕይወት ክፍሎች ልቀትን ለማግኘት እንደሚተጋው በሞራላዊ ሕይወቱም ይህንኑ የሞራላዊ ልዕቀት ለማግኘት መጣር እንዳለበት እና ለዚህ ደግሞ ሞራላዊ ልዕቀት የሚያስገኙለትን የግል ባህሪያት አውቆ ሊያዳብራቸው እንደሚገባ አስተምረዋል፡፡ 

     የሞራል ልዕቀት የሚያስገኘውን ምግባር በምን እናውቃለን? እንዴትስ ልናዳብረው እንችላለን? ሰናይ ምግባር እና እኩይ ምግባር በምን ይገለጻል ግለሰቡስ አንደኛውን ሸሽቶ ሌላኛውን ሊያዳብር የሚችለው እንዴት ነው? “ ምግባረ ሰናይነት” ን መለኪያው እና ማወቂያው መንገዱ ምንድነው?የሚሉትን ጥያቄዎች የግሪክ ፈላስፎች በልዩ ልዩ መንገዶች መርምረዋቸዋል፡፡ ለታዋቂው ፈላስፋ ሶቅራጥስ ምግባረ ሰናይነት ከሞራል ዕውቀት ይመነጫል ምግባሩ ብልሹነት ደግሞ የሞራል ዕውቀት ከማጣት የሚመነጭ ችግር ነው፡ ለሶቅራጥስ ሰዎች በአስከፊ እና አስነዋሪ ድርጊት ውስጥ የሚሰማሩት ተገቢውን የሞራል ትምህርት ስላላገኙ ነው፡፡ በተቃራኒው ሰዎች በበጎ ተግባር የሚሰማሩት እና ቅን ባህሪ የሚያሳዩት ትክክለኛ የሞራል ትምህርት ስላገኙ ነው፡፡ ምክንያቱም ስነ-ምግባር የሞራል ትምህርት ውጤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ሶቅራጥስን ሰዎች ትክክለኛውን የሞራል ትምህርት አግኝተውም ቢሆን ምግባረ ብልሹ ሊሆኑ አይችሉም ወይ? በሚል ለሚቀርብለት ጥያቄ የሚሰጠው መልስ እነዚህ  የሞራል ትምህርት ተሰጣቸው እንጂ የሞራል ዕውቀት አላገኙም፤ የሞራል ዕውቀት ያለው ሰው ምግባረ ብልሹ ሊሆን አይችልም ሲል ይመልሳል፡፡ 

     የሞራል ትምህርት አግኝተው ቢሆን ምግባረ ብልሹ የሚሆኑ ሰዎች ምግባራቸው መጥፎ ሆኖ ሳለ ጥሩ እየመሰላቸው የሚያደርጉት ናቸው፤ ይህ ሁኔታ “ የሶቅራጥስ አያዎ “ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሶቅራጥስ ስለምግባረ ሰናይነት ሲያስተምር የሶቅራጥስ ምልልስ በሚል የሚታወቀውን የራሱን የማስተማር ዘዴ ይጠቀም ነበር፡፡ በመሆኑም ሰዎች የሚከተሏቸው ምግባራዊ የሞራል ፍልስፍናዎች በሶቅራጥስ የጥያቄ ብዛት ይፈተኑ ስለነበረ በሶቅራጥስ የተማረ ሰው ተገቢውን የሞራል ዕውቀት ማግኘቱ አያጠራጥርም፡፡ 

     ለአሪስቶትል መልካም ምግባር ማለት በሁለት ጽንፍ ባህሪያት መሃከል ያለ ባህሪ ነው፡፡ ይህ “የመሃከለኛነት መርህ” በሚል የሚታወቀው የአሪስቶትል አስተሳሰብ ምግባረ ሰናይነትን ለማግኘት የሚረዳ ዘዴ መሆኑ በስፋት ተብራርቷል፡፡ ለምሳሌ ጀግንነት የሚባለውን ባህሪ ለመቀዳጀት በፈሪነት እና በጀብደኝነት መሃከል ያለውን አማካይ ስፍራ ማግኘት ይኖርብናል፡፡ ይህ መርህ በተለምዶ “ወርቃማው መሃከለኛ” በመባል ይታወቃል፡፡ 

እንዲህ የምግባራዊ የሞራል ፍልስፍና (virtue Ethics)ሰዎች ምግባረ ብልሹ ከመሆን ተቆጥበው በስነ-ምግባር ታንጸው ግብረ- ገብነት ያለው ሕይወት እንዲመሩ የሚያስተምር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሰዎች፤ መንግስታት፤ ሃይማኖቶች እና ልዩ ልዩ ተቋማት ትክክለኛውና ለእውነት የቀረበው ሞራላዊ ምግባር ወይም ባህሪ ምንድነው?የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ባህሪ በጊዜ ፤ በቦታ፤ በባህል፤ በትምህርት ሁኔታ፤ በመደብ እና መሰል ሁነቶች የሚለያይ በመሆኑ ዘላቂነት ያለው የሞራል ፍልስፍና አድርጎ ለመውሰድ አስቸጋሪ ነው፡፡ 

ጠቀሜታዊነት

     የዚህ ፍልስፍና አባት ታዋቂው እንግሊዛዊ ፈላስፋ ጄርሜ ቤንታም ነው፡፡ ቤንታም ለእንግሊዝ ህግና ፖለቲካዊ ፍልስፍና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የጀርሚ ቤንታም ተጽእኖ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ አጽሙ ደርቆ ህዝብ እስከ ዛሬ እንዲጎበኘው ተደርጓል፡፡ በሕይወት ዘመኑ ሲኖር ግን በራሱ እጅ ያረቀቀው የወንጀለኞች እስር ቤት  ዲዛይን ጸድቆ እንዲገነባ ከፍተኛ ውትወታ ሲያደርግ ቢኖርም የዚህ ማረሚያ ቤት ያለመገንባት ቅስሙን እንደሰበረው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ቤንታም በተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍና የሚስማማ ከመሆኑም ባሻገር ኢ- አማኝ (Atheist) ነበር፡፡

     ከእርሱ ኅልፈት በኋላ የእርሱ ደቀመዝሙር የነበረው ስቲዋርት ሚል የእርሱን መሰረታዊ ፍልስፍና ደግፎ አንዳንድ ትንታኔዎቹን በመንቀፍ የጠቀሜታውያን የሞራል ፍልስፍና ይበልጥ እንዲስፋፉ አድርጓል፡፡ 

     ለቤንታም የሰው ልጅ በሁለት ጌቶች ስር ይገዛል፤ ደስታና ሐዘን/ እርካታ እና ስቃይ፡፡  በቅድሚያ ሰዎች በእነዚህ ሁለት ጌቶች እየተገዙ እንደሚኖሩ ማመን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የጠቀሜታዊን የሞራል ፍለስፍና መሰረት ይህ እሳቤ ነው፡፡ እያወቅነውም ሆነ ሳናውቀው፤ ፈልገንም ሆነ ሳንፈልግ እነዚህ ሁለት ጌቶች ሕይወታችንን ይገዙታል፡፡ ለዚህ የሞራል ፍልስፍና መዳበር ከጀርሚ ቤንታም ቀጥሎ የተነሳው የቤንታም ወዳጅ ስቱአርት ሚል  ጠቀሜታዊ የሞራል ፍልስፍና እንደሚያትተው የሰው ልጆች ተግባር ወይም ባህሪ ሞራል መሆን ወይም አለመሆኑን ማወቅ የምንችለው በሚሰጠው ተጨባጭ ጥቅም ነው፡፡ አንድም ምግባር ለአድራጊው ወይም ከዚያ ተርፎ ላሉ ሰዎች ምንም አይነት ጥቅም የማያስገኝ ከሆነ ሞራላዊ ተግባር አይደለም፡፡ 

የጠቀሜታዊ የሞራል ፍልስፍና ሲጠቀለል “መጠነሰፊ ደስታን ለብዙ ቁጥር ሕዝብ የሚሰጥ” በሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ደስታ መልካምና በራሱ የሰው ልጆች ግብ ሊሆን የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ ተግባሩን መመዘን ያበት በዚህ ድርጊት ከፍተኛ ደስታን ላገኝበት እችላለሁ ወይ? በሚል መለኪያ ብቻ ነው፡፡ ሰዎች በዚህ ድርጊታቸው ደስተኛ እየሆኑ ሲሄዱ የእነሱ ደስታ ተደምሮ ማህበረሰባዊ ደስታን ይፈጥራል፡፡ 

ቤንታም በዚህ ፍልስፍና የሚያምነው ጥብቅ በሆነ መንገድ ከመሆኑ የተነሳ “መጠነሰፊ ደስታ ለብዙ ቁጥር ሕዝብ” የሚለው ፍልስፍናውን ለመለካት” ፌሊሲፊክ ካልኩለስ” የተባለ የሂሳብ ቀመር አዘጋጅቶ ነበር  በዚህም መሰረት አስራ ሁለት የስቃይ አይነቶችን እና አስራ አራት የደስታ /እርካታ አይነቶችን የለየ ሲሆን እያንዳንዱ ድርጊት በተለያዩ ሁኔታዎች የሚያስገኘውን የስቃይ ወይም እርካታ ደረጃ ለመለካት የሚቻልበትን አሰራር ዘርግቷል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቤንታም ይህንነ አስተሳሰቡን የምር ይከተል  እንደነበር ነው፤ ምክንያቱም ይህ መርህ ወደተለያዩ መንግስታዊ የሕግ ማእቀፎች እንዲተገበር ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ 

በኋላ ላይ የሚል ጠቀሜታውያንን “በመርህ ጠቀሜታዊነት” እና “ የድርጊት ጠቀሜታዊነት” በማት ለይቷቸዋል፡፡ መርህ ጠቀሜታውያን አንድ ድርጊት ምንም እንኳ ክፍተኛ ደስታን የሚያስገኝ ቢሆንም በመርህ ደረጃ ኢ- ሞራላዊ ከሆነ ጥቅም አልባ እንደሆነ ሲያስረዱ የድርጊት ጠቀሜታ ግን ድርጊቱ ከፍተኛ ደስታ / እርካታ እስካስገኘ ድረስ አድራጊው ድርጊቱ ኢ-ሞራላዊ ስለመሆኑ መጨነቅ እንደሌለበት ያስረዳል፡፡ ለሚል ትክክለኛው መንገድ  መርህ ተኮር ጠቀሜታዊ የሞራል ፍልስፍና ነው፡፡ እነዚህ ፍልስፍናዎች በአውሮፓ ውስጥ በተነሱ የሕግና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ቀላል የማይባል ተፅእኖ ያሳረፉ እንደመሆናቸው እንደ ዋዛ ልናያቸው አይገባም፡፡ 





ግዴታዊነት

ኢማኑኤል ካንት የዚህ ሞራል ፍልስፍና መስራች ነው፡፡ ካንት በአውሮፓ የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ የጣለ ከመሆኑ የተነሳ እንዳንዶች የአውሮፓ ፍልስፍና ታሪክን ቅድመ ካንት እና ድህረ ካንት በሚል ይከፍሉታል፡፡ ካንት በዲበአካላዊነት፣ በትምህርት ፣ በአብርሆት በእውቀት ፍልስፍናዎች የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ችሏል፡፡ በወቅቱ ውስብስብ እና ከባድ ከተባለው የዲበአካላዊ ፍልስፍና ድርሳኑ እስከታችኛው ማህበረሰብ ድረስ የተነበበለትን “ አብርሆት ምንድነው?” የሚለውን ታዋቂ ጽሁፉ ድረስ ጠቃሚ ሀሳቡን ለዓለም አበርክቷል፡፡ 

    በዚህ ክፍል ስለሞራል ፍልስፍናው ለማንሳት እንሞክራለን፡፡ ለካንት የሞራል ሕይወት የምክንያት እና ግዴታዊ ሃላፊነትን የመወጣት ጥምረት ነው፡ ሁሉም ሰዎች የኃላፊነት ግዴታቸውን ሲወጡ ምክንያታዊ በሆነ የሕይወት መስመር እንደሚመሩ ይጠቁማል፡ ምክንያቱም እንስሳት ተግባራቸው በደመነፍሳዊ ስሜት እንጂ በአመክንዮ እና የግዴታ ስሜት አያስደግፉም፡፡ የሰው ልጅ ግን በአንድ አይነት የሞራል ግዴታ ስር ነኝ ብሎ ራሱን በፍላጎት የሚያስገዛ ብቸኛ ፍጡር ነው፡፡ እውነተኛ የሞራል ሕይወትን መምራት ማለት ሞራላዊ ግዴታን መውጣት ማለት ነው፡፡ 

    በመሆኑም የሞራል ግዴታ ሁሉን አቀፋዊና አጠቃላይ መሆን አለባት፡፡ አንድ ሰው ተግባሩን ሲፈጸም ዓለምዓቀፋዊ የሆነ ሕግ አውጭ አካል መሆኑን እያሰበ እና ይህ ተግባር በሁሉም ሰው እና በሁሉም ቦታ ተፈጻሚ ሊሆን መቻሉን እየመረመረ መሆን አለበት፡፡ ይህም ማለት ራሱን የሚያስገዛበት የሞራል  መርህ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሰው ልጅ የሚስማማ እና በሁሉም የሰው ልጅ ያለምንም ችግር ሊፈጸም የሚችል መሆኑን አርግጠኛ መሆን መቻል አለበት፡፡ 

     ለካንት ሰዎች እና የሚፈጽሙት ሞራላዊ ተግባሮቹ በራሳቸው እንደግብ ሊታዩ ይገባል እንጂ ወደ ግብ ሊያደርስ የሚችሉ መንገዶች መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ ልንከውናቸው አይገባም፡፡ ሰዎችን ስንቀርብ እና ከእነርሱ ጋር ልዩ ልዩ የሕይወት መስተጋብር ስንፈጽም በራሳቸው ፍጹም የሆኑ ግቦች እንደሆኑ እያሰበን እንጂ እነሱን በመጠቀም አንድ አይነት ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ኢ-ሞራላዊ ምግባር ነው፡፡ 

     በመሰረቱ ከመልካም ምግባሮች ሁሉ ተቀዳሚ የሚሆነው ቅን ሃሳብ (good will ) ነው፤ ሌሎች ምግባሮች መልካም ቢሆኑ አንኳ ለክፉ ዓላማ ልንጠቀማቸው እንችላለን ለምሳሌ “ታታሪነት” መልካም ባህሪ ቢሆንም ሰዎች ለተሳሳተ ዓላማ ታታሪ ከሆኑ የምግባራቸው ውጤት ኢ-ሞራላዊ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ቅን አሳቢነትን  ግን ለክፉ ዓላማ ማዋል የማይችል በመሆኑ በራሱ እንደ ግብ ሊታይ ይችላል፡፡ በመሆኑም ሞራላዊ ተግባሮች በሙሉ በቅን አሳቢነት ላይ ከተመሰረተ ግዴታ ሊመነጩ ይገባል፡፡ የሞራል ግዴታዎችም ቢሆኑ ለሁለት መከፈላቸው አልቀረም፡፡ ምናባዊ የሞራል ግዴታ እና ኢ-ፍጹማዊ የሞራል ግዴታች ናቸው፡፡ ፍጹማዊ  እንዳይል ያገድደዋል፡፡ 

    ምናባዊ የሞራል ግዴታ አንድ ሰው ግዴታውን ለተመረጡ ሁኔታዎች ሲል ቢቀይር ሊፈቀድለት ይገባል የሚል ሲሆን ከድርጊቱ ጀርባ ግዴታ ሳይሆን ፍላጎት ብቻ በመኖሩ አድራጊው ካሰኘው ሊተወው ይችላል ፡፡ ለካንት ፍጹማዊ የሞራል ግዴታዎች ሁልጊዜም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው እና በሁለቱ መሃከል ግጭት ቢነሳ እንኳ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ለካንት መልካምነት እራሱን በፍቃድ እና በቅን አሳቢነት ፍጹማዊ ለሆነ የሞራል ግዴታ ማስገዛት ነው፡፡ ይህ የሞራል ግዴታም ሁሉንም ሰዎች እኩል የሚያይ፤ ሁሉንም ሰዎች እንደ ግብ የሚገነዘብ ነው፡፡ በዚህ የሞራል ፍልስፍና የሚገዛ ሰው ሁልጊዜም ቢሆን የኔ ድርጊት ለሰው ልጆች ሁሉ ህግ ሊሆን ይችላል ወይ? ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ 

ህግ እና ፍትህ

ሕግ ፍትህን የምናገኝበት መሳሪያ ነው፡፡ በሕግና ፍትህ መሃከል የምክንያት እና ውጤት ግንኙነት መኖሩን ልንዘነጋ አይገባም፡፡ ፍትህ የሕግ ውጤት እና ዓላማ ሲሆን ህግ ደግሞ ፍትህን የምናገኝበት ምክንያት እና መንገድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ህጎች ወደ ፍትህ አይወሰዱም አንዳንድ ሕግጋት ከፍትህ እና ርትዕ ጋር ይጋጫሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎች መንግስት ለሚያወጣቸው ሕግጋት ባለመገዛት አመጽ እና አብዮት ያስነሳሉ፡፡ በመሆኑም “ፍትሕ” የሚባለውን ጽንሰ ሃሳብ መተርጎም እና መበየን ይኖርብናል፡፡ ፍትህን መተንተን እና ማስረዳት ፍልስፍና ከተጠነሰሰበት ቀን ጀምሮ የሚያከራክር እና የሚያጨቃጭቅ ጉዳይ እንደሆነ አለ፡፡ ፍትህን ለሁሉም ሰዎች ባህል፣ ቋንቋ እና ዘመን በሚመች መልኩ መተርጎም እጅግ ከባድ ተግባር ነው፡፡ ለዚህም ምክንያት አፍላጦን የጻፈው ታላቅ ድርሳን “ሪፐብሊክ” የሚጀምረው ሶቅራሰጥስ ከሁለት ወዳጆች ጋር ከአንድ ስርዓት አምልኮ እየተመለሱ ሳለ በነፋሻማ የባህር ዳርቻ አጠገብ እየተጓዙ “ፍትህ” ምን ማለት እንደሆነ ሲጠይቃቸው ነው፡፡ ይህም የሆነው ፍልስፍና ትክክለኛውን መልስ በማግኘት ሳይሆን ትክክለኛውን ጥያቄ በመጠየቅ የሚገኝ ሃሳብ በመሆኑ ነው፡፡ ፍትህን የሚቃረኑ ሕግጋትን መቃወም ፍትሐዊ ነው? ፍትህን የሚቃረኑ ሕግጋትን በምን እናውቃለን?

     ፍትህን የሚቃረኑ ሕግጋት የምን ያህሉን ሕዝብ መብት ሲጥሱ ኢ- ፍትሐዊ ሊባሉ ይችላሉ? የፍትህ ምንጭ እና ተርጓሚ ማነው? ለተማረው፣ ለባሃብቱ እና ለፍትሕ መገዛት ማንን ይጠቅማል? እነዚህን መሰል ጥያቄዎች መንግስት እና የሕግ እና ፍትሕ አስተዳደር ከተቋቋመ ዘመን ጀምሮ እየተጠየቁ እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል፡፡ 

ለምሳሌ በግሪክ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ንጉስ ድራኮን የሚባል መሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የአቴንስን ሕግጋት በጽሁፍ አስፍሮ በእንጨት ጣውላዎች ላይ በማስቀረጽ የአቴንስ ዜጎች ሁሉ የሚያውቋቸው ቦታዎች ላይ እንዳሰቀላቸው ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሕግጋት በጣም ከፍተኛ እና አስፈሪ ቅጣት የሚጥሉ ከመሆናቸው የተነሳ በስርቆት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን ሁሉ በሞት የሚቀጡ ነበሩ፡፡ በመሆኑም አስከ ዛሬ ድረስ ለተፈጥሮ እና ሰብዓዊነት የማይመጥኑ ኋላ ቀር ሕግጋት ሲያጋጥሙ የድራኮን ሕግጋት ይባላሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመሃከለኛው ዘመን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የክርስትና እምነትን ቀኖና ዶግማ ያፋለሱ መናፍቃን እና በጥንቆላ እና መተት ስራ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን በአደባባይ በንጉሶቹ ትእዛዝ ታቀጥላቸው ነበር፤ የሚገርመው ግን እነዚህ በጥንቆላ የተጠረጠሩ ሰዎች እና “መናፍቃን” ተብዬዎች ለዚሁ ጉዳይ በተቋቋመ የፍርድ ጉባኤ ፊት ቀርበው ራሳቸውን መከላከል ነበረባቸው፡፡

 እነዚህ የጠቀስናቸው ሕግጋት እና የፍርድ ሂደቶች አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ስንመለከታቸው አሰቃቂ እና አስነዋሪ ቢመስሉም በዚያ ዘመን ለሚኖሩ የፍትሕ አካላት እና ህጎች ግን መደበኛ የመንግስት አሰራር ነበሩ፡፡ በዚያን ዘመን የሚኖር አንድ በመናፍቅነት ተጠርጥሮ የተያዘ ግለሰብ ባልተቀበለው ሕግ እና የፍርድ ሂደት ፊት ቀርቦ ራሱን እና ቤተሰቡን ከአሰቃቂ ፍርድ ለማዳን ሲል ክሱን ተቃውሞ መከላከል ይጠበቅበት ነበር፡፡ ከእነዚህም የሩቅ ዘመን ትውስታዎች እና ታሪኮች ወደ ቅርቡ ብንመለስ እንኳ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የነበሩ የቅኝ ግዛት ህጎች ነጮች እና ጥቁሮች ፤ጥቁሮች እና ”የተለዩ“ ጥቁሮች የሚለያዩበት እና አንዱ ከአንደኛው የተሻለ መብት በመስጠት የተከፋፈለ የአኗኗር ስልት አስፍነው ነበር፡፡ 

እነዚህ ከፋፋይ ሕግጋት ከብዙ ትግል በኋላ በመላው ዓለም ኢ-ሰብዓዊ እንደሆኑ ዛሬ ቢታወቅም በዚያ ዘመን ግን ነጩም ጥቁሩም እውነት እና ትክክል እንደሆኑ አድርጎ ይቀበላቸው ነበረ፡፡ ከዚህ የምንረዳው አንድ ትልቅ ቁም ነገር ሕግጋቱ በተለይም ሰው ሰራሽ ሕግጋት በዘመን እና በሳይንስ እድገት እየተሻሩና እየተለወጡ እንደሚሄዱ ነው፡፡ ፍትህ ግን ዘመን- አይሽሬ ፅንሰ- ሃሳብ ነው፡፡ በዚህ ዘመንም መንግስት ሕገ-ወጥ እና ወንጀል ብሎ የፈረጃቸው ተግባራት ከሃምሳ እና መቶ ዓመት በኋላ ግን የሚፈቀዱ እንዲያውም የሚበረታቱ ተግባራት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በሕግ እና ፍትህ መሃከል ያውን ግንኙነት ጥረት ባለ መልኩ አብራራቶ መበየን የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ 

    ፍትህን ዘመን ተሻጋሪ በሆነ መንገድ ለመረዳት ልንተረጉመው የሚገባው ከሕግጋት ጋር በማያያዝ ሳይሆን ከእውነት ጋር በጥልቀት በማገናዘብ ነው፤ ምክንያቱም እውነት የሆነው ነገር ምን ጊዜም ፍትሐዊ ነው፡፡ እውነት ደግሞ ዲበአካላዊ የሆነ ይዘት እና ትርጉም አለው፡፡ እውነት ስለዲበአካላዊነት ካለን አመለካከት ይመነጫል፡፡ ሰውን መግደል የተሳሳተ እና እውነት አልባ ተግባር የሚሆነው ከዚሁም ጋር ተያይዞ ኢ-ፍትሐዊ እንደሆነ በማሰብ የምንከራከረው “ግድያ” የተሳሳተ ተግባር መሆኑን የምንከተለው ዲበአካላዊ ፍልስፍና  የሚያመላክተን ከሆነ ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶች እውነት የማይለውጥ እና የማያረጅ እንደሆነ ሲያስረዱ አንዳንዶች ደግሞ እውነት በጊዜ እና በዘመን የሚቀያየር  እንደሆነ በማመን ይከራክራሉ፡ እውነት የሆነውን ነገር የምናውቅበት ፍልስፍና ደግሞ የእውቀት ፍልስፍና  ይባላል፡፡ 

በመሆኑም ፍትህ በአለምዓቀፍ የሕግ ስርዓት ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል፡፡ እነዚህም የሀብት ክፍፍል ፍትሕ ፤ስነ-ስርዓታዊ ፍትህ; የእርምት ፍትህ ፤ የተሃድሶ ፍትህ; የተፈጥሮ ሃብትና ጥበቃ ፍትህ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለአያሌ የፖለቲካ አብዮቶች ምክንያት የሆነ ነው፡፡ ጥቂቶች በብዙሃኑ ሃብት እና ጉልበት ተጠቅመው እየተንደላቀቁ ሲኖሩ ሰፊው ህዝብ ደግሞ በድህነት አረንቋ ውስጥ ሊዘፈቅ ስለማይገባው መንግስት በሃብት ከፍ ካሉት በግብር፤ መዋጮ እና ቅጣት ሃብት እየሰሰበሰበ ለብዙሃኑ ሊያከፋፍል ይገባዋል በማለት ያስተምራል፡፡ ስነ-ስርዓታዊ ፍትህ በአብዛኛው የሚገለጸው በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ቢሆንም ለፍትሐብሔር ጉዳዮችም ጠቃሚ ነው፡፡

 በመሰረታዊነት ህግ ከግቡና ውጤቱ ይልቅ ሂደቱ ፍትሃዊ ሊሆን እደሚገባና በሀገርኛ አባባል “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሆነ አሰራር ኢፍትሃዊ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በወንጀል ሂደቱ አንድ ተጠርጣሪን በመደብደብ እና በመግረፍ የሚገኝ የእምነት ቃል በፍትሃዊ ሂደት ያልተገኘ በመሆኑ ውድቅ ሊደረግ ይገባዋል፡፡ ፈረንጆቹ ይህንኑ ሃሳብ Due process of Law በማለት ይገልጹታል፤የፍትህ ስርዓት ተገቢውን ሂደት ማለፍ ስለሚገባው በዚሁ መልክ የተገኙ ማስረጃዎችና ፍርዶች ብቻ ፍትሐዊ ናቸው ብለን ማመን አለብን፡፡ የእርምት ፍትህ ከጉዳት እና ካሳ ጋር እንዲሁም ከወንጀል እና ቅጣት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ አንድ ሰው በእውቀትም ሆነ በቸልተኝነት በአንድ ሰው ላይ የወንጀል ድርጊት ከፈጸመ  ተገቢ እና ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃ ሊወስድበት ይገባል፡፡ ይህ እርምት የእርምት አላማ ማስተማርና ማረም ፤ መቀጣጫነት ፤ በቀል  ወይም ማቀብ  ሊሆን ይችላል፡፡ 

     ሌላው በቸልተኝነት የተፈጸመ ጉዳት ቢሆንም እንኳ፣ በአንድ ግለሰብ ላይ የአካል ጉዳት ያደረሰ ሰው ለዚሁ ጉዳት ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ ለተጎጂው ወይም ለቤተሰቡ መክፈል ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም የእርምት ፍትህ በወንጀል ወይም በጉዳት አማካኝነት የተዛባውን ማበረሰባዊ ሚዛን  መልሶ ማቀናት ነው፡፡ የተሃድሶ ፍትህ ግን ሰዎች ባደረሱት ጉዳት ልክ ቅጣት ሊደርስባቸው አይገባም ምክንያቱም ይህ የፍርድ ሂደት የአሸናፊ እና ተሸናፊ ስነ-ልቦና የሚፈጥር በመሆኑ ዘላቂ የሆነ ሰላም እና ፍትህ ለማህበረሰቡም ሆነ ለባለ ጉዳዮች አያመጣም ፡፡ 

በመሆኑም በእርቅ እና ድርድር ባለጉዳዮቹን በተቻለ መጠን ወደነበሩበት እኗኗር ልንመልሳቸው ይገባል ሲል ይከራከራል፡፡ የተፈጥሮ ሃብትና ጥበቃ ፍትህ በበኩሉ ፍትህ ለሰዎች ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ለሚገኙ እንስሶች ፣ እጽዋት እና ግዑዛን ሁሉ ሊሠጥ እንደሚገባው ያስተምራል፡፡ በመሆኑም ሰዎች የአካባቢያቸው አስተዳዳሪ እንጂ ገዢዎች እና ባለመብቶች አይደሉም፤ ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸው የተፈጥሮ አካል በመሆናቸው ተፈጥሮን የመበዝበዝ የተሻለ መብት የላቸውም ፡፡ ይህ አይነቱ የገዢነት እና የበዝባዥነት አስተሳሰብ ሰው የዓለም ማዕከላዊ  እንደሆነ አደርጎ ከሚያስብ አስተምህሮ የመነጨ በመሆኑ አሁን የምናየው አካባቢያዊ ብክለት


 ሊያስከትል ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሰዎች የተፈጥሮ አካል እንደመሆናቸው ለተፈጥሮ ሕግጋት  መገዛት አለባቸው፡፡፤ ምክንያቱም በአካባቢያቸው ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በባለ አደራነት መጠበቅ ይገባቸዋል፣ የመንግስት ሕግጋትም ይህንኑ ሊያጸኑ አንደሚገባ አስተምህሮው ያረጋግጣል፡፡ 













ምዕራፍ ሁለት

የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍና

ለዚህ ፍልስፍና ሕግ ተፈጥሯዊ ነው፤የሰው ልጆች መንግስት መስርተው በሕግ መተዳደር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የሚያወጧቸው ሕግጋት መሰረታቸው ተፈጥሮ ነው፡፡ ተፈጥሮ ስንል ግዑዙን እና ሕይወት ያለውን ሁሉ የሚያጠቃልል ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን ፍጥረታት ከሰራው ልዓለ-ኃያል ፈጣሪ ጋርም ይገናኛል፡፡ በመሆኑም ሰዎች በመንግስታቸው ውስጥ ወንጀልን ለመቆጣጠር፤ ንግድን ለማበረታታት እና የግለሰቦችን መስተጋብር ለማሳለጥ ከሚያወጧቸው ሕጎች ጀርባ ያለው እሳቤ እና የሞራል መርህ የተገኘው አስቀድሞም ቢሆን በተፈጥሮ ውስጥ በተቀመጠ ስርዓት ወይም ይህን የተፈጥሮ ስርዓት ከፈጠረው አምላክ እንደሆነ ፍልስፍናው ያትታል፡፡ በርግጥ የዚህ ፍልስፍና ተከታዮች በአብዛኛው አማኞች ቢሆኑም በአምላክ የማያምኑ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የተጥፈሮ ሕግ ከፈጣሪ የተሰጠ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ እንደማይገባ ተናግረዋል፤ ጽፈዋል፤ አስተምረዋል፡፡    

     ይህ የህግ ፍልስፍና የሰው ልጅ በቅድሚያ ከመሰረቱት የሕግና የፖለቲካ ፍልስፍናዎች ስር የሚመደብ ነው፡፡ የሰው ልጅ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ታግዞ እንደዛሬ ተፈጥሮን በክፉም ሆነ በደግ ለመቀየር እንደሚችል ሳያስብ እና ሳይችል በፊት በተፈጥሮ ሕግጋት ስር እንደሚገዛና ከዚያም አልፎ ይህንን የተፈጥሮ ሕግ የፈጠረ እና የሚዘወር አንድ ሚስጥራዊ ሀይል መኖሩንም ጭምር ያምን ነበር፡፡ በመሆኑም ተፈጥሮን እና ተፈጥሯዊ ነገሮች ማምለክ እና መማጽን እንደልማድ ሆኖ ዛሬም ድረስ በ21ኛው ክፍለ ዘመን  በአንዳንድ ባህሎች ይስተዋላል፡፡ ይህ የሕግ ፍልስፍና ሕግጋት በተፈጥሮ የተሰጡ በመሆናቸው ከሰው ልጆች ሊነጠሉ የማይችሉ እና ሊገረሰሱ የማይገባቸው ውስጣዊ ባህሪያት እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም የሰው ልጆች የሚያወጧቸው ሕግጋት ከእነዚህ የተፈጥሮ ባህሪያት ጋር ሊጣረሱ አይገባም፡፡ 


ሶፊስቶች እና አንጻራዊነት

     ሶፊስቶች የሶቅራጥስ ዘመን ተጋሪዎች ነበሩ፡፡ በእነሱ እና በሶቅራጥስ መሀከል የከረረ ጥላቻ እንደነበር ሶቅራጥስ በሚሰነዘርባቸው ዱላቀረሽ ትችት መገመት ይቻላል፡፡ ሶፊስቶች ፍልስፍና ወይም ትምህርት በእለት ተእለት ህይወታችን ላይ የሚጠቅም ክህሎት ሊሰጠን ይገባል እንጂ እንደ ሶቅራጥስ እና ተከታዮቹ ውስብስብ የሆኑ ሃሳቦችን በመመርመር ሊጠመድ አይገባም ይላሉ፡፡ በተጨማሪም በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች በሙሉ ለሰው ልጅ ህይወት ጥቅም እንዴት ሊሰጡ እንደሚችሉ በማሰብ ሊሰሩ እንደሚገባ ለማሳየት እንደ ፕሮታጎረስ ያሉ ስቶይኮች “ሰው የነገሮች ሁሉ መለኪያ ነው” (Man is a measure of all things) በማለታቸው ይታወቃሉ፡፡

      በመሆኑም የተለያዩ ክህሎቶችን ለማስተማር ከተማሪዎቻቸው ገንዘብን ይቀበሉ ነገር፤ ይሁን እንጂ ገንዘብ ተቀብሎ ማስተማር ለሶቅራጥስ ፍልስፍናን እንደመሳደብ ያህል ነበር፡፡በመሰረቱ ሶፊስቶች ለሰው ልጆች ጥቅም የሚሰጡ እንደየንግግር ክህሎት ፤ ጂኦሜትሪ፤ ሒሳብ፤ ሕግ፤ ፍልስፍና እና መሰል ትምህርቶችን እና ዘርፈ ብዙ ክህሎቶች (polymath) ስለሚያስተምሩ በሁሉ ነገሮች ውስጥ ገብተው መፈትፈታቸውን እና ሁሉን አዋቂ ነን ባይነታቸውን ሶቅራጥስ ይጠላው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የንግግር ክህሎት የህግ አዋቂ ወይም ፖለቲከኛ ለመሆን እጅግ አስፈላጊ ስለነበር የሚሰጡት ስልጥና እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡

 አቴንስ የንግድ እና የባህል ከተማ እንደመሆኗ ብዙ ዓይነት የኑሮ አይነቶች፤ ፍልስፍናዎች እና ስርአተ አምልኮዎች ይካሄዱባት ነበር፡፡ በመሆኑም ያልተገደበ የብዝሃ ህግ ስርአት ፈጸምባት ነበር፡፡ በመሆኑም የማይቀየሩ እና የማይለወጡ የተፈጥሮ ህግጋት የአቴንስ የህግ ስርአት መሰረት ነበሩ ለማለት አይቻልም፡፡  ባህል ህግ እና ሞራል የሚመነጨው በባህል ህግ ውስጥ በመሆኑ ግሪኩም መጤውም የሚተዳደረው በዚሁ ስርአት ነበር፡፡ ለሶፊስቶች በተፈጥሮ እና በማይዳሰሰው የሃሳብ ዓለም መሃከል ልዩነት መኖሩን ያምናሉ፡፡ በመሆኑም ፍልስፍናቸውን ከባድ አንጻራዊነት ተጭኖት ነበር፡፡ 

ለእነርሱ እውነት አንጻራዊ በመሆኑ የተፈጥሮ ህግጋት የማይቀየሩ እና የማይለወጡ መሆናቸውን አይቀበሉም ነበር፡፡ የፍልስፍናቸው መሀከለኛ ሰው እንጂ የማይዳሰሱ ሃሳቦች አልነበሩም፡፡ ለሰው ልጆች ጥቅም እስካገለገለ ድረስ ሁሉም ነገር ሊለውጥ እና ሊስተካከል ይገባል፡፡ ሶፊስቶች የቅድመ ሶቅራጠስ ዓለምን የሚወክሉ በመሆኑ ሶቅራጠስ ለማይዳሰሱ ውስብስብ ሃሳቦች ቋሚ ብያኔ እና ትርጉም ለመስጠት ሲሞክር ምን ያህል ከእነርሱ አስተሳሰብ እንደራቀ መገመት እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ የተፈጥሮ ህግ ፍልስፍና እንዲህ አይነቱን ተግዳሮት ተቋቁሞ ዛሬ የደረሰበት ከፍታ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡


ስቶይኮች እና የተፈጥሮ ህግ

 ስቶይኮች የሮም ስልጣኔ ውጤቶች ናቸው፡፡  ፈጣሪ ወይም አምላክ ከተፈጥሮ ተለይቶ የሚገኝ ቢሆንም የዚህ መለኮት ፍንጣቂ በእያንዳንዱ ሰው ነፍስ ውስጥ የሚበራ እንደመሆኑ ሰዎች ሁሉ የመለኮትነት ተካፋይ መሆናቸውን ያምኑ ነበር፡፡ ይህ ከሩቅ ምስራቅ ሃይማኖቶች ጋር መጠነኛ በሆነ መንገድ የሚመሳሰል አስተሳሰብ ስቶይኮች ለሰው ልጆች የሚሰጡት ክብር ምክንያት ነው፡፡ ሰዎች ውስጥ የመለኮት ፍንጣቂ ስለሚገኝ ሰዎች መለኮት ካቋቋመው የተፈጥሮ ሕግ ጋር ለመስማማት አይቸረጉም፤ እንዲያውም ፈጣሪ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ሁሉ ውስጥ  ይኖራል የሚለው ፍልስፍና (pantheism) መነሻ እነርሱ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል ፡፡ ስቶይኮች የሰው ዘር በሙሉ እኩል ክብር አንዳለው ከማመናቸው የተነሳ ሰፊ የወንድማማቾች ማህበር ለመመስረት ያስቡ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የስቶይኮች ቤተ አስተምህሮ እንደ ኢፒክቲተስ አይነት ባሪያ እና እንደ ኦሪሊየስ ዓይነት ንጉስ የሚከተሉት ፍልሰፍና ነበር፡፡

 በመሰረቱ ምግባራዊ የሞራል ፍልስፍና ተከታዮች ቢሆኑም የሞራል ፍልስፍናቸው መሰረት የተለየ ነው፡፡ የፍልስፍናው መሰረት ሰዎች በደስታም ሆነ በመከራ ለሚመጣ ስሜት ተገዢዎች መሆን የለባቸውም፤ በመሆኑም ከስሜት የራቀ የሞራል ህይወት ሊመሩ ይገባቸዋል ሲል ሰዎችም ቢሆኑ ከገንዘብ ፣ ሃብት፣ ስልጣን እና መሰል አላፊ የሰው ልጆች ፍላጎት ርቀው የሞራል ልዕቀት ለማግኘት መጣር እንደሚገባቸው ያስተምራሉ፡፡ ይህ ስሜት አልባ ምግባራዊ የሞራል ፍልስፍናን አፓቲያ (Apathea) በሚል ይገልፁታል፡፡ 

    ባጠቃላይ ምንም እንኳ ብዙ ድጋፍ እና ትችት ቢያስተናግዱም መለኮት ሕይወት ባለው ነገር ሁሉ ውስጥ እንደሚኖር ማመናቸው ለተፈጥሮ ሕግ የሚሰጡትን ከፍተኛ ቦታ ያሳያል፡፡ የተፈጥሮን ሕግ ማክበር ማለት ሰዎች በውስጣቸው ያለውን “ንዑስ-መለኮታዊነት” መቀበላቸውን እና ማክበራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም ሰዎች ሁሉ አውቀውም ሆነ ሳያውቁት የተፈጥሮ ሕግ አካል ናቸው፡፡ 

         ከታላላቅ ስቶይኮች አንዱ የሆነው ሲሴሮ በሮም ሴኔት በሕግ ባለሙያነት እና ፈላስፋነት ረጅም ዘመን አገልግሏል፡፡ የግሪክ ፍልስፍናዎችን በጥልቀት በማጥናት ወደ ላቲን እንዲተረጎም ከማድረጉም አልፎ የላቲን መዝገበ ቃላትን አሰናድቷል፡፡ ከእርሱ በኋላ የላቲን ቋንቋ አፃፃፍ ስልትና የፍልስፍና ጦማር ዛሬም ድረስ በሕግና ፖለቲካ ዓለም ላይ ተፅዕኗቸው የጎላ ነው፡፡ ሲሴሮ የተፈጥሮ ሕግ ደጋፊ ከመሆኑም በላይ የስቶይክ ፍልስፍና እና የሕይወት ዘይቤ አራማጅ ነበር፡፡ ስቶይኮች የሰው ልጅ ሕይወትን ደስታና ሐዘን/ ስቃይ እና እርካታ ከሚያደርሱበት የስሜት መዘበራረቅ እና የመንፈስ መታወክ ነጥሎ በእርጋታና በምን ይገደኝነት ተረጋግቶ ሊያጣጥማት ይገባል ብለው እንደሚያስቡ ቀደም ብለን አይተናል ፡፡ የሲሴሮ የሕግ የፖለቲካ ፅሑፎች ከትምህርታዊ የምርምር ፅሁፍነታቸው በላይ ስነ-ፅሑፍዊ ውበታቸው አስደማሚ ነበር፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ሲሴሮ የማርክ አንቶኒን ዲክታተር የመሆን ፍላጎት በመቃወሙ አንገቱ ተቀልቶ ተገድሏል፡፡ 

     የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍናን ለመጀመሪያ ጊዜ አብራርቶ የጻፈው ሲሴሮ ሲሆን ለእርሱ ሕግ ማለት አመክንዮ ከተፈጥሯዊ ሕግ ጋር ሲጣመር የሚሰጠን ውጤት ነው፡፡ የተፈጥሮ ሕግ የሰው ልጆች ሕግጋትን ማወጅ ከመጀመራቸው እና መንግስት የሚባል ነገር ከመፈጠሩ በፊትም  እንደነበር እና ይህ ሕግም የማይለወጥ እና ዘላለማዊ እንደሆነ ያስብ ነበር፡፡ የዚህ ሕግ ባለቤት፤ ፈጻሚና ተርጓሚ የሆነ ልዕለሰብዓዊ አካል እንዳለና ይህም አካል ፈጣሪ ወይም አምላክ በሚል የሚታወቅ መሆኑን ጽፏል፡፡ ሲሴሮ ከተፈጥሯዊ ሕግ እኩል ሁሉን አቀፍ እና ገዢ መሆን እንዳለበት የሚገልጸው ቀና አመክንዮን (right reason) ነው፡፡ ትክክለኛና ቀና አመክንዮ ከእውነተኛውና ከማይለወጠው የተፈጥሮ ህግ ጋር ሲዋሃድ ፍትሕ እና ርትዕ ለሰው ልጆች ሁሉ ይደርሳል፡፡ በተጨማሪም መንግስት የግል ሃብትን መጠበቅ እንዳለበት እና መንግስት ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንዱ መሆኑንም ጽፏል፡፡ 



የአምላክ ከተማ  ቅዱስ ኦግስቲን

       ኦግስቲን የተወለደው በሰሜን አፍሪካዋ የዛሬይቱ አልጄሪያ ከተማ ሲሆን በልጅነቱ የክርስትና እምነት ተከታይ የነበረችው እናቱ ከፍተኛ የእምነት እና የመልካም ባህሪ ተጽእኖ ያሳደረችበት መሆኑን ሁሌም ይናገር ነበር፡፡ ከሰሜን አፍሪካዊቷ ግዛት ወደ ሮም ፤ካርቴጅ፤ ሚላን መሰል ከተሞች ለትምህርት የተላከው ኦግስቲን ፤ወጣትነቱ  ከሮም የድሎት እና ስጋዊ እርካታዎች ጋር ተደምሮ መንገዱን አስተውት እንደነበር በኋላ ላይ  ኑዛዜ በተባለው ድርሳኑ አመልክቷል፡፡ 

የአምላክ ከተማ የተሰኘው ድርሳኑ በወራሪዎች የፈረሰችው የሮም ከተማ ሁኔታ የዜጎቹን ስነ ልቦና ክፉኛ የጎዳ በመሆኑ እንደማጽናኛ የተደረሰ ነው፡፡ የሮም ነዋሪዎች  ሮም የወደቀችው የጥንቶቹን አማልክት በመተው ክርስትናን በመከተሏ ከአማልክቱ ቁጣ የተነሳ መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር፡፡ እርሱ ግን  በዚህ ድርሳን  የአምላክ ከተማ (City of God) እና ምድራዊዋ ከተማ በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ እንደሆኑና የማታ የማታ የጽድቅ እና ፍትህ ምልክት የሆነችው የአምላክ ከተማ እንደምታሸንፍ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡

በዚሁ ድርሳን  የአምላክ ፍቃድ ዘላለማዊ ህጋግትን ለማወቅ እንደሚጠቅም እና ሰው ስራሽ ህግጋት ሁሉ ዘላለማዊ ከሆነው የአምላክ ፍቃድ ጋር  ሊሰምሩ የተገባ መሆኑን አመልክቷል፡፡በመሆኑም ኢፍትሃዊ ህግ ማለት ዘላለማዊ ከሆነው ከአምላክ ፍቃድ ጋር የሚጣረስ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ስለዚህም ከተፈጥሮ ህግጋት ጋር የሚጋጭ ህግ ኢፍትሃዊ ህግ ነው፡፡ ኢፍትሃዊ ህግ ደግሞ ህግ አይደለም ፤ ስለሆነም ሰው ሰራሽ በሆነችው ከተማ የሚኖሩ ዜጎች እነዚህን ኢፍትሃዊ ህግጋት ሊቋቋሙ ይገባል፤ ምክንያቱም ቅዱስ ኦግስቲን እያሰብን እንመን ፤ እያመንን እናስብ በሚለው አቋሙ ይታወቃል፡፡ በርግጥ ኦግስቲን በስነ መለኮት፤ ትምህርት ፤ ሳይንስ፤ ሞራል  እና መሰል ጉዳዮች ላይ በሰፊው ተመራምሯል፡፡ እንዲያውም  ስለ ድህነት ፤ ጸጋ እና ቀዳሚ ሃጢያት ላይ ያቀረባቸው የስነ መለኮት ሃሳቦች ዛሬም ደረስ በካቶሊኮቹም ሆነ በፕሮቴስታንቶቹ እኩል የሚጠቀስ መሰረታዊ ስራ ነው፡፡


መነኩሴው ፈላስፋ- ቅዱስ ቶማስ አኩይናስ

       ከልጅነት ዘመኑ ጀምሮ የዶሚኒካን የምንኩስና ማህበር ባሳደረበት ልዩ ተፅዕኖ የካቶሊክ ሃይማኖት መነኩሴ ለመሆን ባሳየው ተነሳሽነት ቤተሰቦቹ ሃሳቡን ለማስተው እንዲታሰር አድርገውት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከብዙ ጥረት በኋላ ተሳክቶለት በምንኩስና ትምህርቱ ቢቀጥልም ትምህርቱ ብዙም ሊዘልቀው ስላልቻለ  ጓደኞቹ “ደደቡ በሬ” እያሉ ይሳለቁበት ነበር፡፡ እየቆየ ሲሄድ ባሳየው ልዩ የምርምር እና ጥናት ብቃት የግሪክ ፍልስፍናን ከሃይማኖት አስተምህሮ ጋር በማዋሃድ የሃይማኖት እውቀትና መገለጥ ከአመክንዮ የተፃረረ እንዳልሆነ እንዲያውም አጋዥ መሆኑን ለማሳየት ብዙና ታላላቅ ድርሳኖችን አሰናድቷል፡፡ አኩይናስ በዕውቀተ ፍልስፍና ፤ በዲበአካላዊነት፤ በስነ-መለኮት፤ በስልተ-ምርት፤ በፖለቲዊ ርዕዮተ ዓለም እና በሕግና አስተዳደር ዙሪያ ብዙ ጽሁፎችን አበርክቷል፡፡ ከሞቱ በኋላ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አብዛኞቹን ድርሳናቱን ለመማሪያነትና ለስርዓተ አምልኮ መገልገያነት እንዲውሉ ስታደርግ እርሱ ደግሞ “የቅዱስነት” ማዕረግን ተጎናፅፏል፡፡ 

     አኩይናስ ከግሪክ ፈላስፎች መሃከል ለአሪስቶትል ከፍተኛ አድናቆትና ክብር ከማዳበሩ የተነሳ “ፈላስፋው” ብሎ የሚጠራው ብቸኛ የግሪክ አሳቢ አሪስቶትልን ነበር፡፡ የካቶሊክ መነኩሴ እንደመሆኑ ሕግ ከፈጣሪ የተሰጠ እና በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኝ ስርዓት መሆኑን ማመኑ ብዙ ሊደንቀን አይገባም ይሁን እንጂ ሕግ የሚባለውን ሀሳብ ራሱ ለአራት ዋና ዋና ርዕስ ክፍሎች በማብራራቱ ሃሳቡን በሚገባ ልናጤንለት ይገባል፡፡ 

     እነዚህም ዘላለማዊ ሕግ፤ የሰዎች ሕግ፤ መለኮታዊ ሕግ እና የተፈጥሮ ሕግ የሚባሉት ንዑስ ክፍሎች ናቸው፡፡ ዘላለማዊ ሕግ  ዘላለማዊ እንደመሆናቸው በዘላለም ውስጥ ያሉ የማይቀየ እና የማይለወጡ እንደሆኑ አድርጎ ፈጣሪ የደነገጋቸው ሕግጋት ናቸው፡፡ እነዚህ ዘላለማዊ እና የማይቀየሩ ሕግጋት ለሰው እና ለተፈጥሮ በሚችሉት እና በሚረዱት መልኩ ይገለጻሉ፡፡

     ዘላለማዊ እና ፍጹም የሆነው ሕግ ለሰዎች የአዕምሮ ብቃት እንዲመጥን ተደርጎ ሲተላለፍ እና ሰዎችም ይህንኑ ሲረዱት የተፈጥሮ ሕግ ይባላል፡፡ የተፈጥሮ ሕግ ማለት ሰዎች በተረዱት እና በገባቸው መጠን በዘላለማዊ ሕግ ውስጥ በሚያደርጉት ተሳትፎ የሚወሰን ስርዓት ነው፡፡ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከተሰጠው ባህሪያት እና ችሎታዎች አንዱ አመክንዮ  እንደመሆኑ ዘላለማዊ እና ጥልቅ የሆነ ነገሮችን በምክንያታዊነት መርምሮ ራሱን ወደ ፍጹማዊነት ሊያስጠጋ እንደሚገባ ይታመናል ይህ ሰብዓዊ እና ምክንያታዊ የሆነ ፍጽምና የተፈጥሮ ህግ ይባላል፡፡ 

    በመሆኑም ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው በአንድነት የሚረዱት እና የሚያውቁት የራሳቸውንም ሆነ የሌላ ሕይወት ያለው ፍጥረትን ህላዌ ሊያዳብሩ የሚችሉበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ሕግ ምክንያታዊ ለሆነ ሰው በተፈጥሮ የተገለጠ ነው፡፡ መለኮታዊ ሕግ ግን በምክንያት ለሚመሩ ሰዎች በተፈጥሮ የተገለጠ ባለመሆኑ የሚታወቅ አይደለም፡፡  በመሆኑም መለኮታዊ ሕግን ለመረዳት ሰዎች ከምክንያታዊነት ባሻገር መለኮታዊ ድጋፍ እና ጣልቃገብነት ያስፈልጋቸዋል፡ መለኮታዊው ሕግ በልዩ መለኮታዊ መገለጥ ዘላለማዊ የሆነውን ህግ የሚያስረዳ እና የሚያስፈጽም ሲሆን ዋንኛ ግቡም የሰው ልጆች ዘላለማዊ ግባቸው የሆነውን መለኮታዊ ሕይወት እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው፡፡ መለኮታዊ ሕግ ምድራዊ የሆነውን ሕይወታችንን ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ የሆነውን ሕይወት የሚገዛና ለዚሁ የሚያዘጋጀን ነው፡፡ የሰዎች ሕግ ወይም ህገ-ሰብ የምንለው ሰዎች ማህበራዊ ሕይወታቸውን ለማቃናት የተፈጥሮ ሕግን በአዋጆች እና መመሪያዎች ውስጥ አካተው ሲያጸድቁ የምናገኘው ነው፡፡ በመሆኑም የሰዎች ሕግ ከተፈጥሮ ሕግ ጋር መስማማት ያለበት ብቻ ሳይሆን የሞራል መስፈርት ሆኖ ሊያገለግል ይገባል፡፡ የሰው ልጆች ሕግጋት ከቦታ ቦታ ሊለያዩ እና ሊሰዋወጡ ይችላሉ፡፡ 

     በመሃከለኛው ዘመን በነበረው ምሁራዊ ባህል መሰረት አኩይናስ አስቀድሞ ታዋቂ ሐቲቶችን ያስቀምጥና የራሱን ተቃውሞ እንደመልስ ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ ሕግ ሰዎችን መልካም ያደርጋልን; ብሎ ከጠየቀ በኋላ በአሉታዊው መልስ ይሰጣል፡፡ የሰዎች መልካምነት የሚገኘው በሕግ ሳይሆን አስቀድሞም ቢሆን በሰዎች ውስጥ የተቀመጠ መልካምነት በመኖሩ ሕግ ያንን ተፈጥሯዊ መልካምነት ታሳቢ በማድረግ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ያትታል፡ ይሁን እንጂ ሰዎች በውስጣቸው መልካምነት ቢኖርም ይህንኑ ላለማድረግ አልፎ አልፎ ቢያፈነገግጡ እንኳ ሕጉ በቅጣት ወደ መልካምነታቸው ሊመልሳቸው እና ሊያለማምዳቸው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ እንደሚታወቀው አኩይናስ የአሪስቶትል ፍልስፍና አድናቂ እና ተከታይ እንደመሆኑ ልክ በሶቅራጥስ እና አፍላጦን መሀከል የነበረው የሃሳብ መወራረስ በእነርሱም ዘንድ ይታያል፡፡ 

    አሪስቶትል የሰው ልጅ “ፖለቲካዊ ፍጡር” እንደሆነ እና በዚህ ባህሪው የተነሳ በማህበር ለመኖር እንደተገደደ እና ማህበሩ በጥቅል የሚያነሳው እና የሚያሳየው ባህሪ በማህበሩ አባላት ላይ እንደሚንጸባርቅ ያስባል፡፡ ይህም ማለት ግለሰቡ የሕይወት ትርጉም እና ዓላማውን የሚያገኘው በቀጥታ ከማህሩ ዓላማ ነው፡፡ በመሆኑም ሕግ የማህበሩን ጥቅል ደህንነት (common good) ማስጠበቅ እንዳለበት እና ግለሰቡም በተመሳሳይ ይህንኑ እንደሚከተል ተናግሯል፡፡ አኪይናስ ይህን ሃሳብ የሚስማማበት ሲሆን የአሪስቶትልን ፍልስፍና በሙሉ በማጥናት “ክርስቲያናዊ” መልክ እና ጣእም እንዲረው ከማድረግ ውጪ ብዙም እንዳልጨመረበት ይስማማሉ፡፡ ይህ ጥንታዊ የግሪክ ፍልስፍናን ከክርስትና ጋር እያዋሃዱ የማጥናት ስልት በወቅቱ scholasticism በመባል ሲታወቅ ብዙ ድጋፍ እና ነቀፋ ነበረው፡፡ አኩዮናስም ቢሆን እንዴት የአንድን አረማዊ ፈላስፋ ፍልስፍና ታስፋፋለህ በሚል ብዙ ትችት ደርሶበት ነበር፡፡ 



ማህበረ-መንግስታት - ሁጎ ግሮቲየስ

ምንም እንኳ ከፍተኛ እውቀት ያተረፈው የአለም አቀፍ ህግን በስፋት በማጥናት እና በማስተዋወቅ ቢሆንም ከዚሁ ጋር በተያያዙ የተፈጥሮ ህግ ላይ በመመራመሩ ይታወቃል፡፡ ሁጎ ግሮቲየስ ማርቲን ሉተር ባስነሳው የተሃድሶ ቀውስ በምትናጠው አውሮፓ ውስጥ እየኖረም ቢሆን የተለያዩ የክርስትና ሀይማኖት ዘርፎችን ለማስታረቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ፍትሃዊ ጦርነት (Just war) በዓለም አቀፍ ህግጋት እና ልማድ አንጻር በምን መንገድ መተርጎም አለበት?ለሚለው ጥያቄ በሰጠው መልስ የተፈጥሮ ሕግን አስተራቂ ፍልስፍና እንደ ማስረጃነት አቅርቧል፡፡ የዚህ አሰተምህሮው ምንጮች ሲሴሮ እና የስቶይክ ፍልስፍና መሆናቸውን ከጽሁፎቹ መረዳት እንችላለን፡፡

 የፍትሐዊ ጦርነት ምክንያቶች የተፈጥሮ ሕግ እና አለም አቀፍ የማህበረ-መንግስት ልማድ ናቸው፡፡ በጦርነት ሕግ መሰረትማንኛውም ሀገር የራሱን ልዑላዊነት የማስጠበቅ ተፈጥሯዊ መብት ስላለው ራሱን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት ለመከላከል የሚገባበት ጦርነት ፍትሐዊ ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ መንግስት ራሱን ለመከላከል፤ የተዘረፈበትን ሃብት ለመስመለስ እና በደረሰበት ጥቃት ልክ ተመጣጣኝ የቅጣት እርምጃ በመውሰድ የሚያስችል ተፈጥሯዊ መብቶች በተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሃገር የውስጥ ህግጋትም የሚገኙ እንደመሆናቸው በማህበረ-መንስታት ጸድቀው አለም አቀፋዊ ሕግጋት መሆን ይገባቸዋል ሲል ጽፏል፡፡ ሁጎ ግሮቲየስን የአለም አቀፍ ሕግ አባት እንደሆነ አድርገው የሚያቀርቡ ሰዎች ሉዓላዊና ሰላማዊ ሀገራትን ማህበረ- መንግስታት በሰላምም ሆነ በጦርነት ወቅት ሊያስማማቸው የሚችል አንድ የተጻፈ ወይም የልማድ ሕግ መኖሩ አስፈላጊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ መጻፉን ያነሳሉ፡፡ የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍና አብዛኛውን ከሰብአዊ መብቶች አፈጣጠር ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ከዓለም አቀፍ የጦርነት ሀግጋት ጋር አያይዞ ሀሳብ መፍጠር አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ 

መሰረታዊ እሴቶች -ጆን ፊኒስ

ጆን ፊኒስ የሕግ ፍልስፍና ተመራማሪ እና ለሀገሩ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አማካሪ ፤ ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያነትን ደርቦ የሰራ ሲሆን በአሁን ወቅት በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ፊኒስ ዘመናዊ የተፈጥሮ ሕግ ተከታይ ቢሆንም ጥንታዊ የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍና አሻራዎች በስራዎቹ ውስጥ ማየት ይቻላል፡፡ ፍልስፍናው ሰባት ተፈጥሯዊ የሆኑ መሰረታዊ መልካም እሴቶች እንዳሉ ይጠቅሳል፡፡ እነዚህም ህይወት ፤እውቀት፤ መዝናኛ፤የስነ-ውበት አድናቆት፤ ወዳጅነትንና ጓደኝት፤ተግባራዊ አመክንዮ እና ሃይማኖት ወይም እምነት ናቸው፡፡

 ሕይወት ቀዳሚው የተፈጥሮ ስጦታ ሲሆን የመኖር እና የመስራት ጉልበት ምንጭ ነው፡፡ ሌላኛው እውቀት ብቻ ሳይሆን የማወቅ ጉጉትንም ይጨምራል ይህን ስንል እውቀትን ለማወቅ እና እውነትን ለማግኘት ጥማት ስንል ብቻ የምንፈልገው መሆን አለበት፡፡ መዝናናት ከእውቀት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በራሱ የሚቆም እሴት ሲሆን እውነተኛ ደስታን እና መዝናናት የሚያመጣ ሲሆን ለመዝናት ስንል ብቻ ልንተገብረው ይገባል፡፡ ውበትን ማድነቅም እንዲሁ ምንም አይነት ድርጊት ሳንፈጽም ሆነ ራሱ የስነ-ውበት እሴቶችን በመፍጠርም ጭምር የምንተገብረው ነው፡፡ ማህበራዊ ግንኙነት የሚፈጠረውና እውነተኛ ጓደኝነትን እና ወዳጅነትን በመፍጠር ሲሆን ከእነዚህ ጉድኝቶች ውስጥ ፈልቆ የሚገኘው ስሜትም የእውነተኛ ደስታ ምክንያት ነው፡፡ ተግባራዊ አመክንዮ ሰዎች እና ማህበራት የግልና የጋራ እጣ ፈንታቸውን የሚወስኑበት መሳሪያ ሲሆን የመጨረሻው መልካም እሴት ሃይማኖት ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት መልካም እሴቶች በሙሉ ስርዓት እና መልክ የሚይዙበት ማጠቃለያና መደምደሚያ እሴት ነው፡፡ እነዚህ እሴቶች በተፈጥሮ የተገኙ ሲሆኑ በምድር ላይ የሰው ልጅ ህይወት ትርጉም እና ዓላማ የሚያገኝባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ እነዚህ መሰረታዊ የመልካምነት እሴቶች (basic goods) የማይበላለጡ እና የማይወዳደሩ በራሳቸው የሚቆሙ ናቸው፡፡ 



ምዕራፍ ሶስት

የሕገ-ሰብ ፍልስፍና

     የሰው ልጅ ከቅድመ -መንግስት ታሪክ ተላቅቆ ራሱ በመረጣቸውም ሆነ ባልመረጣቸው መንግስታት መመራት ሲጀምር የእለት ተእለት ህይወቱን የሚገዙ ህግጋት ማስፈለጋቸው አልቀረም፡፡ ከዚህም በላይ መንግስታት እና መሪዎች መንግስታዊ መዋቅሮችን የሚያስተዳድሩበት ሕግ አበጅተው ለረዥም ዘመናት እየተገለገሉበት ኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሕጎች እንዴት ይፈጠራሉ? ማን ለምን እና እንዴት ያውጃቸዋል በሚሉት ነጥቦች ላይ ዛሬም  ድረስ መግባባት ላይ ባለመድረሳችን ብዙ ሰዎች የተለያዩ ፍልስፍናዎችን እና አስተምህሮችን ዛሬም ድረስ ይሠነዝራሉ፡፡ 

     የሕገ ሰብ ፍልስፍና (Positive Legal Theory) ከእነዚህ ፍልስፍናዎች መሃል አንዱ ሲሆን በአጭሩ የሰው-ሕግ የሚል ትርጉም አለው፡፡ የእዚህ ፍልስፍና አቀንቃኞች ሕግ በመሰረቱ ሰው - ሰራሽ ግኝት እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ከዚያ አልፈው ሕግ ሰው ሰራሽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሰው ስራሽነቱ የመቀጠሉንም አስፈላጊነት በአጽንኦት ያረጋግጣሉ፡፡ ሕግ ሃይማኖታዊ፤መንፈሳዊ፤ ትውፊታዊ፤ ዲበአካላዊ እና መሰል ተጨባጭነት ከሌላቸው መነሻዎች እና ትርክቶች ፍጹም በሆነ መንገድ የጸዳና የተለየ መሆን አለበት፤ በመሆኑም ሕግ አውጪዎች አስፈጻሚዎች እና ተርጓሚዎች ይህን እውነታ አውቀው ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ 

     ሕግ ማለት የሰው ልጆች ለአንድ የተለየ ዓላማ ብለው የሚፈጥሩት ስርዓት እንጂ በተፈጥሮ የተገኘ ወይም ከፈጣሪ የተሰጠ ትእዛዝ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም የሕግ ስርዓት በወቅቱና በጊዜው በስርዓቱ ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲያገለግልና እንዲጠቅም ሊታወጅ ፤ ሊሻሻል እና ሊሻር ይገባል፡፡ ይህ ፍልስፍናም ቢሆን በውስጡ ልዩ ልዩ ንዑስ ክፍሎች እና ተቃራኒ ሃሳቦችን እና ፈላስፎችን አፍርቷል፡፡

የሕገ-ሰብ ፍልስፍና መሰረቱን ያደረገው በተለምዶ የቪየና ክበብ (viena circle) የሚባለው የፈላስፎችና ሳይንቲስቶች ስብስብ ባስቀመጠው አቅጣጫ ነው፡፡ በ19ኛው ክ/ዘመን የነበሩ የተፈጥሮና የማህበረሰባዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች ፍልስፍና እንደ ጥናት ዘርፍ እየሄደበት ያለውን አቅጣጫ እና አዝጋሚነት ለመገምገም ተነስተዋል፡፡ በዚህም መሰረት ፍልስፍና ከሌሎች የእውቀት ዘርፎች ሁሉ ቀድሞ ተነስቶ እያደር ግን የእድገት ደረጃው እየቀነሰ ሄዶ በመቆሙ ምክንያት ይህን የእድገት መቀጨጭ ለመመርመር የተሰበሰቡት ምሁራን በየቅዳሜው ጠዋት ተሰብስበው በሚያደርጉት የሃሳብ ፍጭት የተነሳ ለፈልስፋና አዲስ አካሄድ አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት ፍልስፍና ከዚህ ቀድሞ ራሱን ያለአግባብ ሲያስጨንቅበት ከነበረው የዲበአካላዊነት (metaphysical)፤ የኑባሬአዊነት (existentialism): ሞራላዊ ፍልስፍና ጥያቄዎች እና መልስ የፍልስፍና ተግባራት በሙሉ ተቆጥቦ ዋንኛ ስራው አመክንዮ  እና ቋንቋን ካላስፈላጊ ሃሳቦች ማጥራት መሆን እንዳለበት አስተምረዋል፡፡ ምክንያቱም በቋንቋችን ውስጥ የማይጨበጡ እና የማይዳሰሱ ለሰው ልጆች የእለት ተእለት ሕይወት ምንም የማይፈይዱ ሀሳባዊ ኮተቶችን ካስወገድን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መነጋገር እንችላለን፡ የዚህ ፍልስፍና አቀንቃኞች በኋላ በእንግሊዝና አሜሪካ ከተፈጠረው analytic philosophy ዘርፍ ጀማሪዎች በመሆን አገልግለዋል፡፡ ሁሉም የዚህን ክበብ ዋነኛ መርህ በመውሰድ በየዘርፉ ተግብሮታል፡፡ በሕግ ፍልስፍናም የሆነው ይኸው ሲሆን የሕግ አስተምህሮ በእጅጉ ዲበአካላዊ መንፈሳዊ እና ሞራላዊ የሆኑ የቋንቋ ጭነቶች የተከመሩበት እንደመሆኑ የሕግ ጥናትን እና ልምምድን ከእነዚህ ሸክም የሆኑ ሀሳቦች ለማጥራት በሚል የሕገ-ሰብ ፍልስፍና ሊመሰረት ችሏል፡፡ 

የሂዩም መቀስ - ዴቪድ ሂዩም

ልማዳዊነት (Empircism) መሰረታዊ የእውቀት ፍልስፍና ነው፡፡ የሰው ልጆች ተወልደው ወደዚህ ምድር ከመጡ ወዲያ በሚያዳብሩት ተግባር እና ተሞክሮ አማካኝነት እውቀታቸውን ያከማቻሉ እንጂ አስቀድሞም ቢሆን ሰው በመሆናቸው ብቻ በአእምሯቸው የተጻፉ የቅድመ እውቀት መሰረታውያን እንደሌሉ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም የዚህ ፍልስፍና አቀንቃኞች ሰዎች ወደ እዚህ ምድር ሲመጡ ታቡላ ራሳ ወይም ነጭ ወረቀት መሆናቸውን ያወሳሉ፡፡

የዚህ ፍልስፍና ዋንኛ አቀንቃኝ የነበረው ዴቪድ ሂዩም እስከዛሬ ድረስ የሚታወስበትን የውጤት እና ምክንያት ግንኙነትን በመጠቀም ከላይ የተገለጸውን የልማዳዊነት ፍልስፍና ለማብራራት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ በምድር ላይ በተፈጥሮ በምናያቸው ድርጊቶች መሃከል ያለውን የምክንያት እና ውጤት ግንኙነት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማስረዳት ወይም ማረጋገጥ አንችልም ይልና ለምሳሌ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሳ ጸሃይ በምስራቅ እንደምትወጣ ወይም መሽቶ እንደሚነጋ ልናውቅ የቻልነው ይህ የድርጊት ቅደም ተከተል ለረዥም ዘመን ሳይዛነፍ በመቀጠሉ እንጂ በርግጥም  በመምሸት እና በመንጋት መሀከል ያለውን የምክንያት እና ውጤት ግንኙነት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ስላረጋገጥን አይደለም በማለት ይከራከራል፡፡ 

    ለሂዩም ሰዎች ያለማቋረጥ በተደጋጋሚ የሚሰሩት ስህተት የሆነውን ነገር አይተው መሆን ስለሚገባው ነገር ወይም ስለሚሆነው ነገር የማውራታቸው አባዜ ነው፡፡ ለእርሱ  በሆነው (what is) እና ሊሆን በሚገባው( what ought to be) መሃል ምንም አይነት ሳይንሳዊ ግንኙነት ከሌለ ይህንን  ጉድኝት ልንበጥሰው ይገባል በማለት ይከራከራል፡፡ ይህም ሳይንሳዊ እና አመክንዩአዊ አካሄድ የሂዩም መቀስ በመባል ይታወቃል፡፡

ይህ የሂዩም መቀስ የህገ ሰብ ፍልስፍና በሃያኛው ክፍለ ዘመን በሚያንሰራራበት ወቅት እጅግ ከፍተኛ በሆነ መንገድ አገልግሏል፡፡ ምክንያቱም የህገ ሰብ ፍልስፍና አቀንቃኞች  ህግን ከሞራል ፤ ከመንፈሳዊ እና ከዲበአካላዊ ግሳንግሶች እናጸዳለን ብለው ሲንቀሳቀሱ የተጠቀሙት ይህንኑ የዴቪድ ሂዩም መቀስን ነው፡፡


የሉዓላዊው አካል ትዕዛዝ -ጆን ኦስቲን

ዕውቁ የሕገሰብ ፍልስፍና አቀንቃኝ ጆን ኦስቲን በሕይወት እያለ በሕመም ሲሰቃይ እና በጠበቃነት ኑሮውን ለመግፋት ሲውተረተር ኖሮ ብዙም ሳይሳካለት አልፏል፡፡ በሚገርም ሁኔታ የጄርሚ ቤንታም ወዳጅ በመሆኑ በእርሱ በኩል በያኔው የሎንዶን ዩኒቨርሲቲ የማታ መርሃግብር በአስተማሪነት ተቀጥሮ የሕግ ፈልስፍና ለማስተማር ቢሞክርም ብዙም ተደማጭ አልነበረም፡፡ ደራሲ እና ተርጓሚ የነበረችው ሚስቱ በምታገኘው አነስተኛ ገቢ ቀሪዎቹን የሕይወቱን ዘመናት ለመግፋት ተገዷል፡፡ ከእርሱ ህልፈት በኋላ ሚስቱ ሳራ ኦስቲ በድጋሚ መጽሀፍቱን ማሳተም ስትጀምር ሰራው ተሰሚነት ሊያገኝ ችሏል፡፡

ጆን ኦስቲን የሕገሰብ ፍልስፍና እንዲታወቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት በአግባቡ እንዲደራጅ አደርጎታል፡፡ ለኦስቲን ሕግ ሰው ሰራሽ ግኝት ሲሆን በህግና ሞራል መሃከል ምንም አይነት ግንኙነት የለም፡፡ እናም ባለቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ ባሳተመችው ድርሳን “የትእዛዝ መርህ” በመባል እስከዛሬ የሚታወቅለትን መርህ መስርቷል፡፡ በዚህም መሰረት ሕግን ከሐይማኖት እና ሞራል እንዲሁም በወቅቱ በሰፊው ይራመድ ከነበረው “የተፈጥሮ ሕግ” ፍልስፍና በመነጠል ብቻውን ለማጥናት ጥረት አድርጓል፡፡ እንደ ኦስቲን አስተሳሰብ “ሕግ የአንድ ሉዓላዊ አካል ትዕዛዝ ነው” ይህ ትእዛዝ ደግሞ በቅጣት መደገፍ ይኖርበታል፡፡ የጂርሚ ቤንተም የቅርብ ወዳጅ እና ጎረቤት ስለነበር የጠቀሜታውያን ፍልስፍና ተጽእኖ ሳያሳድርበት አልቀረም፡፡ ለእርሱ ህግ ማለት ከአንድ ሉአላዊ አካል ለሌላ በስልጣን የሚያንስ አካል ከቅጣት ማስፈራሪያ ጋር ተደግፎ የተሰጠ ትእዛዝ ነው፡፡ 

ይህ ማለት ኦስቲን የፈጣሪ ህግን ይቃወማል ማለት አይደለም፡፡ የፈጣሪ ሕግ ከሰው ሕግ በላይ በመሆኑ መለኮታዊ ጉዳዮችን ብቻ እንደሚያስተዳድር ከሰው ሰራሽ ሕግጋት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ይገልጻል፡፡ ሕግን ለበታች አካላትና ህዝቦች በትእዛዝ መልክ የሚያስተላልፈው ይህ  “ሉዓላዊ አካል” ግን በሕግ ሊገዛ አይችልም፡፡ ሉዓላዊው አካል የሚሰጠው ትእዛዝ ከማህበረሰባዊ ሞራል ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፤ ሉዓላዊው አካል ማህበረሰባዊ ሞራልን አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜ ሊያማክር እና ሊጠቀም ይችላል እንጂ ሊገደድባቸው አይችልም፡፡ ኦስቲን ከቤንታም ፍልስፍና በመውረስም ህግጋት ለሰፊው ህዝብ መጠነ ሰፊ ደስታና ጥቅም የሚያስገች መሆን እንዳለባቸው ያስረግጣል፡፡ 

     በተጨማሪም የህግ ፍልስፍና ስራ መሆን ያለበት ሕግ ራሱን የቻለ እና በራሱ አመክንዮ የሚመራ ደረቅ ሳይንስ አድርጎ መቅረጽ ነው፡፡ ሕግ መረቀቅ እና ማጠናት ያለበት “መሆን ስላለበት” ጉዳይ ሳይሆን “ስለሆነው” ማህበራዊ ሁኔታ ነው፡፡ ህግ መሆን አለባቸው ወይም መደረግ ይገባቸዋል ከሚላቸው ሃሳባዊ ሞራላዊ የማህበረሰብ ልማዶች መጨነቅ የለበትም፡፡ ሕግ ማለት ከአንድ ሉዓላዊ አካል የመጣን ትእዛዝ ስለመፈጸም እና ስለ ማስፈጸም በማሰብ  ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ሲባል የሚጠና ነው፡፡ ማህበራዊ ሞራል  “መሆን ስለሚገባው” ሲያስብ ሕግ ግን “ስለሆነው” ነገር ያስባል፡፡ የማህበረሰባዊ ሞራል አና ህግ ድንበር ፈጽሞ ሊገናኝ አይገባም በሚል በኦስቲን የተራመደው ሃሰብ የጠቀሜታውያን የሞራል ፍልስፍና መሰረት አለው፡፡ ሕግጋት በትእዛዝ መልክ ከአንድ ሉዓላዊ አካል ሲወጡ የብዙሃን መብት እና የእርካታ ደረጃ ያስጠብቃሉ ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ከዚህ ተርፎ ባለ የማይመስጥ እና መሰረት አልባ የዲበአካላዊ እና ሞራላዊ ጥያቄዎች ውስጥ ገብቶ መፈትፈት ለህግ ስርዓቱም ሆነ ለሕግ ባለሙያዎች እርባናቢስ የሆነ ልፋትን የሚያስከትል ነው፡፡ 

     ጄርሚ ቤንተም ራሱም ቢሆን የጠቀሜታውያን ሞራል ፍልስፍና መስራች እንደሆነ ቢነገርም በስነ-ህግ ጥናት እና ምርምርም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ከማሳረፉ የተነሳ ለቀዳሚው የሕገ-ሰብ ፍልስፍና አቀንቃኝ ጆን ኦስቲን መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በኦስቲን ስራዎች ላይ ተጽእኖ ካሳደሩ የቤንተም ሃሳቦች መሃከል ጥቂቆቹን መዳሰስ ይኖርብናል፡፡ ቤንታም የእንግሊዝ ዳኛ ሰራሽ ሕግጋት ወይም በኩር ውሳኔዎች (precedents)የእንግሊዝ የፍትህ ስርዓት ያልተረጋገጠ፤ ወጥነት የሌለውና የማይገመት እንዲሆን ስላደረገው መሰረታዊ የሆነ ለውጥ እንደሚያስፈልገው አመልክቷል፤፤ በመሰረቱ ቤንተም በፈጣሪ መኖር እና በተፈጥሮ ሕግ የማያምን በመሆኑ እንዲፈጠር የሚፈልገው ሰርዓት ሰው ሰራሽ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ በሆኑም ቤንተም በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ሲታገል የነበረው ህግጋት በዓይነት ተከፋፍለው ወጥነት እና አጠቃለይነት ባለው የሕግ ድርሳን (code) ተሰንደው መቀመጥ እንዳለባቸው ለማስረዳት ነው፡፡ በዳኛ ሰራሽ የሕግ ስርዓት ውስጥ እየኖሩ ፍርድ ቤቶች ሊመሩ የሚገባው አስቀድሞ በታወቀ እና በፖርላማ በጸደቀ የህግ ስርዓት እና የህግ ድርሳን (code) መሆን እንዳለበት እየጻፉ እና እየተከራከሩ መኖር የቤንተምን ህይወት እጅግ ከባድ አድርጎት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሃሳቡ ከሀገር እንግሊዝ አልፎ እስከ ሩሲያ ድረስ እንዲታወቅለት ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ነገስታት ጋር ሲጻጻፍ ኖሯል፡፡ 

     ቤንተም ዳኛ ሰራሽ ህግጋትን የውሻ ሕግ (dog Law) እስከማለት ድረስ ቢሄድም የእንግሊዝ ህግጋትን በተጠቃለለ የሕግ ድርሳን (code) የማስቀመጡና የዚህም ድርሳን የፍልስፍና መሰረቱ ጥብቅ የሆነ የጠቀሜታውያን ፍልስፍና እንዲሁም ማስገደድ በብዙዎች ዘንድ የከፋ ትችን እንዲሰነዘርበት አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ codification የሚለውን ቃል በማግኘቱ እና በማስፋፋቱ ዛሬም ድረስ የላቀ እውቅና ከማግኘትም አልፎ የእንግሊዝ ሀገር የሕግ ስርዓት ራሱ የተጠቀለሉ የሕግ ድርሳናትን  በከፊልም ቢሆን እየተቀበላቸው ይገኛል፡፡ 

የህግ ፅንሰ ሃሳብ - ሃርት

“የህግ ጽንሰ ሃሳብ” / The concept of law “በሚል የሚታወቀው ድርሳን በህገ ሰብ የስነ ህግ ፍልስፍና አቀንቃኞች ዘንድ እንደ መዓዘን ድንጋይ የሚታይ ነው፡፡ እንዲያውም ከእነ ጆን ኦስቲን በኋላ በነበረው ዘመን የነበረውን የእንግሊዝን የሕግ ፍልስፍና አነቃቅቶታል፡፡ የዚህ ድርሳን ፀሐፊ የሆነው ምሁር ኤች ኤልኤ ሃርት በእንግሊዝ መንግስት ውስጥ በተለያዩ የሐላፊነት ደረጃዎች የሰራ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የእንግሊዝ የስለላ ድርጅትን በመቀላቀል ለሀገሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለረጅም ዘመን አብራው የኖረችው ሚስቱ ግን በድብቅ የእንግሊዝ ኮሚኒስት ፓርቲ አባል ነበረች፡፡ ከአይሁድ ቤተሰቦች የተወሰደው ሃርት በሀገረ እንግሊዝ ለጥቂት ጊዜ በጥብቅና ሙያ ከሰራ በኋላ ወደ ማስተማር ዘርፍ ገብቶ የሕግ ፍልስፍናን ለረዢም ጊዜ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ አስተምሯል፡፡ 

     በዚህ ንዑስ ርዕስ ለማየት የምንሞክረው “የህግ ፅንሰ ሃሳብ” በሚል የተሰየመው ድርሳን ውስጥ የተገለጡትን ሃሳቦች ነው፡፡ በመሰረቱ ሃርት ቀንደኛ የህገሰብ ፍልስፍና አራማጅ እንደመሆኑ ይህ ድርሳኑም ይህንኑ ፍልስፍና የሚያብራራበት ነው፡፡ ሃርት ጆን ኦስቲን በስፋት የሚታወቅበትን “ህግ የሉዓላዊ አካል ትእዛዝ ነው” የሚለውን አባባል በመተቸት ጽሁፍን ይጀምራል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የሚያነሳቸው “ፅኑ ጥያቄዎችን” ነው፡፡ ሕግ በነገስታት ማስፈራሪያ ከታከለባቸው ትእዛዝ እንዴት እና በምን ይለያል? የህግ ግዴታስ ከሞራል ግዴታ ጋር ያለው ጉድኝት ምንድነው?

     “ህግ በቅጣት የተደገፈ የሉዓላዊ አካል ትእዛዝ ነው” የሚለው አባባል ለሃርት አልተዋጠለትም ፡፡ ህግ ከሉዓላዊ አካል ትእዛዛት በይዘት በምንጭ እና በተዳራሽነታቸው ስፋት እንደሚለዩ በመተንተን ይጀመራል፡፡ ለምሳሌ ሁሉም ህግጋት ትእዛዝ ላይሆኑ ይችላሉ አንዳንድ ህግጋት አመቻች ሌሎቹ ፈቃጅ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የሕግ ሁሉ ምንጭ አንድ “ሉዓላዊ አካል” አንደሆነ አድርገን መደምደም እንደሌለብን እና ህግጋት የተለያዩ ምንጮች ሊኖራቸው እንደሚችል ብቻ ሳይሆን ህግጋቱን ያወጡት አካላት ራሳቸው በሕግጋቱ መገዛት እንዳለባቸው ያትታል፡፡ ሃርት ሲቀጥል “በማህበራዊ ልማድ” እና በማህበራዊ ህግጋት” መሃል ልዩነት እንዳለ ይጠቅስና ማህበራዊ ልማዶች በማህበረሰቡ  በተለምዶ የሚደረጉ ወይም የማይደረጉ ነገሮች እንደሆኑና ቢጣሱም ያን ያህል ችግር እንደማይፈጥሩ ይገልጻል፡፡ “ማሀበራዊ ህግጋት” ግን ከማህበራዊ ልማዶች ከፍ ባለ መልኩ አስገዳጅነት እንዳላቸው እና ቢጣሱ ከማበረሰቡ ቅጣት የሚያስጥሉ ናቸው፡፡ መንግስት የሚያወጣቸው ሕግጋት ከማህበረሰባዊ ህግጋት ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ይጠቅስና ማህበረሰቡ በሌሎች 3ኛ ወገኖች ሲታይ ሕግጋቱን የሚተገብርበት ሁኔታ ውጪያዊ እይታ እንደሚባል ማህበረሰቡ ግን በፍላጎት ህጉን የሚተገብርበት ሁኔታ ውስጣዊ እይታ እንደሚባል ይጠቅሳል፡፡ ቀጥሎም አንድ ሕግ ጥራቱን እና ውጤታማነቱን የሚያገኘው ከዚህ ውስጣዊ እይታ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ የሕግ ስርዓትን ለመስፈን አስፈላጊው መስፈርት አንድ ተራዜጋ ለሕጉ ያለው ውስጣዊ እይታ ሳይሆን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሃላፊዎች ለሕጉ ያላቸው ውስጣዊ እይታ እንደሆነ ድርሳኑ አበክሮ ያሳስባል፡፡ ምክንያቱም ባለስልጣናት ከተራ ዜጋው ይልቅ በሕጉ የመገዛት ውስጣዊ ፍላጎት ከሌላቸው የመንግስት ተጠያቂነትን ማስፈን እንደማይቻልና የራሳቸውንም ሆነ የሌሎች የመንግስት ኃላፊዎችን ድርጊት መቆጣጠር እንደማይችሉ ይጠቁማል፡ 

     ሃርት ህግጋትን በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ አንደኛ ደረጃ ሕግጋት እና ሁለተኛ ደረጃ ሕግጋት ፡፡ አንደኛ ደረጃ ሕግጋት የማህበረሰቡን ምግባር እና ተግባር የሚገድቡና የሚያርቁ ናቸው፡፡ ማህበረሰቡ ማድረግ የሚገባውን እና የማይገባወን በዝርዝር ያመለክታሉ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ህግጋት ወይም አስቻይ ህግጋት የሚባሉት ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ህግጋት የሚቀየሩበትን፤ የሚሻሻሉበትንና የሚፈጸሙበት አግባብ ይደነግጋሉ፡፡ በተጨማሪም ቀዳሚ ህግጋት /አንደኛ ደረጃ ህግጋት ግልጽነት ፣ቅልጥፍና እንዲኖራቸው እንዲሁም ተገማች እና ተመሳሳይ እንዲሆኑ ያስችላሉ ወይም ያግዛሉ፡፡ 

     የሁለተኛ ደረጃ ህግጋት ደግሞ በራሳቸው ለሶስት ንዑስ ህግጋት ይከፈላሉ፤ እነዚሁም የቅቡልነት ህግጋት፤የለውጥ ህግጋት እና የሙግት ህግጋት ይባላሉ፡፡ የቅቡልነት ህግጋት አንደኛ ደራጃ ህግጋት ዕውቅና አንዲያገኙና ግልጽነት እንዲኖራቸው ያስችላሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ ንዑስ የቅቡልነት ህግጋት ቀዳሚ ህግጋት የሚጸድቁበትና ዕውቅና የሚያገኙበት የቅቡልነት መስፈርቶች በዝርዝር ሲያስቀምጡ ከጊዜ እና ሁኔታ ጋር ሊቀየሩ የሚችሉባቸው አግበብን ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚህ  ሕግጋት አንደኛ ደረጃም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ህግጋት ሊለወጡ እና ሊቀየሩ የሚችሉበትን መስፈርቶች ይዘረዝራሉ፡፡ መስፈርቶቹ እንደሁኔታው የሚለያዩ ሲሆን ህግጋቱን ሲያስቀምጡ እነማን ምን መቀየር እንደሚችሉና የሚቀይሩበትን ስርዓት በዝርዝር ያሳያል፤ የሙግት ንዑስ ህግጋት አንደኛ ደረጃ ህግጋት በተጣሱ ጊዜ እነማነ እንዴት ውሳኔ ያስተላልፋሉ የሚለውን የሚደነግጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የትኞቹ ቀዳሚ ህግጋት ሲጣሱ እነማን በእነማን ላይ የመዳኘት ስልጣን ይኖራቸዋል የሚለውን ያብራራሉ፡፡ 

     በሀገር የህግ ፍልስፍና ውስጥ መሰረታዊ የሆነው ጽንሰ ሃሳብ የቅቡልነት ሕግ ነው፡፡ ቀዳሚ ሕግጋት ቅቡልነት የሚያስገኙት በዚሁ ህግጋት ከሆነ ራሱ የቅቡልነት ሕግን እንዴት ልናውቀው እንችላለን? ብሎ ይጠይቅና ይህን ማወቅ የምንችለው የመንግስት እና የማህበረሰቡ ተለምዷዊ ድርጊት እና ልማድ በማየት መሆኑን ማለትም የመንግስት ተቋማትን፤ ፓርላማ፤ ፍ/ቤቶች፤ የህግ ባለሙያዎች አስተያየት እና የሕግ ምሁራን ጽሁፎች በመመርመር ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የሃርት እሳቤ የማህበረሰባዊ እውነታ መርህ (social fact theory) በመባል ይታወቃል፡፡ 

በኋላ ኬልስን ይህንን እይታ በመቀወም የህግ ልማድ እና ማህበረሰቡ የሚደርገውን አይተን የቅቡልነት ህግጋትን መመስረት አንችልም በማላት ንጹህ እና ያልተቀላቀለ የቅቡልነት ህግ ለመመስረት ጥረት አድርጓል፡፡

 የሕግ እና ሞራል ግንኙነትን በተመለከተ ከሃርት በፊት የነበሩ የሰው ሰራሽ ሕግ አስተምህሮ አቀንቃኞች ሕግ የሰው ልጅ ግኝት እንደመሆኑ በምንም መልኩ ማህበረሰባዊም ሆነ ግለሰባዊ ሞራል በሕግ አወጣጥ እና አተገባበር ላይ ተጽእኖ ሊያሳርፍ አይገባም በሚል ተከራክረዋል፡፡ ሃርት ግን የቅቡልነት ህግጋትን በምንለይበት ወቅት ማህበረሰባዊ ሞራል በራሱ የቅቡልነት ሕግ አካል የሚሆንበትን መንገድ ማስቀመጥ እንደሚቻል ይገልጻል፤ምክንያንቱም ህግ እና ሞራል የተለያዩ መሆናቸውን ሃሳባዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል ቢቻልም በልማድ እና በሕግ አተገባበር ወቅት ግን ሁለቱን መለያየት እጅግ ከባድ መሆኑን ያነሳል፡፡

 ከዚህ በተለየ መልኩ ጆሴፍ ራዝ የተባለ ፈላስፋ ሃርትን በመተቸት ሞራል እና ህግ መቼም ቢሆን በሰው ሰራሽ የሕግ ፍልስፍና ውስጥ ሊደባለቁ እንደማይገባ የህጉን የቅቡልነት መሰረት ማወቅ የምንፈልግ ቢሆን እንኳ ቀዳሚ ህግጋቱ የወጡባቸውን ምንጮች (sources of Law) በመመርመር በምንናገኘው የትርጉም ሂደት ልንገዛ ይገባል እንጂ ሞራልን በቅቡልነት ሕግጋት  ውስጥ ማካተት ተገቢነት የለውም ሲል ሃሳቡን ሰንዝሯል፡፡ 

     ሎርድ ዴቭሊን በበኩሉ የሞራላዊ ሕግ እሳቤ (Legal moralism) አመንጪ ሲሆን አንድ ሕግ የማህበረሰቡን የቡድን ሞራል (collective moral) ሊያስጠብቅ እንደሚገባ በማሰብ ተከራክረዋል፡፡ የአንድ ግለሰብ ደርጊቶች ምንም አንኳ በማህበረሰቡ ላይ በቀጥታ የአካልና የስነ-ልቦና ጉዳት ባያደርሱም እንኳ ከህብረተሰቡ የሞራል መሰረቶች ጋር የሚጋጩ ከሆነ ህጉ ሊያወግዛው እና ሊገድበው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የስተዋርት ሚልን “የጉዳት መርህ” በመተቸት ማበረሰቡ ላይ ጉዳት እስከሚደርስ ድረስ ህግ በግለሰቦች ደርጊት ጣልቃ ሳይገባ ይቀመጥ ማለት ለማህበረሰባዊ ሞራል ተገቢውን ክብር ያለመስጠት ውጤት መሆኑን አሳስበዋል፡፡ በርግጥ ሃርትም ቢሆን የሕገ-ሰብ ፍልስፍና አራማጅ እንደመሆኑ ሕግ “ስለሆነው” እንጂ “መሆን ስለሚገባው” መጨነቅ እንደሌለበት ይቀበላል ይሁንና በሕግና ሞራል መሀከል ያለው ጽንፍ የረገጠ ልዩነት ጠቃሚ እንዳልሆነ ያትታል፡፡


ትርጉም እና መርህ- ሮናልድ ደርኪን

ሮናልድ ዶርኪን የስነ-ሕግ አስተምህሮውን የጀመረው የሀርትን የሕገ-ሰብ ፍልስፍና በመተቸት ነው፡፡ ዶርኪን ይህንኑ ትችት ሲጀምር በህግ እና ሞራል መሀከል ያለውን ልዩነት የህገሰብ ፈላስፎች እጅግ እንደሚያከሩት ሕግ ከሞራል ተነጥሎ የራሱ የሆነ ሕይወት አለው ሊባል እንደማይቻል ይገልጻል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፍ/ቤቶች ውሳኔ በሚሰጡበት ወቅት ከሕግጋቱ ይልቅ አጠቃላይ መርሆዎች ላይ እንደሚያተኩሩ ይህም በሕግ እና ሞራል መሃል ያለውን ልዩነት እንደሚያጠበው ያሳያል፡፡ በመሆኑም ከህግ ይልቅ መርህ ዳኞች በእጃቸው ያለውን ጉዳይ እንዲፈቱ መሳሪያ ይሆናቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሰው ሰራሽ ህግጋቱ ሁሉንም አይነት አጨቃጫቂ የፍ/ቤት ጉዳዮች እና ግጭቶች የሚፈቱ ባለመሆናቸው መርሆዎች (legal principles) በተግባር ላይ ይውላሉ፡፡ የተደነገጉት ሕግጋት የማይገዟቸው እና ከሕግ አውጪው እይታ ውጪ የሆኑ ጉዳዮች በየእለቱ ለዳኞች እና ፍ/ቤቶች ይቀርባሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚህን “ብርቱ ገዳዮች” (Hard cases) ለመወሰን ዳኞች የተጻፈ ሕግ ማግኘት ስለማይችሉ ወይ ከዚህ ቀደም የተወሰኑ ጉዳዮችን በማየት ለዚህ ጉዳይ የሚመጥንና ከብዙ ህጎች በተውጣጣ አዲስ የሕግ ቀመር መሰረት ጉዳዮን ይወስናሉ ወይም አጠቃላይ መርህን መሰረት በማድረግ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ስለሆነም እነዚህ ብርቱ ጉዳዮች ባጋጠሙ ቁጥር ለጉዳዮ ፍትሐዊ የሚሆነውን ውሳኔ የሚያውቀው ዳኛው ብቻ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ዳኞች እነዚህ ጉዳዮች በሚያጋጥሙበት ወቅት ምክንያታዊ እና ትክክለኛ መልስ (the right answer thesis)የመሥጠት ሞራላዊ ሃላፊነት ይኖርባቸዋል ይልና ዳኞች በግሪክ አፈታሪክ ውስጥ ካለና ኃይልነት ከተጎናጸፈ አምላክ (Hercules) ጋር ያዛምዳቸዋል፡፡ 

     ዶርኪን እና ሃርት በምሁራዊ ስራቸው እና በግል ሕይወታቸው ወዳጆች የነበሩ ቢሆንም ደርኪን የሃርትን ሰራዎች በተደጋጋሚ ከተቹ ሰዎች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ለምሳሌ ሃርት ቀዳሚ ሕግጋት በሚላቸው ድንጋጌዎች መሃከል አንዳንዴ ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችልና ዳኞች እንደዚህ አይነት ክፍተት በሚያጋጥማቸው ወቅት የራሳቸውን ስልጣን (discretion) በመጠቀም ሊሞሉት እንደሚገባና የእነሱ ውሳኔም ሕግ የማውጣትን ያህል ሊቆጠር እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ ዶርኪን በበኩሉ በእነዚህ ብርቱ ጉዳዮች ወቅት ዳኛው ክፍተቱን በራሱ ስልጣን ተጠቅሞ ይሞላዋል ማለት አግባብነት የሌለው ነው፤ ይልቁንስ ዳኞች እነዚህን ጉዳዮች ሲወስኑ ከራሳቸው ስልጣን ወይም ተለምዷዊው የሕግ አተረጓጎም ይልቅ ”መርህ”ን መሰረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ይመክራል፡፡ ምክንያቱም የሕግ መርሆዎች ምንም እንኳ አጠቃላይ በሆነው የሰው ሰራሽ ሕግጋት ማዕቀፍ ውስጥ የሚካተቱ ባይሆንም የሕግጋቱን አጠቃላይ ፍልስፍና እምቅ በሆነ መንገድ የሚገልጹ ናቸው፡፡ 

     በተጨማሪም የሕግ መርሆዎች እርስ በእርሳቸው የማይጋጩ ሲሆኑ ሕግጋት ግን አንዳንዴም ቢሆን እርስ በእርሳቸው ይጋጫሉ፡፡ በመሆኑም አንድ ዳኛ የሕግ መርህ መርጠ ሲወስን መርሆው በስርዓቱ ካሉ ሰው ሰራሽ ሕግጋት ጋር የሚጣጣም መሆኑም ሊያረጋግጥ ይገባዋል፡፡ በመሆኑም አንድ ዳኛ ይህንን ተግዳሮት ሊፈታ በሚችል መልኩ አንድ ልዩ እና ተገቢነት ያለው መልስ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ እንዲህ አይነት መልስ ባያገኝ እንኳ ሊገኝ እንደሚችል ማመን ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም “ብርቱ ጉዳይ” የምንላቸው እነዚህ ፈታኝ ጉዳዮች በመደበኛ የሕግ ክፍተት ሳቢያ የሚፈጠሩ ፈተናዎች ከመሆናቸውም አልፎ ለዚህ ክፍተት ተገቢውን የህግ መርህ ለማግኘት በሚደረግ ትግል የሚፈጠሩ ናቸው፡ ዳኞች እነዚህ መሰል ጉዳዮች በምናስበው ሁኔታ እና በግልጽ የእለት ተእለት ስራዎቻቸው ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ መገመት ያሻል፡፡ እነዚህ ፈታኝ ጉዳዮች በተለምዶ በአብዛኛው በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቶች የሚቀርቡ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ 

    ምክንያቱም የይግባኝ አቤቱታ ምክንያት የሚሆኑት በአብዛኛው የሕግ ትርጉም ክፍተቶች በመሆናቸው ነው፡፡ ዶርኪን ሃርትን መተቸቱን ሊቀንስ ሃርት በተለምዶ የቅቡልነት ህግጋት የሚላቸው በማህበረሰባዊ እውነትነት የሚታወቁ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ዳኛ ከማህበረሰባዊ እውነታነት (social fact) የተወሃዱ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ በመርህ ላይ ተመስርቶ እንዲወስን ሊጠበቅበት ይችላል፡፡ በመሆኑም የዳኛው ወይም ባጠቃላይ የሕግ ስርዓቱ ዋነኛ ስራ “የሕግ ትርጉም” መስጠት ነው፡፡ ዳኛው የሕግ ትርጉም በሚሰጥበት ወቅት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ህጋዊ አሰራሮችን የሚደግፍ የሕግ መርህ በመምረጥ እና ይህ መርህም ከማህበረሰቡ ሞራል ጋር ያልተጋጨ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም የሕግ ትርጉም በሂደቱ እና ይዘቱ የስነ-ጥበባዊ ወይም የስነ-ፀሑፋዊ ትርጉም ወይም ሂስ ጋር እንደሚመሳሰል ይገልጻል፡፡ አንድ የስነ- ጥበብ ስራ በአንድ ሐያሲ ሰተረጎም ደራሲው የጻፈው ቃል እና ነጥብ ላይ ብቻ ባተኮረ መልኩ ሳይሆን ከሃያሲው እይታ አንጻር መርሆዎች ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ ሁሉ፤ ከሕግ ስርዓቱ አጠቃላይ ልምድ ጋር በሚስማማ መልኩ  የዳኛው ልዩ የአተረጓጎም ስልት መቼም ቢሆን አይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ያሳስባል፡፡ 

     በመሆኑም ይህንን የትርጉም ስልት ገንቢ ትርጉም (constructive interpretation) ሲባል ዳኛው የሚሠጠው ትርጉም በእነዚህ ፈታኝ ጉዳዮች ውስጥም ቢሆን ለህግ ስርዓቱ አጠቃላይ መርሆ እና አሰራር የቀረበ እና ለዚያ ጉዳይ ደግሞ በተናጠል ልዩ እና አርኪ መልስ የሰጠ መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ 

ፍጹማዊ የስነ-ህግ አስተምህሮ - ሃንስ ኬልስን

 በሀገረ- ኦስትሪያ ተወልዶ ያደገው ሃንስ ኬልሰን በአይሁዳዊነቱ ምክንያት በሂትለር   ወደ አሜሪካ ቢሰደድም በዘመኑ ፍጽማዊ የስነ-ሕግ አስተምህሮን (pure theory of Law) መሬት እንዳይዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ኬልሰን ቀዳሚውን የኦስትሪያ ሕገ መንግስት አርቅቋል በቪየና እንዲሁም በአሜሪካ በማስተማር እና በመመራመር ብዙ እውቀትን አግኝቷል፡፡ በአይሁድ ቤተሰብ ውስጥ ቢወለድም ሲያድግ በካቶሊክ እምነት ተከታይነት ከተጠመቀ በኋላ ከሚስቱ ጋር ቆየት ብሎ የሉተራን እምነት ተከታይ ሆነዋል፡፡ 

     ኬልስን በወቅቱ የነበረው የሕግ አስተምህሮ በፖለቲካዊ ርዕዮቶች፤ በሞራላዊ ለከብቶች እና በማህበራዊ ሳይንስ ፍልስፍናዎች ተጽእኖ ስር በመውደቁ እንደተበከለ ያስብ ነበር፡፡ በመሆኑም የሕግ አስምህሮን ከእነዚህ ሁነቶች ማንጻት ያስፈልጋል በማለት ተከራክሯል፡፡ የማንኛውም የህግ አስተምህሮ እና ስርዓት መሰረታውያን የሕግ ልማዶች ናቸው፤ ልማድ ማለት ደግሞ የድርጊት ትርጉም ነው፡፡ የሕግ ልማድ ስርዓት ህግጋት እና መመሪያዎች ሕጋዊ ቅቡልነታቸውን የሚያገኙበት አሰራር ነው፡፡ አንድ አዋጅ ሕጋዊ ቅቡልነትና ትርጉም የሚያገኘው በቀደመ እና ከፍተኛ በሆነ የሕግ ስርዓት የጸደቀ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህ ቀዳሚ እና ከፍተኛ የሕግ ስርዓትም እንዲሁ በቀደመ እና ከፍተኛ ከሆነ የሕግ ስርዓት ቅቡልነትን ማግኘት አለ በመሆኑም ህግጋት በእዚህ መንገድ የስልጣ ከዋረድ ይመሰርታሉ፡፡ ህግጋት ቅቡልነት እና ሕጋዊነት የሚያገኙበትን መስመር ተከትለን ወደ ኋላ ስንሄድ ሁሉም ህግጋት እና የሕግ ልማዶች ቅቡልነታቸውን እና ሕጋዊነታቸው ያገኙበትን አንድ ቀዳሚ እና መሰረታዊ ሕግ እናገኛለን፡፡ ይህ መሰረታዊ የሕግ ስርዓት (Grundnorm) በአንድ ሃገር የሚገኙ አዋጆችና መመሪያዎች በአንድነት የፈጠሩትን የህግ መረብ እና ሰንሰለት የሚያስጠብቅ እና የሚያቋቁም ነው፡፡ በመሆኑም በአንድ የሕግ ስርዓት ወይም በተለያዩ የሕግ ስርዓቶች ውስጥ ያሉ የሕግ አሰራሮች እና ልማዶች የተፈጠሩበት እና ቅቡልነት ያገኙበትን ምክንያት ከአንድ መሰረታዊ ሕግ የምናገኝ ከሆነ እነዚህ የሕግ ልማዶች ከአንድ የሕግ ስርዓት እንደተፈጠሩ መገመት ይቻላል፡፡ 

     በመሆኑም አንድ ሕግ ቅቡል ብቻ ሳይሆን ውጤታማም መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ይህ ሕግ የጸደቀበት አካሄድ ቀደም ብለን በጠቀስነው መንገድ ተገቢውን የስልጣን ተዋረድ ጠብቆ መሆን አለበት፡፡ በዚህም መሰረት “ፈጹም ” የሆነ የሕግ ስርዓት ለመመስረት የሕግ ስርዓቱን በሙሉ ከዚህ የሕግ ስልጣን ተዋረድ ውጪ ካሉ አስተሳሰቦች እና አሰራሮች ማንጻት ያስፈልጋል፤ ያን ጊዜ ይህ ንጹህና ፍጹም የሆነው የሕግ ስርዓት ተገቢውን ውጤታማነት ያገኛል፡፡ በመሆኑም ይህ ፍጹም የሆነ የሕግ መሰረታዊ በሆነ መልኩ በህገ-ሰብ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ አንደመሆኑ ሕግ ሰው ሰራሽ መሆኑን ይቀበላል፡፡ 

     አሁን ባለንበት ዘመናዊ የህግ ስርዓት ይህንን የኬልሰንን መሰረታዊ የሕግ ስርዓት /ልማድ/ (Grundnorm) ከሕገ መንግስት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን ኬልስን ቀዳሚውን የኦስትሪያ ሕገ መንግስት ማርቀቅ ብቻ ሳይሆን በንጉሱ ቀጥተኛ ትእዛዝ የኦስትሪያ ሕገ መንግስት ፍርድ ቤት አባል እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ ይሁን እንጂ ኬልሰን በአንድ ሀገር ውስጥ ከዚህ መሰረታዊ ህግ ውጪ ሌላ ተደራቢ ወይም አቻ የሕግ ስርዓት አንዲኖር አይፈቅድም በዚህም ምክንያት ባህላዊ ለሆኑ ሕግጋት እውቅና አይሰጥም፡፡ ከዚህም በላይ በአንድ የመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ የፅደቀ አንድ አነስተኛ መመሪያ ሂሳባዊ በሆነ መንገድ አንድ ሁለት ብሎ ምንጩን ከመሰረታዊው ህግ ጋር ማገናኘት አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ በራሱ የሚንሳፈፍ መመሪያም ሆነ አዋጅ ጸድቆ ወደ ስራ ቢገባ ቅቡልነት የሌለው ሕግ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ 

     ኬልስን መሰረታዊ ሕግ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአንድ የሕግ ስርዓት ውስጥ በተጻፈና በተለየ መንገድ የሚገኝ ወይም ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት ሕገ-መንግስት ላይሆን ይችላል፡፡ ኬልሰን ለመገንባት የሚፈልገው የአንድን የሕግ ስርዓት የቅቡልነት መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም መሰረታዊ ሕግ (Grundnorm) የተባለው ሕግ የሀገሪቱ መደበኛ ሕጎች አካል አይደለም፡፡ እንዲያውም ሕግጋቱ ሁሉ ቅቡልነታቸውን የሚያረጋግጡበት የሕግ አካል እና የአሰራር ዘይቤ ነው፡፡ በመሆኑም ለኬልስን ሰው ሰራሽ ሕግጋት በሙሉ ጥብቅ የሆነ የስልጣን ተዋረድ ሊኖራቸው አንደሚገባ እና ይህ ጥብቅ የሆነ የስልጣን ተዋረድ ደግሞ ሊረጋገጥ የሚችለው ጥብቅ የሆነ የቅቡልነት ሰንሰለት ከታች ወደ ላይ ሲዘረጋ ብቻ ነው፡፡

 በመሆኑም በአንድ የሕግ ስርዓት ውስጥ ያሉ ሰው ሰራሽ ሕግጋት በሙሉ ቅቡልነታቸውን ከአንድ የሚታወቅ ሕግ ወይም የሕግ አሰራር ሊያገኙ እንደሚገባና የሰው ሰራሽ ሕግ ፍልስፍና መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብም ይኸው መሆኑን ኬልሰን በተለያዩ ድርሳኖቹ እና ጽሑፎቹ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ በመሆም “መሰረታዊ ሕግ” የሚለውን ሀሳብ እንደ ሕግ ብቻ ሳይሆን የህግጋት ቅቡልነት ማግኛ እና ማስጠበቂያ አሰራር እንደሆነ አድርገን ልናየው ይገባል፡፡

 ሌላኛው ጥያቄ ሁሉም ሕግጋት ቅቡልነታቸውን ከዚህ ከዚህ መሰረታዊ ሕግ የሚያገኙ ከሆነ ይህ “ መሰረታዊ ሕግ” ቅቡልነቱን  ከየት ያገኛል? የሚለው ነው፡፡ ኬልስን ሲመልስ ይህ “መሰረታዊ ህግ” ቅቡልናው ቅድመ- ታሳቢ የሚደረግ ነው ምክንያቱም ከዚህ ህግ በላይ የሆነ የቅቡልነትም ሆነ የስልጣን የበላይነት ያለው ሕግ ሊኖር አይችልም ወይም አይገባም፡፡ በመሆኑም ሰው ሰራሽ ሕግጋት ከታች ወደ ላይ የሕንጻን አገነባብ ደረጃ በተከተለ መልኩ የሚገነቡ ናቸው ብንል መሰረታዊ ሕግ ልክ እንደመሰረት የሚያገልግል ነው፡፡ 


የሕግ ውስጣዊ  የሞራል  ውቅር - ሎን ፍለር

ፉለር በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፍልስፍና እና የውል ሕግ ያስተማረ ሲሆን ከሃርት ጋር በ1958 እ.ኤ.አ ባደረገው ታዋቂ ሙግት ሳቢያ አስከ ዛሬ ድረስ የሚታወቅበትን “ውስጣዊ የሞራል ውቅር” መስርቷል፡፡ ፉለር ለስነ-ሕግ ፍልስፍና እና ለተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍና መሀከለኛ የሆነነ መንገድ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ በቅድሚያ ሕግ ከልዕለ ሰባዊ ኃይል የመነጨ ዲበአካላዊ እና መንፈሳዊ ምንጭ እና ይዘት እንዳለው አይቀበልም ፤ይሁን እንጂ ሕግ ሰው ሰራሽ ቢሆንም የራሱ የሆነ ውስጣዊ የሞራል ውቅር እንዳለው ያምናል፡፡

ይህንኑ ጉዳይ ሲያብራራ በህግና ሞራል መሃከል ምንም አይነት ግንኙነት አንደሌለ እና ፍጹም የማይገናኙ ተደርጎ በቀደምት የሕገ-ሰብ ፍለስፍና አራማጆች የሚሰብከው አስተምህሮ ስህተት እንደሆነና ሕግ በመሰረቱ ሰው ሰራሽ ቢሆንም ሰው ሰራሹ ሕግም ቢሆን ውስጣዊ የሞራላዊ ይዘት እንዳለው እና ሊኖረው እንደሚገባ ያስረዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ህግጋት ሰው ሰራሽ ቢሆንም “ውስጣዊ የሞራል ውቅር” (internal morality of the law) ስላላቸው ሊታለፉ  የማይገባቸው  እነዚህ መስፈርቶች፡-

በቂ በሆነ መልኩ አካታችነት እና አጠቃላይነት

በይፋ  ለህዝብ የታወጁ

የወደፊቱን ትውልድ /ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ

እርስ በእርሳቸው የማይጋጩ እና የማይቃረኑ

ግልጽ እና በቀላሉ ለመረዳት የሚቻሉ

6. በየጊዜው የማይለወጡ እና የማይሻሩ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ቋሚነት ያላቸው፤

7. ለመታዘዝ እና ለመተግበር የማያዳግቱ

8. ሲተገበሩም ከታቀዱለት ዓላማ ውጪ ውጤት የማያመጡ

እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟላ ሕግ በቂ የሆነ የሕጋዊነት ይዞታ ያለው እንደመሆኑ ርትዕ ያለው እና ተገማች ሊሆን ይችላል፡፡

በሎን ፋለር እና ኤች ኤል ኤ ሃርት በ1958 ዓም በሐርቫርድ ሎው ሪቪው የታተሙ ሙግቶች ተካሄደዋል፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ሃርት ሕግና ሞራል  የሚገናኙበትን መንገድ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ የህግ ስራ የማኅበረሰብን ባህሪ መቅረፅ እና መምራት እንደመሆኑ ውጤት ተኮር ነው፡፡ በመሆኑም ሕግ ውጤታማ በሆነ መንገድ ይህንን ዓላማ ያሳካ ዘንድ እነዚህ ስምንት መስፈርቶች ጥብቅ በሆነ ስነ-ስርዓታዊ መንገድ መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ፉለር ጥናታዊ የተፈጥሮ የሕግ ፍልስፍና ቢቃወምም በተሻሻለ መልኩ የተፈጥሮ ሕግ ደጋፊ እና ተከራካሪ ሆኖ ቀርቧል ሲሉ የሚከራከሩ ሰዎች አሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ ፉለር ስነ-ስርዓታዊ የተፈጥሮ- ሕግ አቀንቃኝ (Procedural Naturalist) እንደሆነ ተደርጎ ቢታይም ሃርት ይህንን ሂደት ሲተች ፍለር “ሞራል” እና “ውጤታማነትን” አምታቶታል፤ ምክንያቱም ሕግ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲተገበር ማድረግ እና የሕግን ሞራል መፍጠር ለየቅል ናቸው፤ ምክንያቱም የፉለር መስፈርቶች እኩይ የሆነ ሕግ ለማውጣት ቢሆን ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊያገለግሉ ይችላል ይላል፡፡



ምዕራፍ አራት

ማህበረሰባዊ ውል እና የግለሰብ ነጻነት

ሕግ ከማኅበረሰባዊ ሞራል እና ልማድ ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳለው ሁሉ ከፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች ጋርም ትይዩ የሆነ እድገት እና ቅርበት ያለው ድንበርተኝነትን ይጋራል፡፡ ከሰው ልጂች የቅድመ ታሪክ ዘመን ጀምሮ ያለው የሕግና ሞራል ትስስር ብንመረምር ማኅበረሰባዊ ሞራል ለመንግሥት ሕግጋት መንገድ ጠራጊ በመሆን አገልግሏል፡፡ በዘመናዊ መንግሥታት ምስረታ ደግሞ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም እና ፍልስፍና ለሕጎች እና አዋጆች አቅጣጫ ጠቋሚ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን የትኛውም መንግሥት የሚያወጣው ሕግ የሚከተለው ፖለቲካዊ ፍልስፍና ነፀብራቅ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ሕግጋት የፖሊሲ እና የፖለቲካዊ ርዕዮተዓለም ማስፈፀሚያ መሳሪያ እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ በታሪክ ውስጥ የሁለቱ እድገት አቻነት ያለው በመሆኑ ፍፁም በሆነ መንገድ አንድነታቸውን እና ልዩነታቸውን ሰንጥቀን ማሳየት አንችልም፡፡

 በተወሰኑ ሁኔታዎች ፖለቲካዊ ርዕዮት የሆነው ሃሳብ የሕግ ፍልስፍና በመሆንም ሊያገለግል ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የጠበቀ ትስስሮች በሌሎች የፍልስፍና ዘርፎችም መታየቱ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ በሃይማኖት ፍልስፍና ወይም ስነ-መለኮት እና በዲበአካላዊነት ፍልስፍና (Metaphysics) መሃከልም የሃሳብ መወራረስን ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ስለ ሕግ ፍልስፍና የተመራመሩ ሰዎች እና ስለ ፖለቲካዊ ፍልስፍና የተመራመሩ ሰዎች በአብዛኛው አንድ አይነት ናቸው፡፡ የጆን ሎክ ማኅበረሰባዊ ውል (social contract) ፤ የቶማስ ሆብስ ሕገ-አራዊት (state of nature) እና የስቲዋርት ሚል “የነፃነት” ሃሳብ በአብዛኛው እንደ ፖለቲካዊ ፍልስፍና የሚታዩ ቢሆንም ከእነዚህ ፍልስፍናዎች መፅነስ በኃላ የተነሱ የሕግ ፍልስፍናዎች፤ ምርምሮች፤ የተዋጁ ሕግጋትን ተላለፉ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በእነዚህ ፍልስፍናዎች ተፅዕኖ ስር የወደቁ ናቸው፡፡

 ሕግና ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች የሚጋሯቸው ባህሪያት እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ በዚህ አጭር ፅሑፍ ብቻ ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ማሳየት አንችልም፡፡ በመሆኑም አንድ ማነፃፀሪያ መስፈርት ማኅበረሰባዊ ውል (social contract) ነው፡፡ በዘመናዊ የመንግሥታት ታሪክ ውስጥ ማኅበረሰባዊ ውል የዜጎችን እና የመንግስታትን መብትና ግዴታ ከመደንገግ እና ከማብራራትም አልፎ እንደ ሕግም እንደ ፖለቲካዊ ሰነድም ሊታይ የሚችል ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ እንደ ፖለቲካዊ ፅንሰ ሃሳብ የሚታየው ዜጎች ከመንግሥታቸው የሚፈልጉትን መብት እና ጥቅም እንዲሁም የራሳቸውን ግዴታ አስፈሪው የሚተማመኑበት የቃል ኪዳን ሰነድ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ውል በአንዳንድ ሁኔታ ሃገረ- መንግስትን የሚመሰርት ሲሆን በሌላ ሁኔታ ደግሞ ሃገረ- መንግስትን የሚያፀና ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ሃገር ያሉ ዜጎ እና የፖለቲካ ሃይላት የሚወዳደሩበትን፤ የሚተዳደሩበትን እና መብት የሚፈጥሩበትን ስርዓት ያስቀምጣል፡፡

 ይህ ማኅበረሰባዊ ውል ሕግ እንደመሆኑም በሕግ አዋቂዎች እና ምሁራን የሚብራራ፤ የሚተረጎም፤ ተጠቅሶ ውሳኔ የሚሰጥበት የሚሻሻል እና የሚሻር ነው፡፡ በተለምዶ ማኅበረሰባዊ ውል እንደሆነ ተደርጎ የሚወስደው ሕገ- መንግስት እንደመሆኑ እንደ ማንኛውም ሕግ በባለሙያዎች የሚተረጎም እና የሚብራራ መሆን አለበት እንጂ አንዴ ካፀደቀ በኃላ ሳይነካ የሚቀመጥ ቅዱስ መፅሐፍ አይደለም፡፡ በመሆኑም የዚህ የማኅበረሰባዊ ውል ፅንሰ ሀሳብ መነሻ የሆኑትን ፍላስፎች ሃሳብ መዳሰስ ያስፈልገናል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ውል አስፈላጊነት፤ አስገዳጅነት፤ የተዋዋይ ወገኖች ባህሪ፤ አስቻይ ሁኔታዎች እና መሰል ሁነቶች ላይ የተለያዩ ፈላስፎች የተለያየ ዓይነት አመለካከት አዳብረዋል፡፡ በመሆኑም የዚህ ውል ይዘት፤ ቅርፅ እና የሚሽፈነው ስፋት በብዙ  ይለያያል፡፡


ሕገ - አራዊት - ቶማስ ሆብስ

በእንግሊዝ ከነበሩ ታላላቅ ፈላስፋዎች መሃከል የሚመደበው ቶማስ ሆብስ ዘመን ተሻጋሪ የሆነው ድርሳኑ ለብዙ የማኅበረሰባዊ ሳይንስ ጥናቶች መሠረት ሆኗል፡፡ ሆብስ በወቅቱ በእንግሊዝ ሃገር ውስጥ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት እና የመንግስት መዳከም ስለተመለከተ የእርስ በእርስ ጦርነትን ከሚጋብዝ መንግሥት የተሻለ መንግሥት ለመገንባት ምን ዓይነት ንድፈ ሃሳብ ያስፈልጋል ለሚለው ጥያቄ የራሱን ፈላስፋን አስቀምጧል፡፡ ሆብስ በቅድሚያ መንግሥት እና ሕግ በሰው ልጆ መሃከል ባይኖር ምን ሊፈጠር ይችላል? በማለት ይጠይቅና ራሱ በሚሰጠው መልስ የሚፈጠረው ክፍተት ሕገ-አራዊትን (State of nature) እንደሚፈጥር ያስረዳል፡፡ 

በዘመነ- አራዊት ሰዎች ከሰውነት በታች ይወርዳሉ፡፡ መንግሥት ባለመኖሩ ሁሉም ደስ ያስኘውን ያለ ከልካይ ይፈፅማል፤ በሞራል እና ሕግ የማይገዛ ማኅበረሰብ በመፍጠሩ ግለሰቦች በራሳቸው ሕግ ተመርተው ያሻቸውን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ከመሯሯጥ በስተቀር የሚገዙበት ቆስቋሽ ምክንያት የላቸውም በሕግ የተደራጃ ማህበረሰብ ባለመኖሩ ባህል፣ ሳይንስ፣ ስነጥበብ የጊዜ፤ቦታ ንቃተ ህሊና አይኖርም፡፡ በመሆኑም የግለሰብ ሕይወት የተነጠለ፤ የተጎሳቆለ፤ አስከፊ፤ ያልሰለጠነ እና እጅግ አጭር ይሆናል፡፡ 

በዚህ አስከፊ ምናባዊ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም በጉልበት የሚያስጠብቁ እንደመሆናቸው በማያበራ ጦርነት ውስጥ ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ በመሆኑም በሕጉ- አራዊት ውስጥ ያሉ ሰዎች በጦርነት ውስጥ ለመኖር ከመገደዳቸውም አልፎ ይህ ጦርነት ሁሉም በሁሉም ላይ ያወጀው ጦርነት እንደመሆኑ በቀላሉ ሊገታ የማይችልና አስከፊ እንደሚሆን ያስታውቃል፡፡ ይሁን እንጂ ሰዎች በሕገ አራዊት ተመርተው ከሰውነት በታች ወርደው ተራቆቱ እንጂ የአመክንዩ ጥበባቸውን ያልረሱ በመሆናቸው አንዳንዶች የሰው ልጆች በሰላም እና በተረጋጋ ሁኔታ መኖር እንዳለባቸው ሰው በመሆናቸው ብቻም በተፈጥሮ የታደሉት የማይገረሰስ፤ የማይነጠል እና የማይለወጥ የከበረ መብት እንዳላቸው ለመገንዘብ ይገደዳሉ፡፡

 በዚህ አባባሉ ምክንያት ብዙ ሰዎች ቶማስ ሆብስ የተፈጥሮ ሕግ ፈላስፋናን ይደግፋል ወይም ይከተላል በማለት ይከራከራሉ፡፡ በሕገ-አራዊት መኖር የሰለቻቸው እነዚህ ሰዎች የራሳችንን መብት እና ጥቅም የሚያስጠብቅ አንድ “ሉዓላዊ አካል” መፍጠር አለብን በማለት መስማማት ላይ ይደርሳሉ፡፡ ይህ የጋራ ስምምነት ወይም ማኅበራዊ ውል ይህን ሉዓላዊ አካል ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም ሉዓላዊነት የተሰጠ እንጂ የተገኘ አይሆንም፡፡ ይህን ሉዓላዊ አካል ለመፍጠር ሰዎቹን ያነሳሳቸው ዋነኛ ምክንያት ፍርሃት ነው፡፡ በዘመነ- አራዊት ውስጥ የሚኖር ሰው ድንገትና ባልጠበቀው ሁኔታ በሌላ ግለሰብ ጥቂት ሊደርስበት እና ጥቀቱን ያደረሰበትም ሰው ያለ ምንም ቅጣት ሊኖር ይችላል፡፡ በመሆኑም ይህን “ሉዓላዊ አካል” በስምምነት ወይም ውል የፈጠሩ ሰዎች ራሳቸው በዘመነ-አራዊት ሲኖሩ ከታደሉትና የፈለጉትን ነገር በፈለጉት ሰው ላይ እና በፈለጉት ጊዜ የማድረግ እንስሳዊና ያልተገደበ መብት ቀንሰው ለዚህ በትብብር ለፈጠሩት ሉዓላዊ አካል ይሰጡታል፡፡ ይህ ሉዓላዊ አካልም በተራው የእነዚህን ተዋዋይ ወገኖች መብት እና ሕይወት የመጠበቅ ግዴታ ይጣልበታል፡፡ 

ሆብሰን ይህ የተፈጠረውን ሉዓላዊ አካል “ሌዋታን” ሲል ይጠራዋል፡፡ ሌዋተን በአፈ ታሪክና በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚታወቅ አስፈሪ የባህር ውስጥ አውሬ ነው፡፡ ይህንን ስዕል መሳል የፈለገው ይህ ሉዓላዊ አካል ከተፈጠረ በኃላ በተዋዋይ ወገኖች ፍጹሞ የሆነ ታዛዥነት ሊኖረው እና ስልጣኑም ፍፁም መሆን እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡ የዚህ ፍፁማዊ ስልጣን መብት ጉዳይ ብዙ ሰዎችን አያስማማም እንዳንዶች እንዲያውም ሰዎች ሌላ ሰውን በመፍራት በውል የፈጠሩት አካል በሚደርስባቸው ፍርሃት አዘል አገዛዝ ስር ከወደቁ አንድን መጥፎ ነገር በሌላ መጥፎ እንዳመተካት ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ 

ሌዋታኑ ”ፍፁም ሉዓላዊ አካል” እንደመሆኑ ሕግ የማውጣት፤ ሕግ የመተርጎም እና ሕግ የማስፈፀም ፍፁማዊ ስልጣን አለው፡፡ በመንግስቱ ስር ለሚኖሩ ተዋዋይ ወገኖች የሚሰጠውን ትዕዛዝም ዜጎች ፍፁማዊ በሆነ መንገድ ሊከተሉት እና ሊታዘዙት ይገባል፡፡ ይህ ጉዳይ ፍልስፍናውን ከሕገ- ሰብ ፍልስፍና ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ጆንኦስቲን የዚህን የሕግ ፍልስፍና መሠረት ሲጥል “ሕግ ማለት ከሉዓላዊ አካል የተሰጠ ትዕዛዝ ነው” በማለት እንደደመደመ ማስታወስ አለብን፡፡ ምንም እንኳ የኦስቲን እና የሆብስ “ሉዓላዊ አካላት” በፍልስፍናዊ የንድፈ ሃሳብ አመሠራረታቸው እና በሚያስገኙት ውጤት እጅግ የተለያዩ ቢሆኑም ሁለቱም ሕግ የሉዓላዊ አካል ትዕዛዝ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ በመሆኑም የሆብስ ፍልስፍና ከተፈጥሮ ህግ ፍልስፍና እና ከሕገ-ሰብ ፍልስፍና ጋር የሚጋራው እና የሚያመሳስሉት ነገሮች እንዳሉት መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ ሆብስ ቀዳሚ የሆነውን የማኅበራሰባዊ ውል (ፍልስፍና) የጠነሰሰ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምክንያቱም በሕገ-አራዊት የሚመሩት ሰዎች ሌዊታኑን ወይ ሉዓላዊ አካሉን የሚፈጥሩት በጋራ በሚያደርጉት ስምምነት ነው፡፡ ይህን ስምምነት አንድ ማኅበረሰባዊ ውል አድርገን ልንወስደው ይገባል፡፡ ሆብስ ያሰበውን መሠረታዊ ውል በኃላ ላይ የማኅበረሰባዊ ውል ፈላስፎች አዳብረው እና አስፋፍተው የዘመናዊ መንግስት መመስረች እና መተዳደሪያ ፅንሰ ሃሳብ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ የአንድ ሃገር ዜጎች በፍርሃት አማካኝነት ለተፈጠሩበት የደህንነት ስጋት መብታቸውን የሚያስጠብቅላቸው አንድ ሉዓላዊ ተቋም ቢፈጠተሩም ይህ አካል የዜጎቹን ደህንነት ከማስጠበቅ በዘለለ በዚያው ውል አማካኝነት ተጨማሪ ግዴታዎች፤ መብቶች እና ኃላፊነቶች ሊጣሉበት ይችላል፡፡ 

ህዝባዊ ፍቃድ - ዣን ዣክ ሩሶ

ሩሶ የፈረንሳይ አብዮት የመንፈስ አባት ታላቁ የዘመነ አብርሆት ተመራማሪ በመባልም ይታወቃል፡፡ የፈረንሳይ አብዮተኞች የእርሱን ፍልስፍናዎች እና አስተምህሮዎች አብዮቱን ለማቀጣጠል ተጠቅመውባቸዋል፡፡ ሩሶ ጄኔቫ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ቢሆንም የሞተው ፈረንሳይ ውስጥ ነው፡፡ ስራዎቹ ከፖለቲካ ፍልስፍና እስከ ትምህርት ፍልስፍና ፤ ከሙዚቀኝነት እስከ የፈጠራ ጽሁፍ ባለሙያነት ድረስ የተስፋፉ ናቸው፡፡ ሩሶ ከደረሳቸው መጻህፍት መሃከል አንደኛው ርዕሱ ራሱ ማህበረሰባዊ ውል የሚል ነው፡፡

በዚህ ድርሳኑ ከእርሱ ቀድሞ የነበረውን ቶማስ ሆብስን ክፉኛ ይተቻል፡፡ በእርሱ አስተያየት ሆብስ በህገ አራዊት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን እንደ አረመኔ አራዊት ፤ ማገናዘብ የማይችሉ፤ ራስ ወዳድ እና ጨካኝ አድርጎ መሳሉ ስህተት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ሩሶ ይህንን ቅድመ መንግስት ተምኔታዊ ሁኔታ ህገ አራዊት የሚሰፍንበት ሳይሆን ህገ ተፈጥሮ የሚገዛበት እንደሆነ ይናገራል፡፡ በህገ ተፈጥሮ ውስጥ ደግሞ ሰዎች ከእውነተኛ ማንነታቸው ውና ከተፈጥሮ ጋር ሰለ ሚዋህዱ ነጻ ፤ አስተዋይ እና ደግ እንደሚሆኑ ይከራከራል፡፡ በመሆኑም ለሰዎች የተሻለው ነገር በዚህ አይነት ምናባዊ ሁኔታ ውስጥ መኖር ነው፡፡

በህገ ተፍጥሮ ውስጥ የሚኖሩት ዜጎች ምንም እንኳ የዘመናዊነት ጸጋን ባይታደሉም ከላይ እንደተባለው በተፈጥሮ የተገኙ መልካም ባህሪያት አሉት፡፡ እንዲያውም በተፈጥሮ ህግ ስር የሚኖር ግለሰብ በቅድመ ሰው ስልጣኔ አረመኔነት እና በዘመናዊ ስልጣኔ የሞራል እና የማህበረሰብ ግንኙነት ውድቀት መሃከል የሚገኝ እንደመሆኑ ትክክለኛው የሰውነት መለኪያ እንደሆነ አበክሮ አሳስቧል፡፡ ይህ በህገ ተፈጥሮ ውስጥ የሚኖር ግለሰብ ቀጣዩ ሰበዓዊ የእድገት ደረጃ መንግስት መመስረት መሆኑን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሲረዳ ተሰባስቦ ማህበረሰባዊ ውል በመመስረት መንግስት ያዋቅራል ፡፡ ይህ ማህበረሰባዊ ውል የተዋዋይ ወገኖች አጠቃላ ስምምነት ያለበት በመሆኑ ህዝባዊ ፍቃድ (General will) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ህዝባዊ ፍቃድ የህዝብ ሉአላዊነት መገለጫ እንደመሆኑ ህግ አውጪው፤ፈጻሚው እና ተርጓሚው ሳይሸራርፉ ሙሉ ለሙሉ ሊያስፈጽሙት ይገባል፡፡


አሪስቶክራቱ ፈላስፋ- ጆን ሎክ

ጆን ሎክ በሙያ ክህሎቱ ሃኪም የነበረ ሲሆን ይህንኑ ሙያ በመጠቀም ከእንግሊዝ መሳፍንት እና ንጉሳዊ ቤተሰቦች ጋር በፈጠረው ግንኙነት የመንግስት አሰራርን እና ፖለቲካን በሚገባ ለመገምገም ዕድል አግኝቷል፡፡ የጆንሎክ የማኅበረሰባዊ ውል ፍልስፍና ከሆብስ በተለየ ሁኔታ የሰዎችን ባህሪ ይገመግማል፡፡ በመንግስት አልባነት ወቅት ሆብስ እንደሚፈራው እና እንደሚተነብየው ሕገ-አራዊት አይሰፍንም ይልቁንም ሰዎች በተፈጥሯቸም መልካም እና በጎ በመሆናቸው መንግስት ባይኖር እንኳ እርስ በእርሳቸው ወደ መጠፋፋት አይሄዱም፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜም ቢሆን በጋራ ወደ መተማመን እና መስማማት በመምጣት መንግስትን ለመፍጠር አይቦዝኑም፡፡ መንግስትን ለመፍጠር የሚገቡበት “ማኅበረሰባዊ ውል” ዋነኛ ዓላማ ግን እርስ በእርስ እንዳይገዳደሉ እና እንዳይጠፋፉ የሚጠብቃቸው አካል ለመፍጠር ሳይሆን ነፃነታቸውን እና ንብረታቸውን የሚያስከብር ከሌላ ሰው ጋር ክርክር ውስጥ ቢገቡ “ነፃና ገለልተኛ ዳኝነት” የሚሰጥ ተቋም ለመፍጠር ነው፡፡

    በመሆኑም በዚህ ማኅበረሰባዊ ውል የሚፈጠረው አካል ሆብስ እንደሚለው አስፈሪ “ሌዋታን” ሳይሆን ማኅበረሰባዊ ውሉን የተዋዋሉት ሰዎች ለጋራ ጥቅማቸው ብለው የሚቀጥሩት ሠራተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳ በተሰጠው ኃላፊነት አማካኝነት ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ መብት ቢኖረውም ለሎክ መንግስት ፍፁማዊ አንምባገነንነት የተጎናፀፈ አይደለም ሊሆንም አይገባም፡፡ በመሆኑም መንግስት ከሕዝቡ በሚሰበስበው ቀረጥ አማካኝነት የሕዝቡን መብት በተለይም የግል ንብረትን የማስጠበቅን የፀና ልዩ እና የማይተካ ሚናውን ሊፈፅም ይገባል ምክንያቱም ንብረት ማፍራት መንግስትን ከመፍጠር ይቀድማል፡፡ 

ጆን- ሎክ ሰዎች በመሠረታዊነት መልካም እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ የማይነጣጠሉ እና የማይገረሰሱ መብቶች እንዳሏቸው እና እነዚህም ሕይወት፤ ነፃነት እና ንብረት የማፍራት መብት እንደሆኑ ፅፏል፡፡ የጆንሎክ ፅሑፍ አሜሪካ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ተላቅቃ የራሷን ሃገረ- መንግስት እና ሕገ-መንግስት እንድታቋቁም ተፅዕኖ አድርጓል ተብሎ ይታሰባል ምክንያቱም የእርሱ ሐሳቦች በአሜሪካ ሕገ-መንግስት ውስጥ ተካትዋል፡፡ ጆንሎክ ራሱ የእንግሊዝ መንግስት ባቋቋመው የመሬት ስሪት እና ክፍፍል ኮሚቴ ውስጥ ተሳትፎ መሬትን እየለካ ያካፍል ስለነበረ መንግስት እና ሕዝብ በግል ንብረት ወይም ሃብት ማፍራት እና በማስጠበቅ ላይ ያላቸውን ፍንጪ በግልፅ እና በቅርበት ተመልክቷል፡፡ ጆንሎክ ስለ ንብረት የፃፋቸው ሃሳቦች በንብረት ሕግ ፍልስፍና ውስጥ በመርሆነት እና ማስተማሪያነት አገልግለዋል፡፡

 ሎክ ሰዎች ንብረት ወይም ሃብት የሚያፈሩት ጉልበታቸውን በተፈጥሮ ከተገኘ ሃብት ጋር ሲያገናኙት እና ሲያዋህዱት መሆኑን ፅፏል፡፡ ይህ በተለምዶ The Labor theory of Ownership የሚባል ሲሆን ለሎክ ፈጣሪ የተፈጥሮ ሃብትን ለሰው ልጆ ሁሉ በጋራ እና በእኩልነት የሰጠ በመሆኑ የሰው ልጆች ይህን የተፈጥሮ ሃብት የግላቸው ለማድረግ የግላቸው መሆኑን እርግጠኛ ከሆኑበት የራሳቸው ጉልበት ጋር ሊያዋህዱት ይገባል፤ ሰዎች ወደ ግላቸው ሊያዞሩት የሚገባው ሃብትም ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ሠጥቶ ከተረፈው ላይ ብቻ ነው፡፤ በመሆኑም ሰዎች ተሰባስበው የሚፈጥሩት ይህ ማኅበረሰባዊ ውል ሕይወታቸውን እና ነፃነታቸውን ከመጠበቅ አልፎ የልፋታቸው ውጤት የሆነውን የግል ሃብት ሊጠብቅላቸው ይገባል፡፡ 

በመሆኑም ሰዎች ማኅበረሰባዊ ውል የሚመሰረቱት ለሕይወታቸው በመስጋትና በፍርሃት በመጠርነፍ ሳይሆን አስቀድሞም ቢሆን በተፈጥሮ ያገኙት የማይነጠል እና የማይገረሰስ መብት የሚጠብቅ ሰራተኛና አገልጋይ ለስራው ኃላፊ እና ተጠያቂ የሚሆን መንግስት ለመመሰረት ነው፡፡  


የፍትሕ ቀመር- ጀን ሮውልስ

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከተነሱ ጥቂት ፈላስፎች መሃከል ከሮውስ ጋር በአቸነት የሚቆሙ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሮውልስ በሕግና በፖለቲካ ፈላስፎች የሚታወቀውን የማኅበረሰባዊ ውል (Social contract) ሃሳብ እጅግ ጥልቀት ባለው መልኩ እንዲራቀቅ እና እንዲስፋፋ አድርጎታል፡፡ ከ600 ገጽ በላይ በሆነው ድርሳኑ ፍትሃዊ ርትዕ (Justice as fairness) በሚል የሰየመውን የፍትህ ቀመር ለማብራራት ሞክሯል፡፡ ፍልስፍናውን የሚጀምረው የጠቀሜታውያንን የሞራል ፍልስፍና በመተቸት ነው፡፡ ጠቀሜታዊ የሞራል ፍልስፍና የግለሰቦችን ልዩ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ የማያስገባ እና ከደስታ በፊት የትክክለኛነትን ጥያቄ የማይመለስ ነው፡፡ አንድ ድርጊት ለሰፊው ሕዝብ መጠነ ሰፊ ደስታ ያመጣል ተብሎ ከመታሰቡ በፊት ለአንድ ግለሰብ ደስታ እንደሚያመጣ እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ ከዚያም አልፎ ግለሰቡ ደስታን ያመጣው ድርጊት ያስገኘለትን የእርካታ ደረጃ ከመለከታችን አስቀድሞ ትክክለኛነቱንና ቀናነቱን መለካት ይኖርብናል፡፡ 

የሮውልስ ፍትሃዊ ርትዕ መሠረታዊ በመሆነ መልኩ ከማህበራሰባዊ ውል ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ የሚፈልቅ ነው፡፡ ይሁንና የዚህን ማኅበረሰባዊ ውል ይዘትና ቅርፅ ከመወያየታችን በፊት ይህን ውል ከጥንታዊ መሠረቱ ጀምሮ እንዴት፤ ለምን እና እነማን ተዋዋሉት የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ በመሆኑ ሊመለስ ይገባዋል፡፡ ይህ ውል ሳይፈፅም በፊት ያለውን ምናባዊ አሰላለፍ “ቀዳማዊ ሁኔታ” (orginal position) ብንለው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ተዋዋይ ወገኖች ያሉበት አቋም እና ማንነትም መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ “ቀዳሚዊ ሁኔታ” ያሉ ተዋዋይ ወገኖች ግለሰባዊ የማንነት መሠረታቸውን እንዳይረዱ “የመርሳት ሽፋን” (veil of Ignorance) በሚባል ተግዳሮት ፆታቸውን፤ የማኅበረሰባዊ መደባቸውን፤ ሃይማኖታቸውን፤ ብሔራቸውን እና መሠል ማንነታቸውን ከመገንዘብ ተከልክለዋል፡፡

 ይሁን እንጂ መሠረታዊ  የአመክንዩ እድል እና መሰረታዊ የሰሌት እውቀት ክምችት አላቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ የመርሳት ሽፋን ተከልለው በዚህ ማኅበረሰባዊ ውል ወሰን መካተት ስላለባቸው እና ስለሌለባቸውም መርሆዎች እና አንቀፆች ተከራክረው እና ተወያይተው ለእያንዳንዱ ተዋዋይ ወገን የሚያስማማ እና የተሻለ ሕይወት ለመኖር የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያደርጉትን ድርድር ሮውልስ ሂሳባዊ በሆኑ ቀመሮች በምናብ ተመርቶ አስቀምጧቸዋል፡፡ በመሆኑም ተዋዋይና ተደራዳሪዎቹ በኃላ የመርሳት ሽፋኑ ሲነሳ በውሉ መሠረት የሚደርሳቸውን ዕጣ ስለማያውቁ ድንገት የማያምር ዕጣ ሊደርሰኝ ይችላል ብለው ስለሚሰጉ ለሁሉም ተዋዋይ ወገኖች ሊያስማማ የሚችል መርህ በውሉ ውስጥ እንዲሠፈር ይከራከራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 በመሆኑም በድርድሩ ወቅት ያሉ ተዋዋይ ወገኖች በእነዚህ ሁለት የፍትህ መርሆዎች ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አንደኛው መርህ ሁሉም ሰው በእኩልነት እና በነጻነት ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ ሁለተኛው መርህ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስክ እኩልነት እንዳይኖር ሊፈቀድ የሚችለው በሚደረገው ውል የአነስተኛ ተጠቃሚነት ዕጣ ለሚደርሰው ወገን ጥቅም ከሆነ እና ይህን የተሻለ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ የማገኘት እድል ለሁሉም ሰው የተሰጠ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ 

ሁለተኛው መርህ “የልዩነት መርህ” በመባልም ይታወቃል ምክንያቱም በቀዳማዊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ተዋዋይ ወገኖች መጨረሻ ላይ አነስተኛ የማኅበረሰባዊ ወለል ላይ የሚገኝ የሕይወት ዕጣ ሲደርሳቸው አንዳንዶች ሃብታም ሊሆኑ የሚገባው አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ሕይወት የሚጠቅም ቁስ የሚያመርቱ ወይም መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ የልብ ስፔሻሊስት ዶክተር ቅንጡ መኪና እና ሰፊ ቤት ቢኖረው በሙያው እጅግ ብዙ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የልብ ሕሙማን የሚረዳ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ 


ስለ ነፃነት- ስቱአርት ሚል

ስቱአርት ሚል በስፋት የሚታወቀው የጠቀሜታውያንን የሞራል ፍልስፍና በማስፋፋት ነው፡፡ የሚል አባት ጄሞስ ሚል የጄርሚ ቤንተሞ አድናቂ እና ተከታይ በመሆኑ ልጁ ሰቱዋርት ሚልን የሚቀጥለው የጠቀሜታውያን የሞራል ፍልስፍና አቀንቃኝ እንዲሆን ከልጅነት ጀምሮ ኮትኩቶ አሳድጎታል፡፡ ስቱአርት ሚል ገና በሕጻንነቱ ግሪክ እና ላቲን አጥንቷል፤ ይህ ከፍተኛ የጥናት እና ምርምር ስራው ከቤተሰቦቹ ከፍተኛ ጫና ጋር ሲደመር በሃያ አመቱ የአዕምሮ ጤና መታወክ እንዲደርስባት አድርጎታል፡፡ በሂደት የረጅም ጊዜ ጓደኛው የሆነችውን ሃሪየት ቴይለር የተባለች እንሰት ሲያገባ ግን ሕይወቱ እየተረጋጋ እና የፍልስፍና አስተምህሮቶቹም ቅርፅ እየያዙ ሄደዋል፡፡ 

ስቱአርት ሚል “ስለነፃነት” ወይም “On Liberty” የተሰኘውን አነስተኛ ፅሁፍ አዘጋጅቶ እንዲጨርስ በብዙ የረዳችው ሚስቱ እንደሆነች ገልጿል፡፡ ይህች አነስተኛ ድርስን በሕግ ፍልስፍና ታሪክ እና በምዕራባዊያን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ሆናለች፡፡ ይህች ፅሁፍ እስካሁን ድረስ በህግ ትምህርት ቤቶችና በአውሮፓ ፓርላማዊ የሚቀነቀነውን “የግለሰባዊነት” አስተምህሮ ያስጀመረች ናት ቢባል መጋነን አይሆንም፡፡ ይሀች ድርሳን “ግለሰባዊነት” የሕግ ከለላ እንዲኖረው በጽኑ ትከራከራለች፡፡ ግለሰብ የብዙሃኑ አስተሳሰብ ሊጫንበት እንደማይገባና ሕግና መንግስትም የብዙሃኑን መብት ለማስጠበቅ ከመስራት ይልቅ የግለሰቡን መብት በማስጠበቅ ላይ ቢሰሩ እንደሚሻል ትመክራለች፡፡ ሚል “የብዙሃኑ አንባገነንነት” በሚል የሚጠቅሰው አፈና ግለሰቡ ማንንም ሳይጎዳ በሚያራምደው የሕይወት ዘይቤ ላይ የተቀጣ ጥቃት እንደሆነ አበክሮ ይገልፃል፡፡ 

ለመሆኑ የግለሰብ ነፃነት ማለት ምን ማለት ነው መንግስትስ ነፃነትን ለመገደብ የሚገደደው መቼ ነው ግለሰቡም የመንግስትን ጣልቃገብነት መቃወም የሚችለው መቼ ነው የሚሉ ሃሳቦች በሰፊው ተብራርተዋል፡፡ ለሚል በታሪክ ውስጥ በስልጣን እና ነፃነት መሃከል የማይሞት ትግል አለ፡፡ በመንግስት ስልጣን እና በዜጎች ነፃነት መሃከል ያለው ቅራኔ በሂደት የዜጎችን ነፃነት እና መብት እያገዘፈ መሄድ አለበት፡፡ በሰው ልጅ ቀዳሚ የመንግስት ምስረታ ዘመናት መንግስት እንዲመሰረት እና ማኅበረሰብ እንዲፅና ነገስታት እና መንግስታት በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ሃይል ሲያሳርፉ ኖረዋል፡፡ ዘመናዊ የሆኑ መንግስታት ከተመሠረቱ እና የዲሞክራሲ ስርዓት ከተገነባ በኃላ ግን ዜጎች ራሳቸውን በሕግ ማስገዛት ጀመሩ ይሁን እንጂ በዚህ ዘመንም ቢሆን ከመንግስት አንምባገነንነት እና ጭቆና ይበልጥ ለግሰለብ መብት አስፈሪ የሆነው “የብዙሃኑ አምባገነንነት” ነው፡፡ ምክንያቱም ሳለው የሕዝብ አመለካከት በሕግ አይመራም፤ የሚታወቅ ተቋም የለውም፤ የተፃፈ ሕግ አይኖረውም፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ የሰረፀው አስተሳሰብ በታሪክ ቀድሞ በብዙሃኑ ተቀባይነት ስላገኘ ብቻ በነፃ ግለሰቦች አስተሳሰብ ላይ ጫና እያሳደረ ይኖራል፡፡ 

“ስለነፃነት” የተባለው ድርሳን ነፃነትን በሶስት ይከፈላል እነዚህ አንደኛው የሃሳብ እና የስሜት ነጻነት፤ ሁለተኛው ፍላጎትን የማርካት ነፃነት ሲሆን ሶስተኛው የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነፃነት ነው፡፡ የሰው ልጅ የፈለገውን ሃሳብ የመያዝ እና ይህንኑንም የማቀንቀን መብት አለው፡፡ በተጨማሪም ፍላጎቱን እና ጥማቱን ባሰኘው መንገድ የማርካት ነፃነት ሊኖረው ይገባል፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት እና ሃሳብ ከማኅበረሰቡ ልማድ አንፃር ሲታይ ኢ- ሞራላዊ መስሎ የሚታይ ቢሆን እንኳ ሌላ ሰው ላይ ግልፅ የሆነ “ጉዳት” እስካላደረሰ ድረስ ሊታገድ አይገባውም፡፡ ሚል “የጉዳት መርህ” የሚባል የሞራል መርህም ያስቀምጣል፤ መንግስት በግለሰቦች ነፃነት ጣልቃ መግባት የሚገባው ነፃነታቸውን የሚጠቀሙበት መንገድ በሌሎች ግለሰቦች ላይ ግልፅ እና የማያሻማ ጉዳት ሲያደርሰ ብቻ ነው፡፡

 ከዚህ በተጨማሪ ነጻነታቸው ሊገደብ የሚገባው ሕፃናት እና አንዳንድ “ያልሰለጠኑ ሕዝቦች” ናቸው፡፡ በመሰረታዊነት አንድ ማኅበረሰብ “ግለሰባዊነትን” ሊያበረታታ ይገባል “ግለሰባዊነት” እየተበረታታ ሲሄድ ፈጠራ እና ብዙሃንነት እየጨመረ ከመሄዱም በላይ ግለሰባዊነት ሰው የመሆን የመጨረሻ ግብ እና ጥልቅ እርካታን መጎናፀፊያ መንገድ ነው፡፡ ግለሰቡ የራሱን ማንነት እና ፍላጎት እስከ መጨረሻው ድረስ በመሄድ እንዲፈለግ እና እንዲያሟላ ሊፈቅድለት ይገባል ሲልም ተከራክሯል፡፡ 

በተጨማሪም ግለሰቡ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ሊቃወም የሚችልባቸው መስፈርቶች አስቀምጧል፡፡ አንድ ግለሰብ በመንግስት ተአቅቦ የደረሰበትን ድርጊት ከመንግስት በተሻለ ብቃት ድርጊቱን የመፈፀም አቅም ሲኖረው ወይም ግለሰቡ ከድርጊቱ ልዩ ጥቅም የሚያገኝ ከሆነ ወይም ድርጊቱ የመንግስትን ስልጣን ያለአግባብ አግዝፎ ግለሰቡን በመንግስት ላይ ጥገኛ የሚያደርግ ከሆነ አንድ ሰው መንግስት በግለሰቦች ላይ የሚያደርሰውን ጣልቃ ገብነት መቃወም ይኖርበታል፡፡የግለሰባዊነት ፅንሰ ሃሳብ በአውሮፓ የዘመናዊ ፖለቲካ አስጀማሪ ከመሆኑም ባሻገር በተለይም “የጉዳት መርህ” ለብዙ የስነ-ህግ ፍልስፍናዎች መሠረት ሲሆን ደግሞ በስፋት ተቃውመውት ፅፈዋል፡፡ ሚል በጊዜው ሴቶ ከወንዶች እኩል የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ በማሰብ የአያሌ ሴቶችን ፊርማ አስባስቦ ለፖርላማው አቅዷል፡፡ 


ማኅበራሰባዊ ውል እና ግለሰባዊነት

በመንግስት የሚፈጠረው እና የሚፅናው በተፃፈም ሆነ ባልተፃፈ ማኅበረሰባዊ ውል አማካኝነት ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ውሉን የፈጠረው መንግስትም ሆነ ማኅበራዊ ውሉን ያፀደቀው ማኅበረሰብ ግን የተሠራው ከግለሰቦች ነው፡፡ በመሆኑም ውሉን ለማስፈፀም እና ማኅበረሰባዊ ደህንነትን እና ሰላምን ለማምጣት እሠራለሁ በሚለው መንግስትና በግለሰቡ መሃል ሁልጊዜም ቢሆን የማያቋርጥ ትግል አለ፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች ከእለታት በአንዱ ቀን ተነስተው ማኅረሰባዊ ውሉ አይመለከተኝም፤ አይገዛኝም እውቅናም ነፍጌዋለሁ፤ ውሉ ተቋርጦ በራሴ መርህ መመራት እፈልጋለሁ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ማኅበረሰቡ ሊደግፋቸው ወይም ሊቃወማቸው ይችላል፡፡ 

በዚህ ጊዜ መንግስታዊ ስልጣንን የያዙ ሰዎች አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በአንድ ወገን ማኅበረሰቡ ድህንነቴን፤ ሰላሜንና ብልፅግናዬን ያስጠብቅልኛል ብሎ ድምፁን ሰጥቷቸዋል፡፡ በሌላ ወገን ግለሰቡ ይህ የማኅበረሰቡ ሐሳብ በእኔ ነፃነት ላይ የተቃጣ ጥቃት በመሆኑ የሕዝቡን ሃሳብም ሆነ የመንግስታቱን ፖሊሲ እና ሕግጋት አልቀበልም ሊል ይችላል፡፡ ይህ ውጥረት በሰላም ወቅት በነፃ የሚዲያ ተቋማት እየተንፀባረቀ ሲቀጥል የከፋ ቀን ደግሞ አብዮት ወይም መፈንቅለ መንግስትን ሊወልድ ወይም ሊጠነስስ ይችላል፡፡ በመሆኑም ሕግ የእዚህ ውጥረት ማርገቢያ፤ ማንፀባረቂያ ወይም ማባባሻ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ጥሩ የሕግ አርቃቂዎች፤ አፅዳቂዎች፤ አመንጪዎች፤ ተርጓሚዎች፤ አስተማሪዎች እና ተመራማሪዎች በሁለቱ ወገን ያለው ውጥረት ሚዛኑ ተጣብቆ እንዲኖር ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ለዚህ ውጥረት ዕይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው “የፀረ ሽብር ሕግ” ነው የፀረ ሽብር ሕግ ዓለም ዓቀፋዊ በሆነ ደረጃ አከራካሪ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ የፀረ ሽብር ሕግ በተለምዶ የፖሊስ እና የድህንነት አካላት በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብን ከሚመረምሩበት እና ማስረጃ ከሚሰበስቡት መንገድ ለየት ባለ መልኩ ግዙፍ ስልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ የፖሊስ እና የደህንነት አካላት የግለሰቡን ስልክ፤ ኢ-ሜይል፤ የፅሁፍ ግንኙነቶች ያለግለሰቡ ፍቃድ ሊበረብሩ እና ሊመረምሩ ይችላሉ፡፡ በአንድ በኩል እነዚህ አካላት በማኅበረሰባዊ ውሉ አማካኝነት ሕዝቡ የጋራ ድህንነቱን ለማስጠበቅ የሰጣቸው ኃላፊነት አለ፤ በሌላ በኩል ግለሰቡ ነፃነቱን እና የግል ሚስጥሩን የመጠበቅ መብት አለው፡፡ 

የግለሰብ መብት ተከራካሪዎች ይህ በሕግ የተፈጠረ መንግስት የሚባል አካል ያለምንም ከልካይ በግለሰቦች ነፃነት ላይ እየተረማመደ  የሕዝቡን መብት አስጠብቃለሁ የሚል ከሆነ ቀስ ብሎ ደግሞ የማኅበረሰቡ መብት እና ነፃነት ሚጨፈልቅ አገዛዝ ሲፈጥር የሚያስጥለን አይኖርም ይላሉ፡፡ የማኅበረሰቡን የጋራ ጥቅም መጠበቅ አለበት በማለት የሚከራከሩ ደግሞ አንዳንዴ የጋር ጥቅምንና ደህንነትን ለማስጠበቅ የግለሰቡ መብት እና ነፃነት መስዋዓት ሊሆን ይችላል በማለት የጠቀሜታውያን የሞራል ፍልስፍና በማጣቀስ ይከራከራሉ፡፡ በአጠቃላይ መገንዘብ የሚኖርብን ጉዳይ ቢኖር ግን ውጤታማ የሕግ ስርዓቶች በእነዚህ ሁለት ፅንፎች መሃከል ያለውን ውጥረት ሚዛናዊ ሆኖ እንዲቀጥል የማያስችሉ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ 



ምዕራፍ ስምንት

ገሃዳዊ ስነ ሕግ

ገሃዳዊ ስነ ሕግ (Legal Realism) በመሠረቱ ወግ አጥባዊ የሕግ አስተምህሮን (Legal formalism) በመቃመወም የተጀመረ የሕግ ፍልስፍና ነው፡፡ ይህ ፍልስፍና ሕግ ከተፈጥሮ የሚገኝና የማይሻር ወይም ከፍተኛ ስልጣን ባላቸው ሉዓላዊ አካላት የተሰጠ ትእዛዝ መሆኑን አይቀበልም፡፡ በመሆኑም በመሠረታዊነት የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍናንም ሆነ የሕገ-ሰብ ፍልስፍና ይቃወማል፡፡ አስተምህሮው የአሜሪካ የስነ-ሕግ ፍልስፍና እና የሰካንዲኒቪያ የስነ- ሕግ ፍልስፍና በሚል በሁለት ንዑስ ክፍሎች ይከፍላል፡፡ 

በሃገረ-አሜሪካ ያለው የሕግ ስርዓት ሕግ የሚፈጠረው ፍርድ ቤቶች በሚሰጧቸው በኩር ውሳኔዎች አማካኝነት እንደሆነ ያስተምራል፡፡ እነዚህ በኩር ውሳኔዎች የስር እና አቻ ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ ጉዳይ ለሚሰጡት ውሳኔ ልክ እንደ ሕግ ተቆጥረው አስገዳጅ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የሃገረ አሜሪካ ፍርድ ቤቶች ሕግ ተርጓሚ ብቻ ሳይሆኑ ሕግ አውጪም ጭምር ናቸው፡፡ በመሆኑም የአሜሪካው ገሃዳዊ ስነ ሕግ በፍርድ ቤቶች ውሳኔ፤ በዳኞች የአመክንዩና ባህሪ ጉዳይ እንዲሁም በፍርድ ቤት የአሰራር ባህል ላይ ያተኮረ ፍልስፍና ነው፡፡ የዚህ አስተምህሮ ተከታዮች እንደሚሉት ሕግን የሚፈጥሩት ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ ሕግ ማለት ፓርላማው አፅድቆ የላከው ነጭ ወረቀት ሳይሆን ዳኞች እነዚህን ሕይወት አልባ የሕግ አንቀፆችን ከባለጉዳዮች ልዩ የሕይወት ሁኔታ ጋር አጣምረው ፍርድ ሲሰጡ የሚፈጠር ጉዳይ ነው፡፡ 

ስለሆነም ሕግ ከአንድ ሉአላዊ አካል ወይም ፓርላማ የሚሰጡትን ወይም በተፈጥሮ አማካኝነት በሰዎች ህሊና ውስጥ የታተመ የማይለወጥ እና የማይገረሰስ ጉዳይ እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጥር አይገባም፡፡ በዚህ ገሃዳዊ ስነ ሕግ ፍልስፍና ከሕገ ሰብ ፍልስፍና ጋር የሚጋራው ሃሳብ ሕግ ምንም አይነት ዲበአካላዊም ሆነ ተፈጥሮአዊ መሠረት የሌለው መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑን ሕግ ሰው ሰራሽ መሆኑን ይቀበላል፡፡ ይሁንና ሕግ ሰው ሰራሽ ቢሆንም የትኞቹ ሰዎች ይፈጥሩታል በሚለው ነጥብ ላይ ልዩነቱን ያስቀምጣል፡፡ 

የስነ ሕግ ፍልስፍና አራማጆች በአብዛኛው ዳኞች፤ ጠበቆች፤ የሕግ አስተማሪዎችና አርቃቂዎች ስለነበሩ ሕግ ሕይወት ኖሮት በውሳኔዎች ውስጥ የሚገለጥ መሆኑን ሙሉ ለሙሉ ይስማማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሕግንና የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ለማጥናት አንደኛው እና ዋነኛው መሠረታዊ ጉዳይ የዳኞችን ግለሰባዊ ባህሪ እና አቋም ማወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ዳኞች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በውሳኔዎቻቸው ውስጥ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ባህላዊ፤ሃይማኖታዊ እና ግለሰባዊ አቋሞች ያንፀባርቃሉ፡፡ በመሆኑ ከዳኞቹ የግል ባህሪ ተነስተን በአንድ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት ውሳኔ ሊሰጡ እንደሚችሉ መገመት እንችላለን፡፡ 

በተጨማሪም የሕግ ታሪክን ስናጠና የፍርድ ቤቶችን ታሪክን ማጠቃለል የማንችል ከሆነ ተሞክሯችን የተሳካ አይሆንም፡፡ ባጠቃላይ ዳኞች ውሳኔ ሲሰጡ ከውስጥም ሆነ ከውጪ በሚመነጩ ተፅዕኖች ውስጥ ሆነው መሆናቸውን በመገንዘብ የሚሰጡት ውሳኔ ግለሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ፋይዳ እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡ ይህ የሕግ ፍልስፍና ዳኛ ሠራሽ የሕግ ስርዓትን ለማይከተሉ ሃገሮች ብዙም ትርጉም ላይሰጥ ይችላል ምክንያቱም ለእነሱ ሕግ የሚፈጥረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንጂ ዳኛ ወይም ፍርድ ቤቶች አይደሉም፡፡ በመሆኑም በአንድ ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ፓርላማው ወይ አንዱ ሉዓላዊ አካል ካወጣው ህግ የሚያፈነግጥ መሆን የለበትም ዳኛ ሰራሽ ሕግ በሌለበት ሃገር ዳኛ ሕግ ይተረጉማል እንጂ ሕግ አይወጣም አይፈጥርም፡፡

 ሌላኛው ጠንካራ የገሃዳዊ ስነ ሕግ አቀንቃኝ ካርል ሌውለን ሲሆን ሰፋ ባለ መልኩ ሊተነትነው ሞክሯል፡፡ በ1931(እ.ኤ.አ) በፃፈው “some realism about realism” በሚለው መጣጥፍ የገሃዳዊ ስነ ሕግ መሰረታውያን የሟላቸውን ነጥቦች ሰይቷል፡፡ እነዚህም ፡- 1ኛ ሕግ ምንጊዜም ቢሆን በለውጥ ሂደት ላይ ነው 2ኛ ሕግ ወደ ግብ የሚያደርሰን መንገድ እንጂ በራሱ ግብ አይደለም 3. የማኅበረሰብ ለውጥ ከሕግ ለውጥ ይልቅ ይፈጥናል 4ኛ.“በሆነው” እና “ሊሆን በሚገባው” (ማለትም በሕግ እና ሞራል) መሃከል ያለው ልዩነት ጊዜያዊ እና ለህግ ጥናት ዓላማ ብቻ የሚውል ነው 5/ ህግጋት የስር የፍርድ ቤቶችን ስራ/ልምድ አይወሰኑም የሚል ጥርጣሬ ተገቢነት 6ኛ ጠቋሚ እና ገዳቢ ሕግጋት የፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ አናሳነት 7ኛ.የፍርድ ቤቶች ውጤቶችን ልዩ እና ጠባብ በሆኑ ከፍልስፍናዎች ማስቀመጥ 8ኛ ሕግን ሁልግዜም ቢሆን ከሚያመጣው ውጤት አንፃር መገምገም 9ኛ. ከላይ በተዘረዘሩት መርሆዎች የሕግ ጥናትን እና ልምምድን ለመቀየር ጥረት ማድረግ የሚሉት ናቸው፡፡ 

የሰከንዲኒቪያ የስነ- ሕግ ፍልስፍና ጀማሪ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሆነው ካርል አሊቨርኮና  1939 (እ.ኤ.አ) “Law as Fact” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ድርሳን የማኅበረሰባዊ የስነ- ህግ ጥናት (sociological Jurisprudence) አስጀማሪ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለእርሱ “ሕግ ማኅበረሰባዊ እውነታ” ነው “Law is nothing but a set of social facts” በመሆኑም ሕግ የሉዓላዊ አካል ትዕዛዙ አይደለም፤ ተፈጥሯዊ፤መንፈሳዊ ወይም ዲበ አካላዊ ይዘት እና ምንጭ የለውም፡፡ ሕግጋቱ በራሳቸው የቆሙ አስገዳጅነት ያላቸው አሀዶች  “Independent imperatives” ሆነው በዳኞች አእምሮ ውስት ከማኅበረሰባዊ እውነታ ጋር እየተጣጣሙ የሚተረጎሙ ናቸው፡፡ በመሆኑም ህግ በዜጎች አእምሮ ውስጥ ተፅዕኖ ሳያሳድር አስገዳጅነት እና ተቀባይነት የሌለው ከሆነ ዜጎች ምንጊዜም ቢሆን ቅጣት ሳይደርስባቸው ሕጉን የሚያመልጡበትን መንገድ እየፈለጉ ይኖራሉ ሲል ፅፏል፡፡

 

ፈላስፋው ዳኛ - ኦሊቨር ዌንደል ሆልምስ 

ሆልምስ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ከመሆኑ ባሻገር ለየት ባሉ ፍልስፍናዊ አቋሞቹ እስከዛሬ ሲወሳ ይኖራል፡፡ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዘጠኝ ደኞች ሲኖሩት ከሚሰጡት ውሳኔ ውስጥ የልዩነት ሃሳቦችን በተደጋጋሚ በማቅረቡ የተነሳ “ታላቁ ተቃዋሚ” (the great dissenter) በመባል እስከ መጠራት ደርሶ ነበር፡፡ በሃገረ- አሜሪካ የተመሠረተውን ገሃዳዊ ስነ- ህግ ከጠነሰሱት ሰዎች መሃከል ግንባር ቀዳሙ ሲሆን ከእርሱ ሌላ ብዙ ሰዎች አስፋፍተው ፅፈውበታል፡፡ ሆልምስ እንደሚለው “የሕግ ሕይወት በአመክንዩ ሳይሆን በልማድ የሚመራ ነው” ሕግ እና የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ደረቅ በሆነ የሕግ እና የአመክንዮ ሰንሰለት እና ቀመር እየተሰሉ የሚፈጠሩ ሳይሆን በወቅቱ ያለው ጠንካራ ማኅበረሰባዊ እና መንግስታዊ ገዢ ሃሳብ ውጤት መሆን አለባቸው፡፡ ይሀ ልንክደው የማንችለው ሃቅ በመሆኑ ዳኞች በዚህ ማኅበረሰባዊ ወይም መንግስታዊ ገዢ ሃሳብ ስር አውቀውም ሆነ ሳያውቁት ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ 

ዳኞች ይህን የማያደርጉ ቢሆን እንኳ አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ራሳቸው በፈጠሩት ግላዊ ተፅዕኖና ሃሳብ ስር የሚወድቁ በመሆኑ በዕውቀት የዚህ ገዢ ሃሳብ ፈፃሚ መሆን አለባቸው፡፡ መንግስታዊ እና ማኅበረሰባዊ ገዢ ሃሳብ የምንለው ማኅበረሰቡ በወቅቱ የያዘው የሞራል መርህ፤ መንግስት ያቀደው እና የሚያስፈመው ፖሊስ ወይም ለሕዝቡ አንገብጋቢ የሆነ ጉዳዮችን የሚያካትት ነው፡፡ በመሆኑም ዳኛ ውሳኔ ሲፅፍ የምመራው በሕግ እና አመክንዩ ብቻ እንጂ በሌላ ገዢ ሃሳብ አይደለም ማለት የለበትም፤ ምክንያቱን “ሕግ ማለት የፍርድ ቤቶች የዕለት ተዕለት ተግባር ነው” በመሆኑም ፍ/ቤቶች የህግጋዥ ሃሳብ ውጥን ይሳካ ዘንድ በውሳኔያቸው ከመደገፍ አንስቶ ውሳኔያዊ ተአቅቦ  እስከ ማድረግ መሄድ አለባቸው በማለት ተከራክሯል፡፡

የህግ ጥርጣሬ - ፍራንክ ዥሮም

በሃገረ- አሜሪካ በሕግ ሙያን ይተዳደር የነበረው ፍራንክ ዥሮም አብዛኛውን ጊዜ በገሃዳዊ ስነ- ህግ አቀንቀኞች እና በሌሎችም ግለሰቦች የሚታወቀው “ሕግ ማለት ዳኛው ቁርሱን የበላው ነገር ነው” በሚለው አባባሉ ነው ፡፡ ፍራንክ ዥሮም የገሃዳዊ ስነ-ሕግ አቀንቃኞችን በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ ቀዳሚዎቹ የህግ /Rule skeptics) ተጠራጣሪዎች ሲሆኑ ሌሎቹ የፍሬ ነገር (fact skeptics) ተጠራጣሪዎች ይባላሉ፡፡ የህግ ተጠራጣሪዎቹ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች የሚጠቀሟቸው ሕግጋት ግልፅነት የጎደላቸው እና ግራ የሚያጋቡ እንደሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ እነሱም በበኩላቸው ሕግጋት ለሁለት ይከፍሏቸዋል፡፡ የወረቀት ሕግጋት እና እውነተኛ ሕግጋት፡፡ የወረቀት ሕግጋት በህግ አውጪ አካል የሚሠጡ ሲሆኑ እውነተኞቹ ሕግጋት ግን ያልተፃፉ እና የዳኛውን ህሊና የሚለውጡ ሲሆኑ እውነተኛ፤ ተገማች እና ወጥነት ያላቸው እንዲሆኑ እነዚህ ያልተፃፉ ሕግጋት መታወቅና መጠናት ይኖርባቸዋል፡፡

 የፍሬ ነገር ተጠራጣሪዎች በበኩላቸው በስር ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ ያተኩራሉ፡፡ በእነሱ አመለካከት ዳኞች የሠው እና የሠነድ ማስረጃዎችን ከመረመሩ በኃላ ተገቢውን ሕግ መምረጥ ሲገባቸው ምስክር እየተሰማ ወይም የሰነድ ማስረጃዎችን እየሚመረምሩ አስቀድመው ለመረጡት የሕግ ማዕቀፍ ይስማማል በሚሉት መልኩ በመሆኑ ማስረጃው ከአድሎ በፀዳ መልኩ መመዘኑ አጣራጣሪ ይሆናል፡፡

 የስር ፍርድ ቤት ዳኖች “ቅድመ ውሳኔ” ላይ እንዲደርሱ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች የሚታወቁና የማይታወቁ ሲሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ዳኞች ምስክር የሚሰሙበት ወቅት የምስክሩ ልዩ ባህሪ፣ መልክ፣ የንግግር ዘይቤ በሚሰጠው ምስክርነት ላይ ያላቸውን አመኔታ ሊቀንሰው ይችላል፡፡ በተያያዘም የባለጉዳዩ ባህሪ፤ ግለ ታሪክ፤ አሳዛኝነት እና መሰል ሁኔታዎች ከዳኛው ቅድመ ታሪክ ጋር በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መልኩ ተገናኝቶ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚሠጠው ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ 

ማህበረሰባዊ ምህንድስና - ሮስኮ ፓውንድ

በገሃዳዊ ስነ ሕግ ጥላ ሰር በንዑስ ርዕሰነት ፓውንድን ያስቀመጥነው ምንም እንኳ በኃላ ላይ ራሱን ከገሃዳዊ ስነ-ሕግ እንቅስቃሴ የነጠለ ቢሆንም የገሃዳዊ ስነሕግ ጠንሳሽ የሚባል ሰው ስለነበር ነው፡፡ ፓውንድ በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ አስተምሯል፤ የሕግ ትምህርት ቤቱ ዲንም በመሆን አገልግሏል፡፡ ፓውንድ ሕግ የማኅበረሰባዊ ምህንድስና (Social engineering) መሣሪያ እንደሆነ ያምን ነበር፡፡ ሕግጋት ሲወጡ እና ሲተገበሩ አንድ የተለየ ማኅበረሰባዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ተደርጎ መቀረፅ ይኖርባቸዋል ሲል አስተምሯል፡፡ ከዚህም የተነሳ (Sociological Jurisprudence) ቤተ አስተምህሮ አስጀማሪ እንደሆነ ተደርጎ ይወሳል፡፡

 በርግጥ ከገሃዳዊ ስነሕግ እንቅስቃሴ እንዲርቅ ካደረጉት ምክንያቶች አንደኛው ከተዋቂው የገሃዳዊ ስነሕግ አቀንቃኝ ካርል ሌውሊን( Kar LLewiyn) ጋር በተለዋወጠው የፅሑፍ ኃይለ-ቃል አማካኝነት ባሳደረው ቂመኝነት እና ፍራንክሊን ዲ-ሩሰቬልት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛችን ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አስራ አምስት ከፍ ለማድረግ የፍ/ቤቱን ውሳኔዎች ለ New Deal እንቅስቃሴ ተገዢ እንዲሆኑ ለማድረግ ያደረገውን ጥረት በመቃወም ነበር፡፡ 

ምንም እንኳ ፓውንድ የ  New Deal እንቅስቃሴ ደጋፊ የነበረና የእርሱ ፍልስፍናዎችም ለሩዝቬልት እንቅስቃሴዎች መሠረት እንደነበሩ ቢነገርም መጨረሻቸው አላማረም፡፡ ፖውንድ የሕግን ወግአጥባቂነት (Legal formalism) ማለት ሕግጋት የማይቀየሩና የማይለወጡ ስለሆኑ ሊነኩ አይገባም የሚለውን አስተሳሰብ የሚተች ሲሆን ሕግጋቱ የማኅበረሰቡን ሕይወት እና አንገብጋቢ ችግሮች ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መራቀቅ እና መተርጎም እንደሚኖርባቸው እና የሕግ ጥናት እና የማኅበረሰብ ጥናት እጅና ጓንት ሆነው ካልሄዱ የሚፈለገውን የፍትህ ደረጃ ማምጣት እንደማይቻል በሰፊው ፅፏል፡፡

 ሮስኮ ፓውንድ የገሃዳዊ ስነሕግ ጠንሳሽ ተደርጎ ቢወሰድም ከካርል ሌውሊን ጋር ያደረገው ሙግት ከምሁራዊ ጥናት ዳሰሳ ተገልሎ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ በ 1931 (እ.ኤ.አ) ሴውሊን በፃፈው እና ቀደም ብሎ በተጠቀሰው መጣጥፍ የገሃዳዊ ስነ-ሕግ ምሁራን ብሎ ከዘረዘራቸው ሰዎች መሃከል ሮስኮ ፓውንድን ሊያካትተው አልፈቀደም፡፡ ፓውንድ ግን በሃገረ አሜሪካ በ1920ዎቹና 1930ቹ ከተነሱት ወጣት የገሃዳዊ ስነሕግ ምሁራን በዕድሜ ገፋ ያለ ከመሆኑም ባሻገር ቀደም ብሎ የሕግ ወግ አጥባቂነትን (Legal formalism) ተችቷል፡፡ በሁለቱ መሃከል ያለው ፀብ ግላዊ ቢሆንም ሁለት የተለያዩ የህግ ፍልስፍናዎች እንዲበለፅጉ ምክንያት ሆኗል፡፡ 

ሌውሊን በ1931 (እ.ኤ.አ) “Some realism about realism በሚል የፃፈው ፅሑፍ በቀጥታ ለሮስኮ ፓውንድ የተፃፈ ነው፡፡ ምክንያቱም ፓውንድ ቀደም ብሎ በፃፈው ፅሑፍ ካርልሌውሊን እና ፍራንክ ዥሮሞ የሚጠቀሙት ቃል እና ፅንፈኛ አቋማቸውን በመተቸት ፅፏል፡፡ ለዚህ ምክንያት የሆነው ካርልሌውሊን ጋር አብረው እንዲሠሩ በኮሚሽን በወሰዱት ስራ ሊስማሙ አለመቻላቸው ነው፡፡ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ በሁለት ምሁራን መሃከል የተነሳው የግል ፀብ ሁለት ተቃራኒ የሚመሰሉ ቤተ-አስተምህሮዎች እንዲፈጠሩ ሰበብ ሊሆን ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ገሃዳዊ ስነ-ሕግ እና ማኅበረሰባዊ ስነ ሕግን ቀረብ ብለን ስንፈትሻቸው ከሚለያቸው ይልቅ የሚያቀራርባቸው ጉዳይ እጅግ ብዙ ነው፡፡

 ሁለቱም ሕግ ከዲበአካላዊ እና ሞራላዊ ይዘት መላቀቅ እንዳለባቸው ይገልፃሉ፤ ሁለቱም ሕግ መንገድ እንጂ ግብ እንዳልሆነም ይቀበላሉ፡፡ ካርልሌውሊ እና ሮስኮፓውንድ ከዓመታት በኃላ የነበረባቸውን ፀብ አስወግደው በጋራ ብዙ ስራዎችን አበርክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች አሁንም ቢሆን የገሃዳዊ ስነ-ሕግ የመንፈስ አባት አድርገው የሚወስዱት ኦሊቨርዌንዴል ሆልሞስን እንጂ ሮስኮፓውንድን ያለመሆኑ በሁለቱ መሃከል የነበረው ፀብ ምክንያት እንደነበር ይገልፃሉ፡፡ 




ምዕራፍ ዘጠኝ

ነቂሳዊ የህግ ፍልስፍና

ይህ ፍልስፍና የተለያዩ የሕግ አስተምህሮዎችን ያቀፈ ቤተ አስተምህሮ ነው፡፡ ነቂሳዊ የህግ ፍልስፍና (Critical legal theory) የጀመረው በ1970ቹ (እ.ኤ.አ) በሀገረ-አሜሪካ ሲሆን አጠቃላይ ሀሳቡም የሕግ ስርዓቱ ታሪካዊ ሂደት በግልፅ እና በአፅንኦት ያልተመረመረ በመሆኑ በአንዳንድ ሕዳጣን የማኅበረሰብ ክፍሎች የመገለል እና የመገፋት ሰሜትን የሚያሳድር ነው፡፡ በመሆኑም በታሪክ ውስጥ የፍትሕ ስርዓቱ በእነዚህ የኅበረተሰብ ክፍሎች ላይ ያሳደረውን ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ በማጥናት ለህዝብ ግልፅ መሆኑ መንገዶች በማሳተም የንቀተ ህሊና ደረጃን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ የዚህ አስተምህሮ የመንፈስ ወላጅ ገሃዳዊ የሕግ አስተሳሰብ (Legal Realism) እንደሆነ ይታሰባል ይሁንና የዚህ ፍልስፍና አራማጆች በ1970 እና 60ቹ በጥቁሮች መብት አንቅስቃሴ፤ በሴቶች መብት እንቅስቃሴ እና የፀረ-ቬትናም ጦርነት እንቅስቃሴ ሳቢያ የተወለዱ ናቸው፡፡ 

በሕግ እና በፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም መሃከል ቀጥተኛ እና ያፈጠጠ ውህደት እያለ ያንን በመካድ የሕግ ስርዓቱን ማስቀጠል ተገቢነት የለውም፤ በስልጣን እና በሕግ አተረጓጎም እና ማርቀቅ መሃከል ያለው ግንኑነት በታሪክ ውስጥ ተገቢውን ስፍራ ላላገኙ እንደ ጥቁሮች ሴቶች፤ ድሃ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት በማለት ተከራክረዋል፡፡ በመሆንም በዚህ አስተምሮ ስር የሚታቀፉ ምሁራን የራሳቸውን ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ የሚፈጥሩ ሳይሆኑ ከእነሱ ቀድሞ የተፈጠረን የሕግ አሰራር እና ጥናት የሚነቅሉ፤ የሚተቹ እና የሚፈትሹ በመሆናቸው አጠቃላይ አስተሳሰባቸው ይህ ነው ብሎ ለመበየን አዳጋች ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ የጋራ የሆኑ ነጥቦች እንደሚያግባቧቸው መገመት አያዳግትም፡፡ ለምሳሌ ያህል ሕግ አንዳንዴ ግልፅነት የጎደለው እና አጣራጣሪ እንደሚሆን ይህም በሚፈጠረው በሕጉ ውስጥ ባሉ ክፍተቶች እና ተቃራኒዎች መሆኑ ለሁሉም የአፅንዖተ ሕግ አሳቢዎች የሚጋሩት ነው፡፡ ሌላኛው ሕጉ አንዳንድ የኅበረተሰብ ክፍሎችን እኩል የማያስተናግድ በመሆኑ ግልፅ ያልሆነና የሆነ አድልዎ ያዘለ ነው በዚህም ምክንያት ለእነዚህ ወገኖች ስልጣናቸውን እና የበላይነታቸውን የሚያስጠብቁበት መሣሪያ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ከዚያም በላይ ሕጉ የተራቀቀበት ዓላማ እና ግብዓታዊ ያልሆነ እና የተወሳሰበ በመሆኑ የህንኑ ማጥራት (Demystify)ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ይህ አስተምህሮ ረዥም ለሚባል ዘመን በአውሮፓ እና አሜሪካ ባሉ የፍትህ ስርዓቶች ላይ ያለ ማቋረጥ ብዙ ትችቶን ያቀረበ በመሆኑ አንዳንዶች እንደ አፈንጋጮችና ሰርዓት አልባኞ ሊፈረጇቸው ችለዋል፡፡ ሆኖም በዓለም የፍትህ፤ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ምህዳር ያለ ያሳረፉት ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ 




ድህረ- ዘመናዊነት እና ሕግ

ድህረ- ዘመናዊነት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማለቂያ አካባቢ በተለያየ ፈላስፎች፤ ተመራማሪዎች እና የንባብ ሰዎች በተለያየ መልክ እና ቋንቋ እየተገለፀ እዚህ የደረሰ አስተሳሰብ ነው፡፡ ድህረ-ዘመናዊነት ከዘመናዊነት ቀጥሎ ያለ ዘመንን እና ሥርዓትን የሚወክል ቃል ነው፡፡ ዘመናዊነት የሰው ልጅ ከመሃከለኛው ዘመን ጨለማ በጠንካራ አመክንዩ፤ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተላቅቆ በመውጣት የፈጠረውን ወቅት ይወክላል፡፡ ዘመናዊነት (Modernity) በፍልስፍናዊ ፅነሰ ሃሳብነት ሲመረመር የሳይንስ እና የምክንያታዊነት ፍጹማዊ ገናናነትን ይወክላል፤ ከዘመነ አብርሆት (Enlightenment) ጊዜ ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣው ይህ የሳይንስ እና የአመክንዩ ገናናነት ለአንዳንድ የስነ ጥበብ እና የሳይንስ ተመራማሪዎች ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ 

ለምሳሌ በማኅበረሰባዊም ሆነ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች መሃከል እና ውስጥ ያለው ድንበር ጠንካራነት እና አይነኬነት እና የአንዳንድ ቀመሮች፤ መርሆች፤ ንድፈ ሃሳቦች፤ ሕጎች እና አስተምሮዎች አይዳፈሬነት ለብዙ ሰዎች የሚያጠግብ ሊሆን አልቻለም፡፡ በመሆኑም ብዙ ተመራማሪዎች የስነጥበብ ሰዎች፤ ምሁራን ከተለመደው “ሳይንሳዊ” እና “ምክንያታዊ” ማዕቀፎች ሆነ ብለው በማፈንገጥ የራሳቸው ስነ ጥበባዊ እና ሳይንሳዊ ሃሳቦችን ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ይህ አፈንጋጭነት በሕግ፤ በሳይንስ፤ በስዕል፤በሙዚቃ፤ በስነ-መለኮት እና በፍልስፍና መታየት ሲጀመር ሰዎች በተለያዩ ዘርፎች ያሉትን እነዚህን መሰል አካሄደች የድህረ-ዘመናዊነት ውጤት ሲሉ ሰይመዋቸዋል፡፡ 

በመሆኑም ድህረ-ዘመናዊነት በአፍራሽነት (Deconstructionism) እና በአንፃራዊነት (Relativism) ይወክላል፡፡ አፍራሽነት ቀደሞ ሲል የጠቀስናቸውን የአስተሳሰብ ዘርፎች ድንበር እና ልዩ ልዩ መርሆችን ገናናነት ማፍረስ እንደሚገባ ሲያስረዳ እንደ ጃኪውስ ዲራይዳ አይነት ፈላስፎች በብዛት እንዳስፋፉት ይገልፃል፡፡ አንፃራዊነት በበኩሉ በእነዚህ ድንበሮች መሃከል ያለው ልዩነት ከፈረሰ እውነትን ፍፁማዊ በሆነ መንገድ ማግኘት አንችልም፤ ፍፃማዊ እውነት (Objective truth) የሚባለው ተምኔታዊ የሆነ የማይጨበጥ ቅዥት እንደሆነ ያስተማራል፡፡ ይህ ሰፊ የሆነ አስተሳሰብ ለሁሉም የትምህርት ዘርፎች ውስጥ ሰርፆ እንደገባው ሁሉ በሕግ ጥናት እና ምርምር ውስጥ ሰርፆ ገብቷል፡፡ 

ሕግ ሲረቀቅ እና ሲፀድቅ ከዚህ በፊት ተስፋፍተው በነበሩ ቅድመ ዕውቀቶች ሳቢያ የሚታወቁ እና የሚገመቱ ሂደቶችን ያልፋል ሕግ ሆኖ ከታወጀም በኃላ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ሲተረጎም በማኅበረሰቡ ውስጥ ከነበሩ እና በጥልቀት ከሰረፀ እሳቤዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ማኅበረሰባዊ አይነኬ እሴቶች መንግስታዊ አሰራሮች ከሌላ ዕይታ ተመልክተን ሕጉን ልንተገብረው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ድህረ-ዘመናዊ ፍልስፍና ዘር-ተኮር የሕግ አስተምህሮ፤ “ሴታዊ” የሕግ አስተምህሮ፤ የብዝሃ- ሕግ ፍልስፍና፤ እና መሰል የሕግ አስተማህሮዎች እንዲነቃቁ እና እንዲነሱ ከፍተኛ የፍልስፍና ድጋፍ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ ያህል ዘር-ተኮር የሕግ አስተምህሮ (Racial legal theory) በሃገረ- አሜሪካ ውስጥ ሲያብብ የሃገሪቱ ሕግ በነጮች እና በጥቁሮች መሃከል የተዛባ ግንኙነት እንዲኖር በሚታወቁ እና በማይታወቁ መስኮች ጥቁሮችን እየበደለ ይገኛል በሚል የተነሳውን የአስተምህሮ በአብዛኛው ድህረ-ዘመናዊ የፍልስፍና ድጋፍ ያለው ነበር፡፡ ድህረ-ዘመናዊነት ዛሬም ቢሆን በሕግ ስርዓቱ ውስጥ በልማድ ተይዘው ያሉ አስተሳሰቦችን እና የማይደፈሩ ድንበሮችን ለማፍረሰ አዲስ ሕግጋት እና አሠራሮች እንዲመነጩ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ 

ጆርገን ሃበርማስ- የግንኙነት መርህ

      ሃበርማስ ጀርመናዊ የፍልስፍና እና የኅብረተሰብ ጥናት ተመራማሪ የነበረ ሲሆን የፍራንክፈርት ቤተ አስተምህሮ ተከታይ ነበር፡፡ ሃበርማስ “The Theory of communicative Action” እና “Between Facts and Norms” የተባሉ ሁለት ድርሳናት ሲያዘጋጅ ስለ ሕግ እና ማኅበረሰብ መስተጋብር ሰፊ ደሰሳ አስቀምጧል፡፡ ለሃበርማስ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ቀጣይነት ያለው እና የተረጋጋ ስርዓት ለመፍጠር የማያቋርጥ ግለሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በአመክንዩ በሚመሩ ዜጎች መሃከል የሚደረገው የተናጥል እና የጋራ ውይይት ቀስ በቀስ ወደ አንድ የጋራ መግባባት ያደርሳል፡፡

 ይህ የጋራ መግባባት የሚፈጥረው ማኅበረሰባዊ ሞራል የስነ-ሕግ ዋነኛ አጀንዳ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን በተደጋጋሚ የሚደረገው ይህ የግለሰብ ከግለሰብ እና የማኅበረሰብ - ከማኅበረሰብ ውይይት አንዳች ገዥ ሃሳብ ወይም ተፅዕኖ ይፈጥራል፤ ይህ ገዢ ሀሳብ ወይም ተፅዕኖ ደግሞ የግንኙነት ሳይንስ ይወልዳል፤ ይህ ግንኙነት ኃይል በተራው በምርጫ በዲሞክራሲያዊ እየታገዘ  እና  እየተመራ አስተዳደራዊ ኃይል ይሆናል፡፡ ከማኅበረሰባዊ ውይይት የተለያ የግንኙነት ደረጃዎችን አልፎ የተፈጠረው ሕግ ህዝባዊ ቅብልነት ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ሕግ በማኅበረተሰብ መሃከል የውህደት እና የተግባቦት መሣሪያ በመሆን ሊያገለግል ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም የሕገሰብ ፍልስፍና ሕግን ከቅጣት እና ትዕዛዝ ጋር ብቻ ሲያገናኘው የተፈጥሮ ሕግ ፍልስፍና ደግሞ ሕግን ከልዕላ ሰባዊ የሞራል ምንጭ ጋር ያይዘዋል፤ ይሁን እንጂ ሁለቱም ሕግ በዕለት ተዕለት የሰዎች የተግባቦት ሕይወት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ቦታ አልሰጡትም፡፤ ሃበርማስ በሌሎች የማኅበረሰበ ሳይንስ አስተምህሮዎች የሚታወቀው “የግንኙነት መርህ” (Discourse principle) የሚለውን አስተምህሮ በማስገኘቱ ነው፡፡ 

ለሃበርማስ አንድ ድርጊት ወይም ሕጋዊነት የሚኖረው በድርጊቱ ወይ በመመሪያ ተፅእኖ የሚደርስባቸው ሰዎች በውሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ምክንያትም በሆነ ውይይት ከተቀበሉት ብቻ ነው፡፤ ይህ እንደሚታወቀው የሕጋዊነት እና የቅቡልነት ጥያቄ እንደመሆኑ አንድ የሕግ ስርዓት የሚያሳየውን የአሳታፊነት እና የአካተችነት ደረጃ ይመረምራል ምክንያቱም የሰው ልጅ ቋንቋ ይመረምራል፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ቋንቋ በመሠረቱ ትርጉም ያለው ሀሳብ ያዘለ በመሆኑ በውይይት ሁሉ ውስጥ “የተግባቦት አመክንዩ” (Communicative reason) አለ፡፡ ይህ የተግባቦት አመክንዩ እንዲዳብር ደግሞ “ሕዝባዊ መድረክ” (Public space) ያስፈልጋል፡፡ 

ይህ “ሕዝባዊ መድረክ” አካላዊ ሳይሆን ሃሳባዊ ነው፡፡ በፊዩውዳላዊ ስርዓት የባህል ባህሪ የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ የከለከለ እንደመሆኑ “የውክልና ባህል” ልንለው እንችላለን ምክንያቱም ነገስታቱ እና መሳፍንቱ የሕዝቡን ባህል የሚቀርፁና የሚመሩ ነበሩ፤ ይሁን እንጂ የካፒታሊስቱ ስርዓት የፊውዳላዊውን ስርዓት ሲተካው ይህ የውክልና ባህል ተረስቶ አዲስ “ሕዝባዊ መድረክ” ተፈጠረ፡፡ ይህ መድረክ ሀሳባዊ እንደመሆኑ በጋዜጦች፤ መፅሄቶች፤ የውይይት  እና የመፃህፍት ክበብ በልዩ ክበቦች እና ማኅበሮች እንዲሁም ካፌዎች ሊወክል ይችላል፡፡ እነዚህ በሙሉ ለሕዝቡ የውይይት መድረክ በመሆን አገልግላዋል፡፡ በመሆኑም ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ “ሕዝባዊ መድረክ” መንግስት የማይቆጣጠረው የተፅዕኖ ማዕከል ሆነ፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ያነሳነው ማህበረሰባዊ ውይይት (public Discourse) እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መፈጠር እንዳለበት ሃበርማስ አበክሮ ገልፆል፡፡ 

ሃበርማስ ተግባራዊ ተግባቦት በሚለው ፍፃማዊ እና ምናባዊ ግንኙነት ወቅት ሰዎች በእኩልነት እና በቅንነት የሚግባቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በተለምዶ የሰዎች ግንኙነት በስልጣን ግንኙነታቸው ጥላ ስር የወደቁ በመሆኑ ነፃ እና ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ተማሪ እና ሌክቸረር በአንድ ፅንስ- ሃሳብ ላይ ክፍል ውስጥ ተማሪዎች ፊት ቢከራከሩ ወይም ደግሞ አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር እና የጨረቃ ቤት በቅርቡ በዚያው ቀበሌ የሠራ ሰው ሲነጋገሩ ንግግራቸውን ያሉበት የስልጣን ከፍታ እና ዝቅታ ጫና ስለሚያሳድርበት ነፃ አይሆንም፡፡ በመሆኑም በሕግና ማኅበራዊ ውል ስሪት ወቅትም ተዋዋይ ወገኖች በእኩልነት ላይ በተመሠረተ ተግባራዊ ተግባቦት (Communicative action) መሠረት በማኅበራዊ ውሉ ወይም በሚወጣው የመንግስት ሕግ የሚያገኙት እና የሚፈጠርላቸው መብትን አስመልክቶ በሚደረግ ውይይት በእኩልነት የማሳተፍ መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

 ይህም ማለት መብት በሕግ ሲፈጠርላቸውም ቢሆን ይህንኑ መብት እንደያዙ ወይም እንዳላቸው ተደርጎ መታሰብ ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም ብዙ ሰዎች ሃበርማስ የጀንሎክን ሰዎች ከማኅበረሰባዊ ውል በፊትም ቢሆን የሕይወት እና ነጻነት መብት አላቸው የሚለው እሳቤ እና የነሱን ዜጎች ማኅበረሰባዊ ውል ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ምንም ዓይነት መብት የሌላቸው እና መብታቸው በማኅበረሰባዊ ውሉ ተፈጥሯል የሚሉት አስተሳሰቦች ያዛመዳቸው እና የቀላቀላቸው መሆኑን እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም ሃበርማስ እንደሚለው የሕግ መብቶቹ ፈጣሪዎች ራሳቸው የመብቶቹ ባለቤቶች ተደርገው መታሰብ ይኖርበታል፤ በዚህም የህግ መብቶች የመፈጠሩ ጉዳይ በመሠረታዊነት የተዋዋይ ወገኖቹ የፖለቲካዊ ውሳኔ ውጤት መሆኑን ያመለክታል፡፡ 

ሴት-ተኮር የሕግ ፍልስፍና

በዓለማችን ላይ ያሉ ማኅበረሰቦች ከቅድመ ታሪክ ዘመን ጀምሮ አመሠራረታቸው እና ውስጣዊ ውቅራቸው ቢጠና በአብዛኛውና በመሠረታዊነት የተቋቋሙት በአባታዊ (Patriarchal) ጥላ ስር ነው፡፡ አባታዊ የሆነው የማኅበረሰብ አመሠራረት ለወንዶች በቤተሰብ፤ በሕዝብ አስተዳደር፤ በሐይማኖት ተቋማት፤ በትምህርት እና መሰል የማኅበረሰብ መስፈርቶች እና ዘርፎች ቅድሚያ እና ከፍተኛ ቦታ የሚሠጥ ነው፡፡

 ይህ ወንድ-መር የኅበረተሰብ አወቃቀር በታሪክ ውስጥ አልፎ አልፎ በሚነሱ ጠንካራ ሴቶች ውግዘት እና ትግል ቢገጥመውም እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በተደራጀ መልኩ ሁሉን አቀፍ ውግዘት እና ተቃውሞ አልገጠመውም ነበር፡፤ ይህን ትግል የመሩት ሰዎች በተለምዶ አቃፊ ሊባል በሚችል ሴት-ተኮር አስተምህሮ (Feminism) ስያሜ ስር ይጠቃለላሉ፡፡ ይህ አስተምህሮ ሴቶች በሁሉም እና ማንኛውም መስክ ከወንዶች እኩል እንደሆኑና በሁሉም ረገድ እኩል የሃብት የትምህርት እና የስልጣን ድርሻ ሊያገኙ እንደሚገባ፤ ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ የደረሰባቸው ኃላቀርነትም በተጨማሪ ዕድል ሊስተካከል እንደሚገባ ያስተምራል፡፡

 የሴት- ተኮር የህግ ፍልስፍናም በወንዶች እና ሴቶች መሃከል ያለው የተዛባ እና ኢፍትሃዊ የሆነ ግንኙነት በመንግሥት ሕግጋት ውስጥ የሚንፀባረቅ በመሆኑ የፍትህ ስርዓቱን ከአድሎ እና ኢፍትሐዊነት በማፅዳት ለወንዶች እና ሴቶች እኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሕግጋት እንዲወጡ ሊደረግ ይገባል በማለት ይከራከራል፡፡ ፍ/ቤቶችም ህግጋትን በሚተረጉሙበት እና ውሳኔ በሚሠጡበት ወቅት በወንዶች እና በሴቶች መሃከል በታሪክ ውስጥ ያለውን የተዛባ ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሴቶችን ጥቅም ከግምት ውስጥ በሚያስገባ መልኩ መሆን አለበት፡፡ 

በዚህ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ ውስጥ ይህንኑ “ሴታዊ” ፍልስፍና እያራመዱም ቢሆን ከሌሎች ተመሳሳይ ፍልስፍና አራማጆች ጋር የማይግባቡ ሴቶች ይኖራሉ፡፡ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ግን የተለዩ (Equal but different) እንደሆኑ የሚያቀነቅኑ ሴቶች እንዳሉ ሁሉ ሴቶች በሁሉ ነገር ከወንዶች ጋር እኩል ናቸው (sameness theory) የሚለውን ሃሳብ የሚያቀነቅኑ ሴቶች አሉ፡፡ አባታዊ ስርዓት (Patriarchy) ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ አዲስ የቤተሰብ እና የማኅበረሰብ አወቃቀር ዘይቤ መከተል አለብን የሚሉት እንዳሉ ሁሉ አባታዊ ስርዓትን ማፍረስ ሳይሆን ማሻሻል ይገባናል የሚሉም አሉ፡፡

 ይህ በዋናው የሴት-ተኮር ፍልስፍና ላይ የሚታይ ልዩነት በሕግ ፍልስፍናውም ላይ ይንፀባረቃል፡፡ የሴት- ተኮር ፍልስፍና በአብዛኛው “ባደጉት” ምዕራባዊ ሃገራት ውስጥ የሚራመድ እና የተፈጠረ እንደመሆኑ የሴቶችን እና የማኅበረሰብን ግንኙነት የሚያየው ከተማረች ነጭ ምዕራባዊ ሴት አንጻር ብቻ እንደሆነና እያደጉ ባሉ ሃገራት ውስጥ ያለውን ባህል ከግምት ውስጥ አያስገባም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጭቆና ተመሳሳይ እንደሆነና በዓለም ላይ ባሉ ሴቶች በሙሉ ተቀባይነት የሚያገኙ እና የሁሉንም ሴቶች በደል የሚያጎሉ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንደሚቻልም የሚከራከሩ አሉ፡፡  ይህ ልዩነት ቢኖርም ሁሉም ሴታዊትነትን የሚያቀነቅኑ ሰዎች የሚስማሙበት ነገር ቢኖር አሁን ባለው እና በሚመጣው ሰርዓት ሴቶች እና ወንዶች የእኩል ዕድል ተጠቃሚ ሊሆኑ የተገባቸው መሆኑን ነው፡፡ 

















ምዕራፍ ስምንት

ልዩ ልዩ የህግ ፍልስፍናዎች አህጽሮት

1 የአማኑኤል ካንት የሕግ ፍልስፍና

ታላቁ የጀርመን ፈላስፋ አማኑኤል ካንት  የሚታወቀው በዲበአካላዊነት እና በሞራል ፍልስፍናው ቢሆንም ከዚሁ በተጨማሪ ስለ ሕግ እና የሞራል እሳቤዎ ልዩነት በሰፊው ፅፏል፡፡ ካንት ማኅበረሰባዊ ድንጋጌዎችን በሁለት ይከፈላቸዋል፡፡ የሕግ ድንጋጌዎች እና ሞራላዊ ድንጋጌዎች የሚባሉት ናቸው፡፡ ሞራላዊ ድንጋጌ አንድን ድርጊት አስገዳጅ የሚያደርገው ከአድራጊው ምክንያተ- ድርጊት (Motive) የሚሰጠው ምክንያት ወጪያዊ ግዴታ ሳይሆን ፍላጎትን ሲሆን ነው፤ ምክንያቱም ሰዎች በሞራል ተነሳስተው አንድን ድርጊት የሚያደርጉት ተገደው ሳይሆን ፈልገው ነው፡፡

 ከዚሁ በተቃራኒ የሕግ ድንጋጌዎች (Legal legislations) ላይ የተመረኮዘ ድርጊት ምክንያት የሚያደርገው ፍላጎት ሳይሆን ቅጣትን ነው፡፡ በመሆኑም ይህ በሕግና ሞራል መሃከል ያለው ልዩነት መሠረት የሚያደርገው ምክንያተ- ድርጊትን (Motive) የሕግ ምክንያተ ድርጊት ቅጣት ሲሆን የሞራል ግን የራስ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ አጠቃላይ ከሆነ መስፈርት በተጨማሪም እንድ የሕግ ስርዓት ሊያሟላ ይገባቸዋል የሚላቸውን ምክንያቶ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ሕግጋት ማለትም ካላይ የሕግ ድንጋጌዎች (Legal legislation) ያልናቸው በቅድሚያ ታሳቢ የሚያደርጉት በሁለት ሰዎች መሃከል ያለን ተነጻጻሪ የሕግ ግዴታን መሆን አለበት ይህ ተነፃፃሪ የሕግ ግዴታ ከውል ወይም ከሕግ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የውል ሰጪና ውል ተቀባይ ወይም የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ነው፡፡ 

በሁለተኛ ደረጃነት ያለው መስፈርት በዚህ ተነፃፃሪ ግዴታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ዓለም አቀፋዊ ከሆነ መርህ ጋር እሰካልተጋጩ ድረስ ያሻቸውን የማድረግ ሙሉ ነፃነት አላቸው፤ ይህ ማለት በዚህ ግዴታ ተይዘው እስካሉ ድረስ ከዚሁ ተነፃፃሪ ግዴታም ጋር ሆነ በተለየ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ድርጊቶቻቸው ላይ ማንኛውም ወገን ተፅዕኖ ሊያሳርፍባቸው አይችልም ይህንን ስንል ግን የነሱም ድርጊት ቢሆን ዓለም አቀፋዊ እና አጠቃላይ (Universal) ከሆነ ተፈጥሯዊ ሕግ እና መርህ ጋር መጋጨት የለበትም እዚህ ጋር ካንት የተፈጥሮ ህግን እንዴት ከሕግ ፍልስፍናው ጋር እንዳዋሃደው መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በመስተመጨረሻ እነዚህ በተነፃፃሪ ግዴታ ውስጥ ያሉ ሰዎች የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ከሆነ አንደኛው ተዋዋይ ወገን ሌላኛውን ተዋዋይ ወገን በሕግ የማስገደድ መብት ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ከሕግ የሚመነጨው ቅጣት ወይም ግዴታ እንዲሟላ እነዚህ መስፈርቶች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡

 ለሞራል ግዴታ ግን እንደዚህ ዓይነት ግዴታ ሳይሆን ቀደም ብለን ስለ ግዴታዊ የሞራል ፍልስፍና የጠቀስነውን መስፈርት መሟላት በቂ ነው፡፡ ይህም ማለት ሰዎች ሌሎዎች ሰዎችን ጥቅማቸውን የሚያሟሉባቻ መሣሪያዎች አድርገው ማየት ሳይሆን በራሳቸው ፍፁም የሆኑ ግቦች እንደሆኑ በማሰብ እንዲሁም ድርጊቶቻቸው በሁሉም ቦታ ለሁሉም ሰዎች እኩል ተፈፃሚ እንደሚሆኑ በማሰብ ሊፈፅሙ ይገባል፡፡ በጠቃላይ ለካንት ሕግ በተነፃፃሪ የሕግ ግዴታ እና ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎች አንደኛው ወገን ሌላኛውን ወገን አጠቃላይ ከሆነ የተፈጥሯዊ ሕግ (Universal Law) አንፃር በመመርኮዝ የሚያስገድድበት ስርዓት እና የሁሉም ሰው ድርጊት በዚህ መርህ አስከተመራ ድረስ እኩል የሆኑ የነፃ መብቶች (Freedom of equal rights) ተጠቃሚ እንደሚሆን የሚደነግግ ስርዓት ነው፡፡

2 ታሪካዊ የህግ ፍልስፍና  ፍሬድሪክ ቮን ሳቭኒ

በህግ ተመራማሪነት ዘመኑ ረዥም ጊዜውን ያሳለፈው የጥንቷ ሮም ስልጣኔን ህግ እና ቋንቋ በማጥናት ነው፡፡ በህግ እና በማህበረሰባዊ ታሪክ ወይም ስነልቦና መሃከል ያለው ግንኙነት ምን  አንደሆነ ለማጥናት ጥረት አድርጓል ቮን ሳቭኒ፡፡ ሳቭኒ ህግን ከሚሰጠው ጥቅም እና ተግባር ጋር አቆራኝቶ አይመለከትም፡፡ ይልቁንም በህግ እና በማህበረሰቡ ታሪክ ወይም ስነ ልቦና ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ በርግጥ ታሪካዊ የስነ ህግ ፍልስፍና የተመሰረተው ጉስታቭ ሁጎ በሚባል ጀርመናዊ ተመራማሪ ሲሆን ሳቭኒም ከዚህ ግለሰብ በተሻለ የዚህን ቤተ አስተምህሮ እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡

ለሳቭኒ ህግ የማህበረሰቡ ስነ ልቦና ውጤት ነው፡፡ ይህ ማህበረሰባዊ ስነልቦና ደግሞ በማህበረሰቡ ታሪክ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በመሆኑም ህግ የህዝባዊ መንፈስ (Volkgeist/ Popular spirit) ነጸብራቅ ነው፡፡ በመሆኑም ልክ እንደ ቋንቋ ፤ ባህል እና ሃይማኖት ሁሉ የአንድ ማህበረሰብን ህግ በማየት ስለማህበረሰቡ ማንነት እና ቋንቋ መናገር ይቻላል፡፡ እንደ አስተምህሮው ከሆነ ጠበቆች ፤ዳኞች እና የህግ ተመራማሪዎች የዚህ ህዝባዊ መንፈስ አስጠባቂዎች ናቸው፡ ምክንያቱም ህግ የዚህ ህዝባዊ መንፈስ ውጤት ነው፡፡ ፍልስፍናው በራሱ በሁለት የተከፈለ ሲሆን ቀዳሚው እና ሳቭኒ ያለበት ቡድን እውነተኛው የአውሮፓ ስነ ህግ መሰረት እና ስነ ልቦና ያለው ወይም ደግሞ የውሮፓ ህግ ህዝባዊ መንፈስ የሚገኘው በሮመረ ሀግጋት ውስጥ እንደሆነ ሲያስረዳ ሌላኛው ደግሞ የጀርመን ስነ ህግ መሆኑን በመጥቀስ ይከራከራል፡፡

ይህን የህግ ፍልስፍና የሚተቹ ሰዎች ይህ ፍልስፍና አንድ ታሳቢ የሚያደርገው ነገር የዚህ ህግ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ የአንድ እና ተመሳሳይ ቋንቋ ፤ ባህል ፤ ሃይማኖት እና ብሄር ባለቤት መሆን አለበት፤ ይሁን እንጂ በዓለማችን ውስጥ በአንድ መንግስት እና ህግ የሚገዙ ግን በብሄር ፤ በቋንቋ፤ በታሪክ እና ሃማኖት የሚለያዩ ህዝቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ህዝቦእ ሳቭኒ እንደሚለው የአንድ ህዝባዊ መንፈስ ተጋሪ ሊሆኑ አይችሉም ይላል፡፡ ሳቭኒ የሮም ስልጣኔን እና ህግን በሚያጠናበት ወቅት ባደረበት ተጽእኖ ይህን አስተምህሮ አቋቁሞ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም ከጀርመን እና የሮም ስልጣኔ ውጭ ይህ ፍልስፍና ሊሰራ መቻሉ አጠራጣሪ መሆኑን ያክላሉ፡፡

3 ማርክሲስት የሕግ ፍልስፍና

ማርክሲስም በመባል የሚታወቀው የኅበረተሰባዊነት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፍልስፍና በጀርመናዊው ፍላስፋ ካርል ማርክስ የተፈጠረ አስተሳሰብ ሲሆን ዓለምን ከስረ- መሠረቱ የነቀነቀ ሐሳብ ነው፡፡ ካርልማርክስ ጀርመን ውስጥ  ፍፅሞ ሃይማኖተኛ ከሆነ ቤተሰብ የተወለደ ሲሆን ከልብ ወዳጁ ፍሬድሪክ ኤንግልስ ጋር በመሆን አዲስ ፍልስፍና መሥርተዋል፡፡ 

ማርክሲስም

ለካርልማርክስ የሰው ልጆች ታሪክ የመደብ ትግል ታሪክ ነው፡፡ በመሆኑም በሰው ልጆች መሃከል ዕውነተኛ ፍትህ ለማምጣት መደብ አልባ ማኅረሰብ መፍጠር እንደ ግብ አይተን ጭቁን የኅበረተሰብ አካላትን ማንቃት እንደሚገባ ያስባል፡፡ የሰው ልጅ በዝግመቱ ለውጥ ከቅድመ ሰው ዝርያነት ተላቅቆ ጋርዮሻዊ ማኅበረሰብን ከፈጠረበት ጊዜ እስከ ፊውዳላዊ እና ካፒተሊስታዊ ማኅበረሰቦች እስከ ተፈጠሩበት ዘመን ድረስ አንዱ ስርዓተ ማኅበረሰብ በራሱ ጉያ ውስጥ የራሱን ተቃራኗዊ ስርዓት አቅፎ ካሳደገ በኋላ በዚያው ባሳደገው ፍልስፍናዊ ስርአት ተደፍጥጦ እና ተውጦ ያልፋል፡፡ ይህ የዲያሌክቲክስ ፍልስፍና ሲባል የሰው ልጆችን ታሪክ እና አጠቃላይ ቁስአካላዊነት የምንረዳበት መንገድ ነው፡፡ በዚህ ሂደት አማካይነት የሰው ልጆች የደረሱበት የመጨረሻው ስርዓተ ማኅበር ካፒታሊስታዊ ሲሆን ይህ ስርዓት የሰው ልጆችን በተለይም የሠራተኛውን መደብ እጅግ የሚጨቁን እና የሚበዘብዝ ስርዓት በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ሊፈርስ እና የማምረቻ መሳሪያዎች እና የምርት ፈጠራ ሂደቶች በሙሉ በማኅበረሰቡ አባላት እኩል ሊከፋፈል ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ማኅበረሰብ የካፒታሊስት ስርዓቱ እጅግ ከመግነኑ የተነሳ ኢምፔራያሊስት የሆነ የጨቋኝ መደብ ይፈጥራል፡፡

 እነዚህ ጥቂት ካፒታሊስት ኤምፔያሪያሊስቶች የሰው ልጆችን ሃብት እና ገንዘብ በመሉ ለራሳቸው ተቆጣጥረው ሲያበቁ በየፋብሪካው ዕለት ተዕለት ሕይወቱን ለማሸነፍ ለሚሠራው የሠራተኛ መደብ አነስተኛ ክፍያ እና ትከሻ ሰባሪ ስራ እየሠጡ ይበዘብዙታል፡፡ በመሆኑም የሠራተኛው መደብ በቁጥር ብዙ እና እጅግ የበረታ ኃይል ያለው እንደመሆኑ በቁጥር ትንሽ የሆኑትን እና ትንሽ ሃይል ያላቸውን ካፒታስቶች ፈንቅሎ በመጣል የምርት ሂደቱን እና አንጡራ ሃብቱን ሊቆጣጠር ይገባል፡፡ በዚያን ጊዜ እውነተኛ ኅበረተሰባዊነት የሚፈጠር ሲሆን ሰዎች  የሚበዘበዙበትን ስራ ሳይሆን ትርጉም እና እርካታ የሚያገኙበትን ስራ ይሠራሉ፤ ያኔ ከሁሉም እንደየአቅሙ ለሁሉም እንደየፍላጎቱ ስለሚደርስ የሃብት ክፍፍልን አስመልክቶ የሚነሳ ፀብ አይኖርም፡፡ አጠቃላይ የማክሲስሞ ፍልስፍና ሃሳብ እጅግ ባጠረ መልኩ ሲቀርብ ከላይ የተዘረዘረውን ይመስላል፡፡ 

ማርክሲስም እና ህግ

በመሆኑም ለካርል ማርክስ ሕግ የምንለውን ጉዳይ ከፖለቲካዊ ርዕዮት ለይቶ ማየት የማይቻል ነገር ነው፡፡ በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ሕግ የፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለሙ ነጸብራቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የገዢው እና ጨቋኙ ቡርዥዋ እና ካፒታሊስት መደብ መገልገያ መሣሪያ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሕግ በመደቦች መሃከል ያለውን ኢፍትሃዊ የምርት ግንኙነት እና የሃብት ክፍፍል ለማፅናት የሚያገለግል ነው፡፡ በመሆኑም ሕግ ይህንን ሚናውን በመቀየር የካፒታሊስት ስርዓቱን ከማገልገል ተላቅቆ የሠራተኛ መደብ አንምባገነንነት እንዲመጣ ጉልህ የሆነ ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡

 በመጨረሻም እውነተኛ ኮሚዮኒስታዊ ስርዓት ሲገነባ ሕግ ወይም መንግስት የሚባል ነገር አያስፈልግም፡፡ ሕብረተሰቡ በራሱ የምርት ሂደቱን እና ሃብቱን ተቆጣጥሮ ፍትሐዊ ክፍፍል ስለሚያሰፍን በሕግ መገዛት አይኖርበትም፡፡ በመሆኑም በማርክሲሳት ስርኣት ህግ የራሱን መቃብር እንደሚቆፍር ባለፍርድ ከአገልግሎት ውጪ እስከሚሆን ድረስ ራሱን የጭቆና መሣሪያ ከመሆን እየቆጠበ እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ 

4.የሕግ እና ኢኮኖሚ ጥምረት ፍልስፍና

ሕግ እና ኢኮኖሚክስ በታሪክ ውስጥ የነበራቸው ግንኙነት ረዥም እና ሰፊ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜ የተነሱ የፖለቲካስ ኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች በሕግ እና ኢኮኖሚክስ መሃከል ያለውን ግንኙነት በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ሊያጠኑ ሞክረዋል፡፡ ከአዳምስሚዝ እስከ ካርልማርክስ ድረስ የተነሱት ፍልስፍናዎች በሁለቱ መሃከል ያለውን ግንኙነት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ይሁን እንጂ በ1961 (እ.ኤ.አ) በአሜሪክ የቺካጎ የኢኮኖሚክስ ቤተ-አስተምህሮ ስር የተሰበሰቡት እንደ ሮናልድ ኮዝ እና ጄራልድ ካላብሬሲ ዓይነት ተመራማሪዎች በሕግና በኢኮኖሚ መሃከል ቀጥተኛ ግንኑነት እንዳለ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ 

በዚህም ኢኮኖሚክስ ለሕግ አውጪዎች እና ተርጓሚዎች ቁልፍ መሣሪያ እንደሆነና እንድ ሕግ በማኅበረሰቡ እና መንግስት ላይ የሚያስከትለው የወጪ መጠን እና በአንድ ሕግ መሠረት ውሳኔ ሲሰጥ በተከራካሪ ወገኖች ላይ የሚያሳድረው ጫና ምን እንደሆነ ከኢኮኖሚክስ ሕግጋት አንፃር መመርመር እንደሚገባን ይገልፃሉ፡፡ ኢኮኖሚክስ የሕግ ስርዓቱን ሲደግፍ ስርዓቱ ውጤታማ እና ቀልጣፋ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ቅልጥፍና (Efficiency) ያለው የፍትህ ስርዓት አጠቃላይ ለሆነ የሃገር እድገት ወሳኝ ሚናን ይጫወታል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚክስ አንዳንድ ሕግጋት በግለሰቦችም ሆነ በመንግሥት ላይ የሚያስከትሉትን ወጪ እንድንገምት ያግዘናል፤ ለምሣሌ ከውል ውጪ ባሉ ኃላፊነቶች በአንድ ባለጉዳይ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን (Present and future damage) በትክክል ለማስላት መጠቀም ያለብን መሠረታዊ የኢኮኖሚክስ ሕግጋትን እንደሆነ ፍልስፍናው ያስተምራል፡፡

 ዳኞች ዕለት ተዕለት የጉዳት ካሳን በማስላት ሲወስኑ በጣም ኃላ ቀር የሆኑ የስሌት ቀመሮችን እየተጠቀሙ ቢሆን እንኳ ሳያውቁት የኢኮኖሚክስ ሕግጋትን በውሳኔያቸው ውስጥ እየተገበሩ ነው፡፡ በተጨማሪ ሕግጋት በዜጎች ላይ የሚያስከትሉት ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በመገመት ትንበያውን ለሕግ አውጪዎች እና የፖሊስ አርቃቂዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት አንድ ሕግ ሲወጣ ከሃያ እና አርባ ዓመት በኃላ በተወሰኑ የኅበረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ እና አዎንታዊ ተፅዕኖ ቀላል ኢኮኖሚያዊ ሕግጋትን በመጠቀም መተንበይ እንደሚችል ምሁራኑ ያስረዳሉ፡፡

 አንዳንዶች ኢኮኖሚያዊ የሕግ ጥናትን እስከፅንፍ በመውሰድ የሕግ ዋንኛ ዓላማው ቅልጥፍና እና ወጪ ቁጠባን በማበረታታት የአንድ ሃገር ኢኮኖሚ እንዲጎለብት መርዳት እንደሆነ ያትታሉ፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞች ሕግ ተርጓሚዎች የኢኮኖሚክስ መርሆዎችን በመረዳት በፍርዶቻቸው ውስጥ መጥቀስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተለመደ ተግባር አልነበረም፡፡ የዚህ ፍልስፍና አራማጆች ቅልጥፍና (Efficiency) የፍትህ ስርዓቱን የምንለካበት ዋንኛ መሣሪያ እንደሆነ ከማስቀመጣቸው የተነሳ የተለያዩ የመለኪያ መርሆዎችን የቀየሱ ሲሆን አንደኛው ፓሬቶ የቅልጥፍና መርህ (Pareto efficiency rule) ይባላል፡፡ ይህ መርህ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማምጣት በኢኮኖሚክስ ትምህርት የታወቀ ቢሆንም በሃገረ- አሜሪካ በፍትህ ሰዎቹ በሰፊው ከተተገበሩ ኢኮኖሚያዊ መርሆዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ 

5. የብዝሃ- ሕግ ፍልስፍና

በአንድ ሃገር ውስጥ ከአንድ በላይ የሕግ ስርዓቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ የሕግ ብዝሃነት (Legal pluralism) በምን መንገድ ሊስተናገድ እንደሚገባ ብዙ ሰዎች የተለያየ ዓይነት ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ባህላዊ እና የልማድ የሕግ ስርዓቶች ተቀራራቢ እና ተወራራሽ በሆነ መልኩ ተያይዘው በአንድ ሃገራት ውስጥ ከመገኘታቸው ባለፈ ከእነዚህ ሕግጋት በተለየ መልኩ መጤ የሆኑ አውሮፖዊ ሕግጋት በውዴታ እና በግዴታ ተጭነውባቸው ይገኛል፡፡ 

በቅኝ አገዛዙ ዘመነ መንግሥት አውሮፓውያን የራሳቸውን ቋንቋ፤ ባህል እና ሕግ በአፍሪካ ቀዳሚ ባህሎች እና ሕዝቦች ላይ ሲጭኑ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ባህሎች እና ልማዶች ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ የደረሰባቸው በመሆኑ ይህንን ተቃርኖ በማስወገድ በህግ፤ በልማድ ሕግጋት እና በአውሮፓዊ ሕግጋት መሃከል ያለውን ግንኙነት መወሰን ነበረባቸው፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹ የቅኝ ገዢ ሕጎች በተወሰነ መልኩ የባህል ህጎች  ቅኝ በተገዙት ሕዝቦች ላይ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሚደነግጉ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት ከአውሮፓ የመጡት ሕጎች ሰፊ እና ግዙፍ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ ሲሆኑ አነስተኛ እና ግላዊ በሆኑ ጉዳቶች ላይ ባህላዊ ሕግጋት ተፈፃሚ ይሆኑነበር፡፡ይህ ሁኔታ ልዩ የሆነ የብዝሃ-ሕግ ስርኣት እንዲኖር ያደረገ ሲሆነ ሕጋዊ ብዝሃ-ህግ  በመባል ይታወቃል፡፡ 

ይሁን እንጂ ከዚህ በተለየ መልኩ አንድ ሰው በአንድ ሃገር ውስጥ እየኖረ በአንድ እና ተመሳሳይ ጉዳይ ከአንድ በላይ ለሆኑ ሕግጋት ተገዢ እንዲሆን ሲገደድ የሚፈጠረው ሁኔታ ተግባራዊ የህግ ብዙሃነት ይባላል፡፡ በተግባራዊ የሕግ ብዙሃነት ወቅት ዜጎች በአንድ ሃገር ውስጥ ቢሆንም ከክልል ክልል በሚለያዩ ሕግጋት አማካኝነት በተመሳሳይ ጉዳይ የተለያየ ፍርድ ሊጣልባቸው ይችላል፡፡ ይህንን ጉዳይ በማስተዋል ሰዎች የተሻለ ውሳኔ/ ሕግ ወዳለበት ክልል ጉዳያቸውን ይዘው ሲሄዱ የመድረክ ምርጫ ጉዳይ ይከሰታል፡፡

 በቀደመው ሕጋዊ የብዙሃ ሕግ አስተምህሮ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አይከሰትም ምክንያቱም ባህላዊ ሕግጋቱ እና አውሮፓዊ ሕግጋት ጎን ለጎን ሳይገፋፉ በስራ ላይ ይውላሉ፤ በአንድ ሃገር የተለያዩ የሕግ ብዝሃንነትን ለመፍታት የሚያስችል የሕግ ስርዓት መዘርጋት ግን ግዴታ ነው፡፡ በርግጥ አሁን ባለንበት የሉላዊነት ዘመን ባህሎች፤ ህጎች፤ መንግስታት በሙሉ እየታጠፉ ወደ አንድ ማዕከላዊ ባህል፤ መንግሥት፤ ገንዘብ እና ርዕዮት እየመጡ የሚገኝ ቢሆንም ይህ ሂደት ረዥም ጊዜ የሚፈጅ እንደመሆኑ ሃገራት በውስጣቸው ያሉት የተለያዩ የሕግ ምንጮች በማክበር ጠቃሚ ከሚሆን ሁኔታ ሊገላገሉባቸው ይገባል፡፡ 

የብዝሃ-ሕግ ፍልስፍናም አጠቃላይ ሃሳብ አፍሪካ ውስጥ ላሉ ሃገራት ሁኔታ የተለያዩ የልማድ እና የባህል ሕግጋት ማዕከላዊ ከሆኑትንና ከፖርላማ ከሚታወጁት ሕግጋት ይልቅ ለሕዝቡ ሕይወት የሚቀርቡ በመሆናቸው ኗሪ ሕጎች (Living Laws) ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ባህላዊ ሕግጋት እንደ አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴ፤ ባህልን የማሻገሪያ እና የማስተማሪያ ስርዓት፤ ለማዕከላዊ መንግስት የህግ ምንጭነት እና መሰል ሁነቶች ላይ በማዋል ሀገርን እና ህዝብን እንዲጠቅሙ ማድረግ ይገባል፡፡ 

የህግ ንቅለ ተከላ ( Legal Transplantation)

በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታን እንደ ዋንኛ አጀንዳቸው አድርገው መንቀሳቀስ የጀመሩት ህጎቻቸውን በማዘመን ነው፡፡ አብዛኞቹ አፍሪካዊ ሃገራት ዘመናዊነት ወይም ህግ ማዘመን የሚለውን ቃል የተረዱት ያደጉ ሃገራት ህግጋትን መቅዳት በሚል ስለሆነ በተለይም ከቅኝ መገዛት ከተላቀቁ በኋላ ከፍተኛ በሆነ መንገድ ከአውሮፓ ህግ እና ባህል ለመላቀቅ ቢጥሩም አልተሳካላቸውም፡፡

እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ሃገራትም ዘመናዊነትን የፈረንጅ ህግ እና ባህል መቅዳት በሚል የተረዱት በመሆኑ ከፍተኛ ህግ ከአውሮፓ አስመጥተዋል፡፡ህጎቹ ሲመጡም የተካሄደው ንቅለ ተከላ ነው፡፡ በወቅቱ ማዕከላዊ መንግስቱን የሚያገለግሉ እንደ ፍትሃ ነገስት ያሉ ህግጋት ተነቅለው የአውሮፓ ህግጋት ተተክለዋል፡፡ በ1950 ዎቹ አጼ ሃይለስላሴ ይህን ሰፊ የአርቃቂ ኮሚቴ ሲያደራጁ ሃገር በቀል ህግጋት እንዲታከሉ ትእዛዝ ቢሰጡም ህግጋቱ በአመዛኙ አውሮፓዊ መሆናቸው አልቀረም፡፡ የሃገራችን የፍትሃብሄር ህግ፤ የወንጀል ህግ፤ የወንጀል ስነ ስርዓት ህግ፤ የፍትሃብሄር ስነ ስርአት ህግ፤ የንግድ ህግ እና የባህር ህግ በሙሉ የተቀዱት ከአውሮፓ ሃገራት እንደመሆኑ እነዚህ ህግጋት በዚህ ግማሽ ክፍለ ዘመን ለህዝቡ ያመጡት ጥቅም መጠናት ይኖርበታል፡፡

የህግ ስርፀት ( Legal Penetration)

ከአውሮፓ የመጡት ህግጋት ወደ ሃገር ውስጥ መጥተው በጥቅም ላይ ሲውሉ የገጠማቸው ተግዳሮት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በፍትህ ስርዓቱ እና በማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ለመስረጽ ከፍተኛ የሆነ የተቀባይነት ችግር ለማለፍ ተገደዋል፡፡በመሆኑም እነዚህ ህግጋት በማህበረሰቡ ውስጥ ተገቢውን እውቅና  እና ተቀባይነት እንዲያገኙ መንግስት ሰፊ የሆነ የንቃተ ህግ ስራዎችን መስራት አለበት በማለት አንዳንድ ሰዎች ሲከራከሩ የተቀሩት ደግሞ እነዚህ ህጎች በሂደት እና በጊዜ ቀስ እያሉ ወደ ማህበረሰቡ መስረጽ አለባቸው እንጂ በቀጥታ በህዝቡ ላይ መጫን የለባቸውም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ሌሎች በበኩላቸው ውጤታማ የሆነ የህግ አሰራጺነት ተግባር ሊከናውን የሚችለው እነዚህን ህግጋት ሙሉ ለሙሉ በማስፈጸም  ነው፡፡ ለምሳሌ የሴት ልጅ ግርዛት በውንጀል ህጉ የተከለከለ ቢሆነም አሁንም በአብዛኛው የሃገራችን ክፍሎች ይፈጸማል በመሆኑም ይህንን ህግ በሃይል እንዲፈጸም ካደረግነው ሊሰርጽ ይችላል ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ፡፡

የብዝሃ-ሕግ ፍልስፍናም አጠቃላይ የተለያዩ የልማድ እና የባህል ሕግጋት ማዕከላዊ ከሆኑትንና ከፖርላማ ከሚታወጁት ሕግጋት ይልቅ ለሕዝቡ ሕይወት የሚቀርቡ በመሆናቸው ህይወት ያላቸው ሕጎች (Living Laws) ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ባህላዊ ሕግጋት እንደ አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴ፤ ባህልን የማሻገሪያ እና የማስተማሪያ ስርዓት፤ ለማዕከላዊ መንግስት የህግ ምንጭነት እና መሰል ሁነቶች ላይ በማዋል ሀገርን እና ህዝብን እንዲጠቅሙ ማድረግ ይገባል፡፡ ባህላዊ ህግጋት ህይወት ያላቸው የሆኑት ህዝቡ እንደ ባእድ ህግጋት ስለማያያቸው ነው፡፡ለህዝቡ ሃዘን፤ስሜት፤ ደስታ እናሞራል በእጅጉ የቀረቡ ብቻ ሳይሆን መለየት እንኳ አስቸጋሪ ነው፡፡በመሆኑም  በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት በህግ ስርአታቸው  ውስጥ ከአንድ በላይ የህግ  ስርአት መኖሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ሊያዩት ይገባል፡፡

6.ሕግ፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂ 

 በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት እና ባደጉት ሃገራትም ጭምር የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕድገት ፍጥነት ብዙ ማኅበረሰባዊ አወቃቀሮችን እየቀየረ እና አዳዲስ ተግዳሮቶችን እና መልካም አጋጣሚዎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በዓለማችን ላይ በፍጥነት እያደጉ ያሉት እንደ Artificial Intelligence፤Cryptocurrencey፤Social media እና የመሳሰሉት የቴክኖሎጁ ዕድገቶች የሠው ልጆች ሕይወትና የመንግስት አወቃቀር በእውኑ ዓለም ብቻ ሳይሆን በ Virtual world ውስጥም እየጠለቀ መሄዱንና ለወደፊቱም ይኸው የሚቀጥል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በአሁን ወቅት አብዛኛው የሠው ልጆች የግል፤ የተቋም፤ የንግድ፤ የመንግሥት እና መሰል ግንኙነቶች እና ውሎች (transaction) የሚካሄዱት በኢንተርኔት አማካኝነት በተዘረጋው የግንኙነት መስመር ነው፡፡ 

  ሕግ ደግሞ ከአፈጣጠሩም ቢሆን የሰዎችን ውል እና ግንኙነት  ለመቆጣጠር፤ ለመምራት እና ለመገደብ የተፈጠረ ሰው ሠራሽ ግኝት ነው፡፡ በመሆኑም የሰው ልጆች ግንኙነት ከገሃዱ ዓለም ይልቅ ወደ ቨርቹአል ዓለም የጠለቀ እና ያጋደለ ከሆነ የሕግ ዓላማና ትኩረትም ወደዚሁ ዓለም ያነጣጠረ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ እያደጉ ባሉ ዓለማት የቴክኖሎጂ መስፋፋት እጅግ አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር ይኸው የቴክኖሎጂ መስፋፋት በጣም ኃላቀር በሆኑ የመንግሥት እና የዲሞክራሲ ተቋማት፤ ደካማ ኢኮኖሚ፤ ብዙ ያልተማረ የሠው ሃይል እና ከፍተኛ ስራ አጥነት በተንሠራፋበት ሁኔታ ላይ መደረቡ አስጊ ነው፡፡ 

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የቴክኖሎጂ ዕድገት ተግዳሮቶች ለአፍሪክ ሃገራት የማይረዱትን ጥያቄ የመመለስን ያህል የተወሳሰበ ነው፡፡ በመሆኑም ሕግጋቱ ይህንን የዕድገት መንቀራፈፍ ከግምት በማስገባት ገንቢ እና ጠቃሚ አሰራሮችን መቀየስ ይኖርባቸዋል፤ ጠቃሚ ስንል ሕግ የሃገሪቱን ልማት መደገፍ አለበት እያልን ነው፡፡ 

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሕግ እና ልማት መሃከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠና ቤተ አስተምህሮ እ.ኤ.አ በ1960 በሃገር አሜሪካ ተመሥርቶ የነበረ ሲሆን ይህ አስተምህሮ በፎርድ ፋውንዴሽን እየተድገፈ ሕግ እያደጉ ባሉ ሃገራት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ እድገትን በሚያመጣ መልኩ መቀረፅ እንዳለበት ያስተምር የነበረ ቢሆንም ብዙም ድጋፍ ሳያገኝ ሊቀዛቀዝ ችሏል፡፡ ከዚያ በመቀጠል ለሁለተኛ ጊዜ በ1980ቹ የኒዩ ሊብራል አስተሳሰብ ወደ አፍሪካ ሃገራት በሚሠረፅበት ወቅት በድጋሚ ይህ አስተምህሮ ተነሳስቶ በአደጉ ሃገራት መቀጣጠል ጀምሯል፡፡

 የህግና ልማት  ፅንሰ ሃሳብ በጥቅሉ ሕግጋት በአንድ ሃገር የሚመጣውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊያደናቅፉ አይገባም የሚል ነው፤ የአፍሪካ ሃገራት ካሉበት የድህነት አረንቋ ለማውጣት ሰፊ እና ትላልቅ የልማት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በሕግ እና ሕግ-ነክ የቢሮክራሲ ማነቆዎች መደናቀፍ የለባቸውም ይልና እንዲያውም ሕግ ይህንን የልማት ሂደት የሚያግዝ መሣሪያ መሆን እንዳለበት ያሳስባል፡፡ በአሁን ወቅት የሕግና ልማት ጥናቶች በአሜሪካና በአውሮፓ ባሉ ከፍተኛ ትምህርተ ተቋማት ውስጥ በሰፊው ይገኛሉ፡፡ 

በቴክኖሎጂው እድገት ሳቢያ ባደጉት ሃገራት የወንጀል ሕግ አዲስ ዘርፎችን እያካተተ ይገኛል፡፡ እንደ Cyberbullying (የኢንተርኔት ማንጓጠጥ)፤Hate speech (የጥላቻ ንግግር) ፤ Fake news (ሐሰተኛ ዜና) ፤ Hacking (የሚሰጥር ቃል ሰበራ) የመሳሰሉት ጉዳቶች የአሜሪካ የፍትሕ ስርዓትን እየተፈታተኑ ይገኛሉ፤ ይሁንና በኢንተርኔት ላይ የሚደረግ የሕግ ቁጥጥር በገሃዱ ዓለም እንዳለው የሕግ ቁጥጥር ቀላል እና ምቹ ሊሆን አይቻልም፡፡

Artificial Intelligence

ይህ ዘርፍ በተለምዶ የሮቦቲክስ ሳይንስ ከሚባለው በእጅጉ የተለየ እና የረቀቀ ነው፡፡ ማሺኖች እና ሮቦቶች የሰውን ልጅ ባህሪ እና ስሜት መረዳት የሚችሉ ፍጡሮች (Sentient beings) ሆነው እንዲፈጠሩ በሂደትም እውቀት እና ስሜትን እንደ ሰው እየተረዱ እንዲሄዱ መደረጉ አስፈላጊ እና አይቀሬ እየሆነ መጥቷል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ፍጥረታት ወይም ማሺኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ሰውኛነት እየቀረቡ  እና እየመሰሉ መሄዳቻው እጅጉን አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡

በመሆኑም ሰዎች በተለምዶ የሚሰሯቸውን ስራዎች እየተኩ መሄዳቸው የማይቀር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች በገፍ ከስራ ገበታቸው የሚያፈናቅል በመሆኑ እነዚህ ከስራ የተፈናቀሉ ግለሰቦች ለወንጀል ፤ ለዕፅ እና ለተለያዩ ወንጀል ጠቀስ ሁነቶች መጋለጣቸው የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም እንዚህ ማሺኖች ራሳቸው የሚያስተምሩ አድርጎ መስራት እና ማበልጸግ (Machine learning or deep learning) በረጅም ርቀት ከሰው ልጆች ጥቅም አንጻር የሚፈይደው ነገር ሊኖር መቻሉ ሊጠና እና ሊመረመር ይገባል፡፡

Hate speech (የጥላቻ ንግግር)

በተለመደው የወንጀል ህግ ስድብ ፤ ዛቻ ፤ ማስፈራራት እና ስም ማጥፋት እንደ ወንጀል የሚያስጠይቁ ቢሆንም የኢንተርኔት መስፋፋትን ተከትሎ ከማይታወቁ እና ከሚታወቁ ምንጮች የፖለቲከኞችን ፤ የዘርን እና ሃይማኖትን መብት በእጅጉ የሚጎዱ ምስሎች እና ጽሁፎች እይተሰራጩ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የጥላቻ ንግግርን የሚያስቀር የህግ ማእቀፍ አስፍላጊ ነው፡፡

ከዚህ ዓይነቱ ጉዳይጋር በጥቂቱም ቢሆን የሚገናኘው Cyberbullying (የኢንተርኔት ማንጓጠጥ) ሲሆን በተለይ በወጣት ተማሪዎች ዘንድ እንደ ዓለም አቀፍ ችግር እየታየ ይገኛል፡፡ በድሮ ዘመን በትምህርት ቤት ውስጥ ጉልበተኛ እና ታዋቂ የሆኑ ተማሪዎች በደካማ ተማሪዎች ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃት በኢንተርኔቱ ዓለም ደግሞ በዚሁ መልክ እየተገለጠ ይገኛል፡፡በዚህም አማካኝነት ብዙ ተማሪዎች ራሳቸውን ለማጥፋት በቅተዋል፡፡

ሰዎች በተለምዶ በአካል ከሚያደርጉት እና ከሚናገሩት ይልቅ በኢንተርኔት ላይ የሚናገሩት እና የሚያደርጉት ነገር እጅግ የተጋነነ ይሆናል፡፡ከዚህም በተጨማሪ የሰዎች እለት ተእለት ኑሮ ለማህበራዊ ሚዲያ ተግባቦት የተጋለጠ እንደመሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ የሚደርስባቸው ጥቃት ምናልባትም በአካል ከሚደርስባቸው ዛቻ እና ስድብ ይልቅ የሚጎዳ ሊሆን ይችላል፡፡

Fake news (ሐሰተኛ ዜና)

በአሜሪካው የ2016 ምርጫ ለዶናልድ ትራምፕ መመረጥ በተገዳዳሪዎቹ ላይ የተሰራጨው ሃሰተኛ ዜና ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ለእዚህ ዜና መሰራጨት ዓይነተኛ ሚና የተጫወቱ የውጪ ሃይላት እንዳሉ ቢታወቅም እነዚህን ዜናዎች በተቀናጀ አልጎሪትም ለሚመለካታቸው መራጮች በመላክ ውጤቱ እንዲቀየር ለማድረግ መቻሉ ብቻ ለሃሰተኛ ዜናዎች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡

እንደ አፍሪካ ሃገራት ያልጻኑ የዲሞክራሲ ተቋማት ሲኖሩ ደግሞ ጉዳዩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደማለት ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ለተካሄዱ የድህረ ምርጫ ብጥብጦች እና መፈንቅለ መንግስቶች ዋንኛ ምክንያቱ የሃሰተኛ ዜናዎች መሰራጨት መሆኑ የማያከራክር ነው፡፡ ሃሰተኛ ዜና ከጥላቻ ንግግሮች በዓይነቱ የሚለይ ሲሆን ምንም አይነት የጥላቻ ንግግር ያልያዙ እንዲያውም ወደ እውነተኛ ዜናነት የሚጠጉ ሆኖም አሳሳች እና ተቃራኒ ማስረጃዎችን የታጨቀባቸው ዜናዎችን ሆነ ብሎ መበተን የሚያስከትለው ውጤት ነው፡፡ 

Cybercrime (የኢንተርኔት ወንጀሎች)

በአሁን ወቅት ያደገው ዓለም የኢንተርኔት ወንጀሎች ብሎ የፈረጃቸው ጉዳዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉ እና እየተወሳሰቡ ሄደዋል፡፡ ለምሳሌ የሚስጥር ቃላትን እና ቁጥሮችን በመስበር የተለያዩ ተቋማትን ሚስጥር አደባባይ ማውጣት እና አንደ ማሰፍራሪያ በመጠቀም ገንዘብ እና ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት መሞከር ከፍተኛ ጭግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በዚህ ወንጀል ከግለሰብ እስከ ተቋም ድረስ ብዙ ጉዳት ተፈጽሟል፡፡ የሚስጥር ቃል ሰበራ በሃገር ኢኮኖሚ እና ደህንነት ላይ የሚጥለው ችግር ከፍተኛ መሆኑን የምንረዳው በአሁን ሰዓት ከትንሽ ቢሮ እስከ ኒውክለር ማበልጸጊያ፤ የውሃ እና መብራት አሰራሮች በሙሉ በኢንተርኔት የሚታዘዙ በመሆኑ ነው፡፡

በግለሰብ ደረጃ አውርደን ብናየው እንኳ አንድ ግለሰብ የማህበራዊ ደህንነት ቁጥሩ ፤ የባንክ አካውንቱ ፤ መታወቂያው ፤ የኤቲኤም ካርዱ፤ የመስሪያ ቤቱ ማህደር፤ የትምህርት ማስረጃው፤ ማህበራዊ ድህረ ገጹ እና መሰል የማንነት ዘንጎቹ በሙሉ የሚገኙት በኢንተርኔት ላይ በመሆኑ እነዚህን በተቀናጀ መልኩ ከአንድ ግለሰብ ወደ ሌላ ግለሰብ ማዛወር መቻል ግለሰቡን ማንነት አልባ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይህ ባደጉት ሃገራት የማንነት ስርቆት Identity theft የሚባል ሲሆን ወደፊት አስጊ ከሚባሉ የኢንተርኔት ወንጀሎች መሃከል አንዱ ነው፡፡

ሰው እና ዕጣ ፈንታው

 የሰው ልጆች ታሪክ ማለት የህግ እና ሞራል እድገታቸው ታሪክ ማለት ነው፡፡ የሰው ልጆች ሞራል እንዴት እያደገ እንደመጣ በጥቂቱም ቢሆን ተመልክተናል በመሆኑም የሰው ልጆች ታሪክ በኢንተርኔት እና ቴክኖሎጂ እድገት እና ይህን ተከትሎ በሚመጡ ችግሮች እና ጠንቆች እንደሚደመደም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

የምንኖርበት ዘመን በእጅጉ ከተጫነው ድህረ ዘመናዊነት እና አንጻራዊነት ባሻገር አሁን ደግሞ በቴክኖሎጂ እና በማህበራዊ ሞራል ዝቅጠት አንጻር ውዝገብ ውስጥ እየተንደረደረ ይገኛል፡፡ ይህ የድህረ እውነት ዓለም ከላይ ከተጠቀሱት አስተሳሰቦች ጋር ተደምሮ ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ ግብረገብነት እና ስነምግባርን ከዚህ ቀደም ታይቶ ወደማይታወቅ ግዛት እና የሃሳብ  አድማስ እየጎተታቸው ነው፡፡ 

በግለሰባዊ ሞራል እና በማህበረሰባዊ ሞራል መሃከል ያው ገመድ ዕለት ዕለት እየቀጠነ እና እየተወጠረ ይገኛል፡፡ ዓለማት በቴክኖሎጂና በካፒታሊዝም እድገት እየታገዘች የሰው ልጅን ከማህበረሰቡ የተነጠለ ብቸኛ ፍጥረት እንዲሆን አስገድዳዋለች፡፡ ሁሉም ግለሰብ የራሱን የሞራል መስፈርት እና መለኪያ የሚያዘጋጅ ከሆነ የማህበረሰባዊ ሞራል ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለብን፡፡  




Popular Posts

DOCUMENTS

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd

Files

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ 2/ 2006 PDF-Revised Federal Supereme Court s No 2/2006 by ሕግ እና ፍትህ on Scribd