Search This Blog

Oct 25, 2020

ግልጽና ተጓዳኝ ስልጣን



ግልጽና ተጓዳኝ ስልጣን



አብዛኛውን ጊዜ ለመንግስት አካላት የሚደለደለው ስልጣን አሻሚ ባልሆነ አነጋገር ይገለጻል፡፡ ግልጽና ቀጥተኛ ስልጣን በአስተዳደሩ ውስጥ ህጋዊነትን ያሰፍናል፡፡ በተጨማሪም ስልጣንን በመገልገል ረገድ ጥርጣሬና ብዥታን ያስወግዳል፡፡ በተግባር ሲታይ ግን ለውጤታማ አስተዳደር አስፈላጊ የሆኑትን ስልጣናትና ተግባራት መዘርዘር ያዳግታል፡፡ ስለሆነም በግልጽ ስልጣን ውስጥ አስፈላጊ የሆነ በዝምታ የሚተላለፍ ተጓዳኝ ስልጣን ይኖራል፡፡ አንድን ድርጊት ለመፈፀም ግልጽ የሆነ ስልጣን ሲሰጥ የድርጊቱ አካል የሆኑና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል በዝምታ የሚሰጥ ስልጣን ስለመኖሩ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የህጉን ዓላማና ግብ እንዲሁም የህጉን ድንጋጌዎች አነጋገር በጥልቀት መፈተሽ ይጠይቃል፡፡ ተጓዳኝ ስልጣን መኖሩን ለመወሰን የሚከተሉት ነጥቦች ግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡





የህጉ አነጋገር





ይህ የህግ አውጭውን ሀሳብ ለማወቅ ወሳኝነት አለው፡፡ ለምሳሌ የመንግስት እና የግል ድርጅት ሠራተኞች ኤጀንሲዎች በሚያስፈጽሟቸው አዋጆች መሰረት ለማናቸውም ዓይነት አበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች መሟላታቸውን የማረጋገጥና የአበሉን ዓይነትና መጠን የመወሰን ስልጣን አላቸው፡፡ ለአበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በአዋጅ ቁ. 714/2003 እና 715/2003 የተለያዩ ድንጋጌዎች በዝርዝር ተለይተዋል፡፡ ኤጀንሲዎቹ እነዚህን ሁኔታዎች መኖራቸውን የመወሰን ስልጣናቸው ክርክር አያስነሳም፡፡ ለምሳሌ በአዋጅ ቁ. 714/2003 አንቀጽ 41 መሰረት ለሟች ሚስት ወይም ባል የሚከፈለው የጡረታ አበል ሟች ያገኝ ወይም ሊያገኝ ይችል የነበረው የጡረታ አበል 50 በመቶውን ነው፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ላይ ባል ወይም ሚስት የጡረታ አበል በመቀበል ላይ እያሉ ጋብቻ ከፈጸሙ አበሉ የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች ተመልክተዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች መወሰን በኤጀንሲዎቹ ስልጣን ስር ቢሆንም የባልነት ወይም ሚስትነት ጥያቄ በተነሳ ጊዜ ይህንን ማረጋገጥ ከስልጣናቸው ክልል በላይ ነው፡፡ ይህን መወሰን በመደበኛ የዳኝነት አካላት ስልጣን ስር ይወድቃል፡፡ ስለሆነም ‘ለአበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች’ የሚለው አነጋገር በሁለቱም አዋጆች ላይ መለኪያና መስፈርት የተቀመጠላቸውን ሁኔታዎች እንጂ በሌሎች ህጎች የሚወሰኑትን አያካትትም፡፡ የህግ አውጨው ሀሳብም ኤጀንሲዎቹ ለአበል ብቁ የሆኑ የሟች ሚስት ወይም ባል የሚከፈላቸውን መጠንና እና ክፍያውን የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎች እንዲወስኑ እንጂ ከመነሻው ባልነት ወይም ሚስትነትን በተመለከተ ማስረጃ አሰባስበው ውሳኔ እንዲሰጡ አይደለም፡፡





በግልጽ የተሰጠው ስልጣን ወሰን





ስልጣኑ በጠባቡ ከተሰጠ ተጓዳኝ ስልጣን ስለመኖሩ በጠባቡ መተርጐም ይኖርበታል፡፡ በአንጻሩ ሰፊ የሆነ ስልጣን በውስጡ አስፈላጊ የሆኑ ተጓዳኝ ስልጣናትን ያቅፋል፡፡





ለምሳሌ በተሽከርካሪ አደጋ የሶስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁ. 799/2005 አንቀጽ 13 ላይ እንደተመለከተው አንድ ተሽከርካሪ የመድን ተለጣፊ ምልክት ከሌለው የመድን ሽፋን እንደሌለው ስለሚያስቆጥረው የመድን ዋስትና ሰርተፊኬት እስኪመጣ ድረስ ፖሊስ ተሽከርካሪውን ይዞ የማቆየት ስልጣን አለው፡፡ በዚህ ድንጋጌ የፖሊስ የስልጣኑ ወሰን ጠባብ ነው፡፡ መኪናውን ከመያዝና ለማቆያ በተዘጋጀ ስፍራ ላይ ከማስቀመጥ ውጪ ሊወስድ የሚችለው ተጓዳኝ እርምጃ የለም፡፡





ይህንን የፖሊስ ስልጣን አካባቢንና ብክለትን የመቆጣጠር ኃላፊነት ካለባቸው አካላት ስልጣን ጋር ብናነጻጽረው ልዩነቱ በግልጽ ይታያል፡፡ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ወይም የሚመለከተው የክልል ባለስልጣን በአካባቢ ላይ አደጋ እንዳያስከትል ከሚያሰጋ የስራ እንቅስቃሴ ሊመጣ የሚችል ጉዳትን ለመከላከል ድርጅትን እስከ መዝጋት ወይም ወደ ሌላ ቦታ እስከማዛወር የሚደርስ ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡ ድርጅትን እስከመዝጋትና ወደ ሌላ ቦታ እስከማዛወር የሚደርስ ስልጣን ድርጅቱን የማሸግና ሠራተኞች እንዳይገቡ የመከልከል እንዲሁም ጉዳት ለመቀነስ የሚያስፈልጉ ተጓዳኝ እርምጃዎችን የመውሰድ ስልጣን ጭምር ያካትታል፡፡





የህጉ ዓላማ





የህጉ አጠቃላይ ዓላማና ግብ በግልጽ ከተቀመጠው ስልጣን በተጨማሪ የህጉን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ ስልጣናት ስለመኖራቸው አመላካች ነው፡፡ ተጓዳኝ ስልጣን ሳይኖር የህጉን ዓላማ በተግባር ማሳካት የማይቻል ከሆነ በዝምታ የተሰጠ ስልጣን ስለመኖሩ ግምት ይወሰድበታል፡፡





የድርጊቱ ዓይነትና /ባህርይ/ ይዘት





በግልጽ የተሰጠው ስልጣን ማዕቀብ የሚጥል ድርጊት ወይም እርምጃ ከሆነ ተጓዳኝ ስልጣን ስለመኖሩ በጠባቡ መተርጐም ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ የመቆጣጠር ስልጣን በውስጠ ታዋቂነት የመከልከል ስልጣንን አይጨምርም፡፡




Oct 24, 2020

መሰረታዊ የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች።

መሰረታዊ የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች

መልካም አስተዳደር ምንም እንኳን በጥቅሉ ሲታይ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ተቋማዊ እንዲሁም የአመራር እና የአሰራር ሂደቶችን የሚመለከቱ ዘርፈ ብዙ እንደምታዎች ያሉት ቢሆንም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሲታይ ግን ከአስተዳደር ፍትህ ጋር አቻ ሆኖ ሊገለጽ ይችላል፡፡ መልካም አስተዳደር ዋና ግቡ ዜጐች ብቁና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንዲሁም የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደል መቅረፍ እና አስተዳደራዊ ፍትህን እውን ማድረግ እንደመሆኑ ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት ያስቸግራል፡፡ መልካም አስተዳደር ሆነ የአስተዳደር ህግ በራሳቸው አቅጣጫና ሂደት ተጉዘው የግባቸው መድረሻ አስተዳደራዊ ፍትህን ማስፈን ነው፡፡ ስለሆነም በይዘቱ ሰፊ በሆነ የመልካም አስተዳደር እሳቤ ውስጥ የአስተዳደር ህግ አንድ ቁስ ሆኖ በማገልገል የተቆራኘና የተዛመደ ተግባራዊ እገዛ ያደርጋል፡፡

በመልካም አስተዳደርና በአስተዳደር ህግ መካከል ያለውን ተዛምዶ በቅጡ ለመቃኘት ህግ በአስተዳደሩ አካሄድ (Administrative behavior) ወይም በስራ አስፈፃሚው እንቅስቃሴ ላይ ምን አይነት አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ በተግባር የታገዘ ጥልቅ ጥናት ምላሽ መስጠት ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ሚናዎችና ተግባራት ቢያንስ እንደጠቅላላ ሀሳብ በመውሰድ የአስተዳደር ህግ እንደ አንድ የህግ ዘርፍ የራሱ አዎንታዊ ፋይዳ እንዳለው መደምደም እንችላለን፡፡

ያም ሆኖ ግን አስተዳደሩ መልካም እንዲሆን የአስተዳደር ህግ ስልጣን ከመቆጣጠር ባሻገር እንዴት ተቃኝቶ መቀረጽ አለበት? የሚለው ጥያቄ ለአስተዳደር ህግ አጥኚዎች ሆነ ምሁራን የውይይት ምንጭ ብቻ ሳይሆን የጥናት መሰረት መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
የመልካም አስተዳደር እና የአስተዳደር ህግን ተዛምዶ ለማየት የሁለቱም መድረሻ ከሆነው የአስተዳደር ፍትህ ትርጓሜ እንነሳለን፡፡

የአስተዳደር ፍትህ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው የመንግስት አካላት ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ወቅት ከዜጐች መብትና ነፃነት አንጻር ፍትሃዊ መሆን እንዳለባቸው የሚደነግግ መርህ ነው፡፡

የመንግስት አስተዳደር ፍትሃዊ ሲሆን መልካም ይሆናል፡፡
የአስተዳደር ፍትህን በማሳካት ረገድ ሁለት ዓበይት ነጥቦች ቁልፍ ቦታ ይኖራቸዋል፡፡ ይኸውም፡-

አንደኛ፦

የመንግስት ባለ ስልጣናት ወይም የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ወቅት አነስተኛ ለሆኑ የስነ-ስርዓት ደንቦች እና ተቀባይነት ላላቸው መርሆዎች መገዛት አለባቸው፡፡

ከአነስተኛ የስነ-ስርዓት ደንቦች በተጨማሪ የመንግስት አስተዳደር ተቀባይነት ባላቸው የህግ፣ የአስተዳደርና የፍትህ መርሆዎች መመራት አለበት፡፡
ከእነዚህ መካከል በዋናነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
የህጋዊነት መርህ (ህጋዊ ስልጣን ሳይኖር አንዳችም እርምጃ አለመውሰድ፤ በህጉ መሰረት መወሰን)
የሚዛናዊት መርህ (የአስተዳደር አካላት ውሳኔ ወይም እርምጃ እንደየሁኔታው ብዙ ነገሮች ግምት ያስገባ እንጂ ፍርደገምድል መሆን የለበትም፡፡)
የተመጣጣኝነት መርህ (የሚወሰደው እርምጃ ተፈጸመ ከተባለው ጥፋት አንፃር ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡)
የእኩልነት መርህ (ተመሳሳይ በሆኑ ሁኔታዎች ወይም ጉዳዮች አስተዳደሩ የተለያየ ውሳኔ ላይ መድረስ የለበትም፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታዎች በተመሳሳይ መንገድ መወሰን አለባቸው፡፡)
ለውሳኔ በቂ ምክንያት መስጠት (አስተዳደራዊ ውሳኔ የተወሰደበት ምክንያት በግልጽ መጠቀስ አለበት፡፡ ውሳኔውም ፈጽሞ የማያሳምንና ኢ- ምክንያታዊ መሆን የለበትም፡፡)

ሁለተኛ፦

ከላይ የተመለከቱትን ደንቦችና መርሆዎች በመጻረር በህግ ከተወሰነው ስልጣን በላይ እርምጃ ከተወሰደ መብታቸው የተጐዳ ዜጐች አቤቱታ አቅርበው ፍትህ (መፍትሄ) የሚያገኙበት መንገድ መኖር አለበት፡፡ በአስተዳደር አካላት መብታቸው የተጣሰ ሰዎች ቀላል በሆነ ስነ-ስርዓት አቤቱታ አቅርበው ቀልጣፋ መፍትሔ የሚያገኙበት አሰራር ወይም መንገድ ከሌለ የአስተዳደር ፍትህ አለ ለማለት አይቻልም፡፡
ለምሳሌ አካልን ነፃ የማውጣት መብት በህገ-ወጥ መንገድ ከ48 ሰዓት በላይ የታሰረ ሰው ራሱ በቀጥታ ወይም በሌላ ሶስተኛ ወገን በቀላሉ አቤቱታ አቅርቦ ነፃ የሚለቀቅበት ፈጣን ስነ-ስርዓት ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በህገ ወጥ መንገድ ንብረቱን በአስተዳደደሩ የተቀማ ወይም ፈቃዱ አለአግባብ የተሰረዘበት ሰው ቀላል በሆነ
ስነ-ስርዓት መፍትሔ የሚያገኝበት የህግ ድንጋጌ ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህም ነው የአስተዳደር ህግ መኖር ለአስተዳደራዊ ፍትህ ሆነ ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ መሳሪያ ነው የሚባለው፡፡ የአቤቱታው ስርዓት እንዳለ ሆኖ የአስተዳደራዊ ፍትህ የሚገኝበት ተቋም ገለልተኛ፣ ተደራሽ እና ነፃ ሆኖ ቀልጣፋና ውጤታማ ግልጋሎት መስጠት መቻሉ የአስተዳደር ፍትህን በማሳካት ረገድ ዋናውና መሰረታዊው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡


የአስተዳደር ህግ እና የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም።

የአስተዳደር ህግ እና የሰብዓዊ መብት አፈፃፀም

ተደጋግሞ እንደተገለፀው የመንግስት ስልጣን በወርድም በቁመትም እየሰፋ በመጣ ቁጥር ለዜጐች መብትና ነፃነት ፀር ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ የስልጣንን አስፈላጊነት አምኖ ተቀብሎታል፡፡ ውጤታማ አስተዳደር እንዲሁም ቀልጣፋ የአገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስር ሳይሆን የሚፈታ ስልጣን ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ከህግና ከህገ መንግስት የሚያፈነግጥ ስልጣን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የበዘፈቀደ ድርጊት፣ ‘እንደፈለግኩኝ እሆናለው እፈልጣለው እቆርጣለው!’ የሚል አካሄድ አቅመ ቢስ የሆነውን ዜጋ የመኖር፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመናገር፣ ሀሳብን የመግለፅና ንብረት የማፍራት መሰረታዊ መብት አለገደብ ይሸረሽራል፡፡
የአስተዳደር ህግ የሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅ ረገድ ያለው ሚና የሁለቱን ትስስር በሚገባ ያሳየናል፡፡ ህጉ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅና አፈፃፀም ላይ ያለውን አዎንታዊ ተፅእኖ በሚገባ ለመረዳት ከሰብዓዊ መብቶች አተገባበር አንፃር የመንግስትን ግዴታ መተንተኑ አግባብነት ይኖረዋል፡፡ እነዚህም ሚናዎች (ግዴታዎች) የማክበር (respect) የማስከበር (protect) እንዲሁም የመፈጸምና የማስፈፀም (enforcement) ናቸው፡፡
በመጀመሪያው መብቶችን የማክበር የመንግስት ሚና ዜጐች ነፃ ሆነው መብታቸውን ሲጠቀሙ ከየትኛውም የመንግስት አካል የሚመጣ ጣልቃ ገብነትን ይገድባል፡፡ በተለይም መሰረታዊ በሚባሉት በህይወት የመኖር፣ የመፃፍ፣ የመናገር፤ የፈለጉትን ሀይማኖት የመከተል፤ በነፃነት የመዘዋወርና ንብረት የማፍራት መብቶችና ነፃነቶች በተግባር የሚረጋገጡት መንግስት እጁን ሲሰበስብ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች በመንግስት በተለይ በስራ አስፈፃሚውና በስሩ ባሉት የአስተዳደር ተቋማት ውሳኔ፤ ትዕዛዝ፤ ደንብና መመሪያ አማካይነት አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ ህገ መንግስቱ የበላይ ህግ እንደመሆኑ ይህን የሚቃረን ህግ፣ ውሳኔና አሰራር ሁሉ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ይህን መሰሉ የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ በአስተዳደር ህግ ውስጥ አይወድቅም፡፡ ይሁን እንጂ የህገ መንግስታዊነት ብቻ የሚመስል ጥያቄ በአስተዳደር ህግ ማእቀፍ የሚሸፈንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡
በአንድ የአስተዳደር ተቋም የወጣ መመሪያ በህግ አውጭው ከተሰጠ የውክልና ስልጣን በማለፍ የዜጐችን ሰብዓዊ መብት የሚገድብ ሆኖ ከተገኘ በውስጡ የህገ መንግስታዊነት (constitutionality) ጥያቄ ያዘለ ቢሆንም በዋናነት ግን የአስተዳደር ህግ ሊመልሰው የሚገባ የህጋዊነት (legality) ጥያቄ ነው፡፡ ልዩነታቸውን የበለጠ መረዳት እንዲያስችልን የሚከተለውን የድሮው የገቢዎች ሚኒስቴር የአሁኑ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መመሪያ እንመልከት፡፡
ማንኛውም የጉምሩክ ፖሊስ ሰላማዊ ስልፍና የስራ ማቆም አድማ ማድረግ አይችልም፡፡
ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ለማንኛውም ሰው የተረጋገጠ መብት ነው፡፡ መብቱን የሚያጎናጽፈው የአንቀጽ 30 ንዑስ ቁጥር 1 እንዲህ ይነበባል፡፡
ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡
አንድ መመሪያ በስራ አስፈፃሚው አካል ሲወጣ ከህግ አውጭው በግልጽ የተሰጠ የውክልና ስልጣን (Delegation) ሊኖር ይገባል፡፡ መመሪያው የውክልና ስልጣኑን ገደብ ካለፈ ከስልጣን በላይ (Ulta vires) ነው፡፡ ስለሆነም በህግ ፊት ዋጋ አልባ (null and void) ነው፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ይህን መመሪያ ሲያወጣ የስልጣን ምንጩን የጉምሩክ ባለስልጣንን ለማቋቋምና አስራሩን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁ. 368/1995 አንቀጽ 8 (2) (ሐ) እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ይህ የተጠቀሰው የህግ ድንጋጌ እንዲህ ይነበባል፡፡
የጉምሩክ ህግ እንዲያስከብር ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተመደበን የፖሊስ ኃይል ሚኒስቴሩ የፌደራል ፖሊስ አዋጅን ተከትሎ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት በስራ ያሰማራል፡፡ ያስተዳድራል፡፡ ጥፋት ሲገኝም ያሰናብታል፡፡
ይህ አንቀጽ የጉምሩክ ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ በመመሪያ እንዲከለክል ለገቢዎች ሚኒስቴር ስልጣን አይሰጥም፡፡ ከተወካዮች ምክር ቤት ግልፅ ስልጣን ባልተሰጠበት ሁኔታ የወጣው ይህ መመሪያ ህጋዊነት ሆነ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ የአስተዳደር ህግ ይህን መሰል መመሪያዎች በዘፈቀደ እየወጡ የዜጐችን መብትና ነፃነት እንዳይጥሱ በተለያዩ መንገዶች በመቆጣጠር መንግስት ሰብዓዊ መብት የማክበር ግዴታውን እንዲወጣ ያደርጋል፡፡
የመንግስት የማስፈፀም ኃላፊነት አብዛኛውን ጊዜ ከማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች ጋር በቀጥታ ተያይዞ ይነሳል፡፡ መንግስት በዜጐች መብት ላይ ጣልቃ አለመግባቱ ወይም እጁን መሰብሰቡ ብቻ አይበቃም፡፡ ለዜጋው መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማለትም ጤና፣ መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ ወዘተ… ካላቀረበ ነፃ መሆን በራሱ ፋይዳ የለውም፡፡
የአስተዳደር ህግ እና የሰብዓዊ መብት ትሰስር ከመንግስት የማስከበር ግዴታ አንጻርም ሊቃኝ ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት ሰብዓዊ መብትን በማስከበር ኃላፊነቱ መብት እንዳይጣስ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶች በህግ እና በተቋማዊ አደረጃጀት የማጠናከር፣ በመብት መጣስ ጉዳት ለደረሰበት ዜጋ ፈጣን ፍትህ የሚያገኝበትን ስርዓት መዘርጋት አለበት ማለት ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ መንግስት የዳበረ የአስተዳደር ህግ እና የአስተዳደር ህግ ስርዓት መቅረጽ፣ መትከልና ማጐልበት ይጠበቅበታል፡፡


ግልጽና ተጓዳኝ ስልጣን

ግልጽና ተጓዳኝ ስልጣን
አብዛኛውን ጊዜ ለመንግስት አካላት የሚደለደለው ስልጣን አሻሚ ባልሆነ አነጋገር ይገለጻል፡፡ ግልጽና ቀጥተኛ ስልጣን በአስተዳደሩ ውስጥ ህጋዊነትን ያሰፍናል፡፡ በተጨማሪም ስልጣንን በመገልገል ረገድ ጥርጣሬና ብዥታን ያስወግዳል፡፡ በተግባር ሲታይ ግን ለውጤታማ አስተዳደር አስፈላጊ የሆኑትን ስልጣናትና ተግባራት መዘርዘር ያዳግታል፡፡ ስለሆነም በግልጽ ስልጣን ውስጥ አስፈላጊ የሆነ በዝምታ የሚተላለፍ ተጓዳኝ ስልጣን ይኖራል፡፡ አንድን ድርጊት ለመፈፀም ግልጽ የሆነ ስልጣን ሲሰጥ የድርጊቱ አካል የሆኑና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል በዝምታ የሚሰጥ ስልጣን ስለመኖሩ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የህጉን ዓላማና ግብ እንዲሁም የህጉን ድንጋጌዎች አነጋገር በጥልቀት መፈተሽ ይጠይቃል፡፡ ተጓዳኝ ስልጣን መኖሩን ለመወሰን የሚከተሉት ነጥቦች ግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡
የህጉ አነጋገር
ይህ የህግ አውጭውን ሀሳብ ለማወቅ ወሳኝነት አለው፡፡ ለምሳሌ የመንግስት እና የግል ድርጅት ሠራተኞች ኤጀንሲዎች በሚያስፈጽሟቸው አዋጆች መሰረት ለማናቸውም ዓይነት አበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች መሟላታቸውን የማረጋገጥና የአበሉን ዓይነትና መጠን የመወሰን ስልጣን አላቸው፡፡ ለአበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በአዋጅ ቁ. 714/2003 እና 715/2003 የተለያዩ ድንጋጌዎች በዝርዝር ተለይተዋል፡፡ ኤጀንሲዎቹ እነዚህን ሁኔታዎች መኖራቸውን የመወሰን ስልጣናቸው ክርክር አያስነሳም፡፡ ለምሳሌ በአዋጅ ቁ. 714/2003 አንቀጽ 41 መሰረት ለሟች ሚስት ወይም ባል የሚከፈለው የጡረታ አበል ሟች ያገኝ ወይም ሊያገኝ ይችል የነበረው የጡረታ አበል 50 በመቶውን ነው፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ላይ ባል ወይም ሚስት የጡረታ አበል በመቀበል ላይ እያሉ ጋብቻ ከፈጸሙ አበሉ የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች ተመልክተዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች መወሰን በኤጀንሲዎቹ ስልጣን ስር ቢሆንም የባልነት ወይም ሚስትነት ጥያቄ በተነሳ ጊዜ ይህንን ማረጋገጥ ከስልጣናቸው ክልል በላይ ነው፡፡ ይህን መወሰን በመደበኛ የዳኝነት አካላት ስልጣን ስር ይወድቃል፡፡ ስለሆነም ‘ለአበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች’ የሚለው አነጋገር በሁለቱም አዋጆች ላይ መለኪያና መስፈርት የተቀመጠላቸውን ሁኔታዎች እንጂ በሌሎች ህጎች የሚወሰኑትን አያካትትም፡፡ የህግ አውጨው ሀሳብም ኤጀንሲዎቹ ለአበል ብቁ የሆኑ የሟች ሚስት ወይም ባል የሚከፈላቸውን መጠንና እና ክፍያውን የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎች እንዲወስኑ እንጂ ከመነሻው ባልነት ወይም ሚስትነትን በተመለከተ ማስረጃ አሰባስበው ውሳኔ እንዲሰጡ አይደለም፡፡
በግልጽ የተሰጠው ስልጣን ወሰን
ስልጣኑ በጠባቡ ከተሰጠ ተጓዳኝ ስልጣን ስለመኖሩ በጠባቡ መተርጐም ይኖርበታል፡፡ በአንጻሩ ሰፊ የሆነ ስልጣን በውስጡ አስፈላጊ የሆኑ ተጓዳኝ ስልጣናትን ያቅፋል፡፡
ለምሳሌ በተሽከርካሪ አደጋ የሶስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁ. 799/2005 አንቀጽ 13 ላይ እንደተመለከተው አንድ ተሽከርካሪ የመድን ተለጣፊ ምልክት ከሌለው የመድን ሽፋን እንደሌለው ስለሚያስቆጥረው የመድን ዋስትና ሰርተፊኬት እስኪመጣ ድረስ ፖሊስ ተሽከርካሪውን ይዞ የማቆየት ስልጣን አለው፡፡ በዚህ ድንጋጌ የፖሊስ የስልጣኑ ወሰን ጠባብ ነው፡፡ መኪናውን ከመያዝና ለማቆያ በተዘጋጀ ስፍራ ላይ ከማስቀመጥ ውጪ ሊወስድ የሚችለው ተጓዳኝ እርምጃ የለም፡፡
ይህንን የፖሊስ ስልጣን አካባቢንና ብክለትን የመቆጣጠር ኃላፊነት ካለባቸው አካላት ስልጣን ጋር ብናነጻጽረው ልዩነቱ በግልጽ ይታያል፡፡ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ወይም የሚመለከተው የክልል ባለስልጣን በአካባቢ ላይ አደጋ እንዳያስከትል ከሚያሰጋ የስራ እንቅስቃሴ ሊመጣ የሚችል ጉዳትን ለመከላከል ድርጅትን እስከ መዝጋት ወይም ወደ ሌላ ቦታ እስከማዛወር የሚደርስ ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡ ድርጅትን እስከመዝጋትና ወደ ሌላ ቦታ እስከማዛወር የሚደርስ ስልጣን ድርጅቱን የማሸግና ሠራተኞች እንዳይገቡ የመከልከል እንዲሁም ጉዳት ለመቀነስ የሚያስፈልጉ ተጓዳኝ እርምጃዎችን የመውሰድ ስልጣን ጭምር ያካትታል፡፡
የህጉ ዓላማ
የህጉ አጠቃላይ ዓላማና ግብ በግልጽ ከተቀመጠው ስልጣን በተጨማሪ የህጉን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ ስልጣናት ስለመኖራቸው አመላካች ነው፡፡ ተጓዳኝ ስልጣን ሳይኖር የህጉን ዓላማ በተግባር ማሳካት የማይቻል ከሆነ በዝምታ የተሰጠ ስልጣን ስለመኖሩ ግምት ይወሰድበታል፡፡
የድርጊቱ ዓይነትና /ባህርይ/ ይዘት
በግልጽ የተሰጠው ስልጣን ማዕቀብ የሚጥል ድርጊት ወይም እርምጃ ከሆነ ተጓዳኝ ስልጣን ስለመኖሩ በጠባቡ መተርጐም ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ የመቆጣጠር ስልጣን በውስጠ ታዋቂነት የመከልከል ስልጣንን አይጨምርም፡፡


የስልጣን ባህርይ እና መገለጫው

             የስልጣን ባህርይ እና መገለጫው
በአስተዳደር ህግ ውስጥ ስልጣን (power) የሚለው ጽንስ ሀሳብ ከአንድ አስተዳደራዊ ድርጊት በስተጀርባ ህጋዊ ብቃት መኖሩን ያመለክታል፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች ወይም የመንግስት ባለስልጣናት የአንድን ግለሰብ ወይም ድርጅት መብትና ጥቅም የሚነካ ድርጊት ሲፈፅሙ ይህን የሚፈቅድላቸው ከህግ የመነጨ ስልጣን ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ስልጣን ሁሉ ገደብ አለው፡፡ ይህ የአስተዳደር ህግ መነሻ ነው፡፡ የስልጣን ልኩና ገደቡ ካልተሰመረ የመንግስት አስተዳደር በህጋዊነት ማዕቀፍ ውስጥ አይከናወንም፡፡
ስልጣን የፍፁምነት ባህርይ የለውም፡፡ ፍፁም ስልጣን ዘውዳዊ (ንጉሳዊ) ስልጣን ብቻ ነው፡፡ ስልጣን ፍፁም ከሆነ የአስተዳደር ህግ ሆነ ህግ በጠቅላላው አያስፈልግም፡፡ ለዚህም ነው የስልጣን ገደብ የአስተዳደር ህግ መነሻና መሰረቱ ነው የተባለው፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር የስልጣን መገልገል በተለያዩ መለኪያዎች፤ ቅድመ ሁኔታዎች እና ስነ ስርዓቶች ገደብ ይበጅለታል፡፡ በስልጣን ላይ የሚደረግ ገደብ በተለያየ መልኩ ይገለጻል፡፡
ለአብነት በሚከተሉት ህጎች ላይ ስልጣን የተሰጠበትንና የተገደበበትን መንገድ እንመልከት፤
የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነትን በማወቅ በአስተዳደር ክፍል ለአንድ ሰው የተሰጠ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት ማስረጃው የተሰጠው ሰው የዚሁ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብት እንደሆነ እንደሚያስቆጥረው በፍ/ህ/ቁ. 1195/1/ ተመልክቷል፡፡ ሆኖም ይህ የሕሊና ግምት በ1196 ላይ የተዘረዘሩት የሚከተሉት ምክንያቶች መኖራቸው ማስረዳት ከተቻለ ፈራሽ ይሆናል፡፡
(ሀ) የባለርስትነት የምስክር ወረቀት የተሰጠው ከደንብ ውጭ በሆነ አሠራር ወይም ይህን ለመስጠት ሥልጣን በሌለው የአስተዳደር ክፍል የሆነ እንደሆነ
(ለ) የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት የተሰጠው በማይረጋ ጽሑፍ መሠረት የሆነ እንደሆነ ወይም ለከሳሹ መቃወሚያ ሊሆን በማይችል ጽሑፍ መሠረት የሆነ እንደሆነ
(ሐ) ከሳሹ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት ያገኘው፤ የገዛው የእርስት የምስክር ወረቀት ከተሰጠ በኋላ መሆኑን ማስረዳት የቻለ እንደሆነ
በፌደራል መንግስት የፋይናንስ አስተዳደር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁ. 879/2009 አንቀጽ 2/20/ በድሮው አዋጅ ቁ. 648/2001 ላይ ተጨማሪ ሆኖ በገባው አንቀጽ 73 መሰረት በማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተሾመ ወይም የተመደበ ሰው በአዋጆቹና አዋጆቹን ተከትለው በወጡት ደንብ እና መመሪያዎች መሠረት እንደሁኔታው ዕቅድ ወይም የሂሣብ ሪፖርት ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴሩ ወይም ለውጭ ኦዲተር ያላቀረበ ወይም መቅረቡን ያላረጋገጠ ወይም በውጭ ኦዲት ወይም በውስጥ ኦዲት ሪፖርት በተመለከተው መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ ያልወሰደ ወይም እርምጃ መወሰዱን ያላረጋገጠ እንደሆነ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ከብር 5 ሺ እስከ ብር 10 ሺ በሚደርስ ቅጣት ይቀጣል፡፡
የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ በአዋጅ ቁ. 923/2008 አንቀጽ 42/2/ ስር የተመለከተውን ጥፋትa መፈጸሙ ሲረጋገጥ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የሚከተሉትን ፈቃድ የማገድ አስተዳደራዊ እርምጃዎች የመውሰድ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡
ሀ) ድርጊቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለሦስት ወር፣
ለ) ድርጊቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለስድስት ወር፣
ሐ) ድርጊቱ ለሦስተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለአሥራ ሁለት ወር፣
ከላይ በምሳሌነት የቀረቡት ድንጋጌዎች በአጠቃላይ ይዘታቸው ስልጣን ሰጭ ቢሆኑም በዝርዝር ሲፈተሹ የስልጣኑን ገደብ ጭምር ያሰምራሉ፡፡ በፍ/ህ/ቁ. 1196 (ተ.ቁ. 1) የተዘረዘሩት ሶስት ሁኔታዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመሰረዝ ስልጣን በተሰጠው አካል ላይ የተቀመጡ ገደቦች ናቸው፡፡ ስረዛው ህጋዊነት እንዲኖረው በሁኔታዎቹ ስር ያሉ የፍሬ ነገር እና የህግ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ የምሰክር ወረቀቱ ከደንብ ውጭ በሆነ አሠራር ተሰጥቷል በሚል ለመሰረዝ መጀመሪያ ለዚሁ ዓላማ ተብሎ የወጣ ደንብ መኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡ በመቀጠል በምስክር ወረቀቱ አሰጣጥ ላይ ደንቡን በሚቃረን መልኩ የተፈጸመው ተግባር ምን እንደሆነ ተለይቶ መታወቅና በማስረጃ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ከደንብ ውጭ የሆነው አሰራር ምስክር ወረቀቱን ለማሰረዝ የሚያበቃና መሰረታዊ ካልሆነ የመሰረዝ እርምጃው የሚወሰድበት አሳማኝ ህጋዊነት ምክንያት የለም፡፡ ለምሳሌ የቴምብር ቀረጥ ሳይከፈል ከተረሳ ክፍያው ሊፈጸም ይገባል እንጂ በዚህ እንጭፍጫፊ ምክንያት ብቻ የስረዛ እርምጃ ሊወሰድ አይገባም፡፡
በተራ ቁ. 2 ላይ እንዲሁ እያንዳንዱ ሐረግ የስልጣን ገደብን ይወስናል፡፡ በመጀመሪያ በመንግሥት መሥሪያ ቤት የተሾመው ወይም የተመደበ ሰው ሪፖርት የማቅረብ፣ እንዲቀርብ የማስደረግና በሪፖርቱ መሰረት ማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ስልጣንና ተግባሩ ስለመሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ከዚያም አልፎ ግዴታውን ስላለመወጣቱ በፍሬ ነገር ረገድ በበቂ ማስረጃ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ፍሬ ነገሮቹም ግዴታውን ስላለመወጣቱ አሳማኝ ድምዳሜ ላይ የሚያደርሱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ግልጽ ከሆነው ገደብ በተጨማሪ በቅጣት አወሳሰኑ ላይ ህግ አውጭው በተዘዋዋሪ ማዕቀብ አድርጓል፡፡ የቅጣ መጠኑ ከ5 ሺ እስከ 10 ሺ ብር ድረስ እንደመሆኑ የጥፋቱ ደረጃ እና ቅጣቱ ሚዛናዊ በሚባል መልኩ የተመጣጣኝነትን መለኪያ ማሟላት ይኖርበታል፡፡
በተራ ቁ. 3 ላይ ጥፋት ተብሎ በህጉ የተዘረዘረው ድርጊት በማስረጃ ሊደገፍና ቅጣቱ ሲወሰን ቅደም ተከተሉን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ከድንጋጌው ይዘት ከሚመዘዙት ገደቦች በተጨማሪ በአዋጁ ሌሎች ድንጋጌዎች ላይ ውሳኔ ሰጭው ስልጣኑን ሲገለገል ሊከተላቸው የሚገቡ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ተዘርግቷል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 26 በተቀመጠው ስርዓት መሰረት መብቴ ተጥሷል የሚል ሰራተኛ አቤቱታውን አዘጋጅቶ ሲያቀርብ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የአቤቱታውን ቅጂና ደጋፊ ሰነዶች በማያያዝ አቤቱታ የቀረበበት ኤጀንሲ በአሥር የሥራ ቀናት ውስጥ መልሱን በጽሁፍ እንዲያቀርብ የመጥሪያ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ የመጥሪያ አሰጣጥ ስርዓቱ በአዋጁ ላይ ባይጠቀስም ድንጋጌው የተከሳሹን የመሰማት መብት የማስጠበቅ ዓላማ ያለው እንደመሆኑ መጥሪያው በአግባቡ ሊደርሰው ይገባል፡፡ መጥሪያ ሳይላክና ተከሳሹ ደርሶት መልሱን ሳያቀርብ ሚኒስቴሩ ወይም ባለስልጣኑ በራሱ አነሳሽነት ቅሬታ የቀረበበትን ድርጊት አጣርቶ የሚወስደው እርምጃ ህገ ወጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ተከሳሹ ሳይሰማ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በአዋጁ ስልጣን አልተሰጠውም፡፡


የመሻሪያና የክልከላ ትዕዛዝ

              የመሻሪያና የክልከላ ትዕዛዝ
የመሻሪያ ትዕዛዝ (Certiorari) ማለት የበላይ የሆነ ፍርድ ቤት ለሥር ፍርድ ቤት ወይም አስተዳደር ፍርድ ብሎም ሌላ ውሳኔ ሰጭ አካል ውሳኔ የተሰጠበትን መዝገብ እንዲልክለት የሚያስገድድበትና በመቀጠልም ውሳኔው ህጋዊ ስርዓት ተከትሎ በህግ በተፈቀደ የስልጣን ወይም ክልል ውስጥ መሰጠቱ የሚመረመርበት፣ ከስልጣን በላይ ሆኖ በተገኘ ጊዜም የሚሻርበትና ዋጋ የሚያጣበት የመፍትሄ አይነት ነው፡፡a ከትርጉሙ መረዳት እንደምንችለው የመሻሪያ መፍትሄ በሁለት ደረጃዎች የተከፈለ ነው፡፡
የመጀመሪያው ደረጃ የውሳኔውን ሂደት የሚያሳየውን መዝገብ እንዲላክለት የበላይ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ትዕዛዝ ነው፡፡ ይህ ከተሟላ በኋላ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ይተላለፋል፡፡ የበላይ ፍርድ ቤት መዝቡንና ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ከስልጣን ውጭ ወይም በስልጣን አለአግባብ መገልገል መፈጸሙን ካረጋገጠ እንዲሻር ውሳኔ ያስተላልፋል፡፡ ውሳኔው ይሻራል ሲባል ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ የመሻሪያ ትዕዛዝ ከስልጣን በላይ (Ultra vires) ወይም ከዳኝት ስልጣን ክልል ውጭ (Jurisdication error) የተፈጸም ተግባር የሚሻርበትና ዋጋ የሚያጣበትን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ውጤቱ ጥያቄ የተነሳበትን ተግባር እስከመሻር ድረስ ብቻ ነው፡፡ የበላይ ፍርድ ቤት ከዚህ አልፎ በጉዳዩ ይዘት ወይም በፍሬ ነገሩ ላይ ውሳኔ አያስተላልፍም፡፡ በሌላ አነጋገር የበላይ ፍርድ ቤቱ በተሻረው ውሳኔ ፈንታ የራሱን ፍርድ አይሰጥም፡፡
የክልከላ ትዕዛዝን ያየን እንደሆነ አፈጻጸሙ ከመሻሪያ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ውጤቱ ግን ከስልጣን በላይ ወይም ከዳኝት ስልጣን ክልል ውጭ የሆነ ድርጊት ወይም ውሳኔ ለወደፊት እንዳይሰጥ፣ ተጀምሮ ከሆነም ባለበት እንዲቆም ያደርጋል፡፡b ስለሆነም በፍትሐብሔር ሕግ ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነት ላይ ከተቀመጠው የዕግድ ትዕዛዝ ጋር ይመሳሰላል፡፡ በመሻሪያ እና ክልከላ መካከል ያለው ልዩነት የጊዜ ልዩነት ነው፡፡ ይህም ማለት የመሻሪያ ትዕዛዝ የተፈጸመውን አስተዳደራዊ ተግባር ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ ስለሚያስቆጥረው የተፈጸሙ ተግባራት ወደ ቀድሞው ቦታቸው ይመለሳሉ፡፡ በአንጻሩ የክልከላ ትዕዛዝ አንድ ድርጊት ወደፊት እዳይፈጸም የተጀመረ ካለም እንዳይቀጥል በዚህም ነገሮች ባሉበት እንዲረጉ ያደርጋል፡፡
ሁለቱም የፍትሐብሔር መፍትሄዎች ባለመሆናቸው ራሱን በቻለ ዝርዝር የአጣሪ ዳኝነት የስነ-ስርዓት አካሄድ መሰረት ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡ መፍትሄዎቹ የሚሰጡበት የህግ መሰረት እና የሥነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ከአገር አገር የተለያዩ ቢሆንም ሁለቱም በአንድ አቤቱታ በአማራጭ ወይም በማዳበል ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ ታሪካዊ አመጣጣቸው ሲታይ በእንግሊዝ የበላይ ፍ/ቤቶች የስር ፍ/ቤቶችን እና የአስተዳደር ጉባዔዎችን ከመቆጣጠር ስልጣናቸው የመነጩ ናቸው፡፡ ኋላ ላይ ግን በአስተዳደር ውሳኔ ሰጭ አካላት ላይም ተፈጻሚ ተደርገዋል፡፡
የመፍትሄዎቹ መኖር የፖሊሲ መሰረቱ ማንኛውም ውሳኔ ሰጭ አካል በህግ አውጭው ከተሰጠው የሥልጣን ወይም የዳኝነት ስልጣን ክልል አልፎ የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ውሳኔ መስጠት ወይም ድርጊት መፈፀም የለበትም የሚለው የህግ የበላይነት ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ አንደኛው የህግ የበላይነት መርህ ህጋዊነት ነው፡፡ ህጋዊነት የሚረጋገጠው ማንኛው በህግ ስልጣን የተሰጠው አካል በህግና በህጉ መሰረት ብቻ ውሳኔ መስጠቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በህግ ከተፈቀደው የሥልጣን ገደብ በላይ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች የግለሰቦችን መብት መጣሳቸው አይቀርም፡፡ ስለሆነም ፍ/ቤቶች ጣልቃ በመግባት ህገ ወጥ የሆነውን ድርጊት መሻር ብሎም ሊፈፀም እርግጥ የሆነው ደግሞ አንዳይፈጸም የመከልከል ዳኝነታዊ ግዴታ አለባቸው፡፡
ክልከላን በተመለከተ አመልካቹ ማሳየት የሚጠበቅበት ውሳኔ ሰጭው አካል ከስልጣኑ በላይ አንድ ድርጊት መፈጸም መጀመሩን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቀድሞውኑ ከስልጣን በላይ በሆነ ውሳኔ ላይ ተመስርቶ አፈጻጸም እንደቀጠለ ማሳየትም በቂ ሊሆን ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ከስራ ማስወጣትን የተመለከቱ የሥራ ክርክሮችን ማየትና የዳኝነት መስጠት አይችልም፡፡ እንበልና ይህ የክልከላ መፍትሄ በአገራችን የአስተዳደር ህግ ውስጥ ቢኖር ቦርዱ በሰራተኛ የቀረበ ከስራ የማስወጣት የክስ አቤቱታ ተቀብሎ መጥሪያ ለተከሳሹ በላከበት ደረጃ ላይ በበላይ ፍ/ቤቱ የክልከላ ትዕዛዝ ሊሰጥበት ይችላል፡፡ ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተ ማከራከር በጀመረበት በማንኛውም ደረጃ ላይም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ቦርዱ ውሳኔ የሰጠ እንደሆነ በበላይ ፍ/ቤት ሊሰጥ የሚችለው መፍትሄ ክልከላ ሳይሆን የመሻሪያ ትዕዛዝ ነው፡፡ ውጤቱም የቦርዱን ውሳኔ ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ እንዲቆጠር ያደርገዋል፡፡


የመግለጫ (ማስረገጫ) ትዕዛዝ

የመግለጫ (ማስረገጫ) ትዕዛዝ
የመግለጫ ትዕዛዝ (declaration, or declaratory judgment) በሁለት ወገኖች መካከል ያለውን የህግ አቋም በተመለከተ ፍ/ቤቱ መግለጫ የሚሰጥበት የትዕዛዝ ወይም የውሳኔ ዓይነት ነው፡፡a በይዘቱ ከህግ ትርጓሜ የሚመነጭ ግዴታ ወይም መብት ከማስረገጥ ወይም ህጋዊነትና ህገወጥነት ሁኔታ ወይም አቋም ከመደንገግ ወይም ከማስረገጥ ባለፈ አስገዳጅነት የለውም፡፡ ስለሆነም ትዕዛዙን አለማክበር በፍ/ቤት ንቀት ቅጣት አያስከትልም፡፡b
ከስልጣን በላይ ወይም ህገ ወጥ በሆነ ድርጊት ምክንያት አንድ ሰው ለወደፊት በንብረቱና በነፃነቱ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ለሚችል ውሳኔ ሊዳረግ ይችላል፡፡ ውሳኔው እንዳይሰጥ ከተፈለገ አንደኛው አማራጭ በክልከላ ወይም በዕግድ ትዕዛዝ ማስቆም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም የመፍትሄ አይነቶች የራሳቸው የሆነ ልዩ ቅድመ ሁኔታና የሥነ-ስርዓት ድንጋጌዎች አሏቸው፡፡ ቀላሉ መንገድ የመብቱን መኖርና አለመኖር፣ የድርጊቱን ከስልጣን በላይ መሆን አለመሆን ወይም ሌላ ህጋዊ አቋም በፍ/ቤቱ እንዲፀና ወይም መግለጫ እንዲሰጥበት ዳኝነት መጠየቅ ነው፡፡
በዚህ መልኩ ጥያቄ ማቅረብ ተመራጭ የሚያደርገው አመልካቹ ሌሎች የአስተዳደር ህግ መፍትሄዎችን ለማግኘት ማሟላት ያለበት ዝርዝር ቅድመ ሁኔታ እንዲያሳይ አይጠበቅበትም፡፡ ፍ/ቤትም አብዛኛውን ጊዜ ትዕዛዙን ለመስጠት አያመነታም፡፡ በተጨማሪም በመግለጫ የሚረጋገጠው የህግ ሁኔታ ለቀጣይ መፍትሄ መሰረት ይጥላል፡፡ ሌላው ጠቀሜታው ደግሞ በአመልካቹና ጥያቄ በቀረበበት አካል መካከል የከረረ ሙግት ስለማይኖር ሰላማዊ የችግር መፍቻ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡c
የመግለጫ ትዕዛዝ እስከ ቅርቡ 20ኛው ክፍ ዘመን ድረስ የአስተዳደር ተቋማትን በፍ/ቤት የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ሆኖ ብቅ አላለም፡፡d በአጣሪ ዳኝነት የመፍትሄ ማዕቀፍ ውስጥ ከተጠቃለለ ወዲህ ግን ከሌሎች የመፍትሄ አይነቶች እጅግ በጣም በፈጠነ መልኩ ተቀባይት አግኝቷል፡፡
መግለጫ ራሱን እንደ ቻለ ውሳኔ በአገራችን አልተለመደም፡፡ በመደበኛው የፍትሐብሔር ጉዳይ ተቀራራቢ ይዘት ኖሮት ተፈጻሚነት ቢያገኝም በአስተዳደራዊ ክርክር ውስጥ ግን ጥያቄው የተነሳበት ሆኖ ትዕዛዙ የተሰጠበት አጋጣሚ የለም፡፡ የወራሽነት ምስክር ወረቀት፣ የመጥፋት ውሳኔ መግለጫ እና የአባትነት ውሳኔ ፍርድ ቤት የመግለጫው ውሳኔ ከሚሰጥባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
በአስተዳደራዊ ክርክሮች በመግለጫ ብቻ ዳኝነት የሚሰጥባቸው የህግ ሁኔታዎች የሉም፡፡ መብት ለማረጋገጥ የሚቀርብ ክስ ከመነሻው የክስ ምክንያት ስለማይኖረው ውድቅ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 9 አንድ ሰራተኛ የውሉ ጊዜ በአንቀጽ 10 መሰረት ላልተወሰነ ጊዜ እንደተደረገ ቢቆጠርም በመብቱና በጥቅሙ ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ‘የሥራ ውሌ ላልተወሰነ ጊዜ እደተደረገ ይቆጠርልኝ’ የሚል ጥያቄ ሊያቀርብ ሆነ ውሳኔ ሊያገኝ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የተጠየቀው ዳኝነት የክስ ምክንያት የለውም፡፡ የመግለጫ ትዕዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ሰራተኛው በጥቅምና በመብቱ ላይ ጉዳት እስሚደርስ ድረስ ሳይጠብቅ ህጋዊ አቋሙ ማለትም የሥራ ውሉ ላልተወሰነ ጊዜ እንደተደረገ እንዲቆጠርለት ማረጋገጫ ይችል ነበር፡፡ ውሳኔው የፍ/ባለመብት ባያደርገውም ቀጣይ የመብት ጥሰቶችን በቀላሉ ለመቃወም ያስችለዋል፡፡
ትዕዛዙ በውጤቱ አስገዳጅነት የለውም፡፡ ቢሆንም የራሱ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ እንደ አንድ የዳኝነት ዓይነት ተቀባይነት ባገኘባቸው አገራት ፍርድ ቤት መብት፣ ግዴታ ወይም ህጋዊነት በማረጋገጥ የሚሰጠው ትዕዛዝ በውዴታ ይከበራል፡፡ አስተዳደራዊ በደልን ለመቅረፍ ከሙግት ይልቅ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ እንዲሉ በግለሰቡ መብትና ጥቅም ጉዳት ከመድረሱ በፊት የህግ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ማስረገጥ ከአስገዳጅ ፍርድ የበለጠ የጎላ ፋይዳ አለው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የመግለጫ ትዕዛዝ በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ የማይሰጥ ቢሆንም ባህርያቱን በሚከተለው መላምታዊ ምሳሌ ማየት እንችላለን፡፡ በባንክ ስራ አዋጅ ቁ. 592/2000 መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ መረጃዎች ከባንኮች እንዲቀርቡለት የማድረግ ስልጣን አለው፡፡ ሆኖም የየባንክ ደንበኞችን ስም፣ የትዳር ሁኔታ ሆነ ሌላ ግላዊ መረጃ መጠየቅ አልተፈቀደለትም፡፡ እንበልና የብሔራዊ ባንክ ህግ ከፈቀደለት ስልጣን ውጪ እያንዳንዱ ባንክ የተበዳሪዎቹን ግላዊ ሁኔታ ከብድር መዝገብ እየለቀመ ወይም ተበዳሪዎችን በአካል እየጠየቀ በአምስት ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲልክ፣ የማይልክ ከሆነ ግን ፈቃዱ እንደሚሰረዝ በማሳሰብ ለባንኮች ጥያቄ አቀረበ፡፡ ይህንን በመቃወም ባንኮች ቅሬታ በማሰማታቸው ከዚያም አልፎ የብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ህገ ወጥ ተብሎ የመግለጫ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ለፍርድ ቤት አመልክተው ቢሳካላቸው ትዕዛዙ በራሱ አስገዳጅ ውጤት አያስከትልም፡፡ ባንኮቹ በታዘዙት መሰረት ሪፖርት ባይልኩ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እንዳይሰርዝ አያግደውም፡፡ ሆኖም የሪፖርት ጥያቄው ህጋዊነት ከወዲሁ ስለሚታወቅ የመሰረዝ እርምጃውን በፍርድ ለማሻር ቀላል ያደርገዋል፡፡ ምናልባትም ባንኩ የህዝብ ጥቅም ለማስከበር ከቆመ ከሚደርስበት ህዝባዊ ወቀሳ ለመዳን ፈቃድ ከመሰረዝ የሚታቀብበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡


Popular Posts

DOCUMENTS

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd

Files

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ 2/ 2006 PDF-Revised Federal Supereme Court s No 2/2006 by ሕግ እና ፍትህ on Scribd