Search This Blog

Oct 24, 2020

የመሻሪያና የክልከላ ትዕዛዝ

              የመሻሪያና የክልከላ ትዕዛዝ
የመሻሪያ ትዕዛዝ (Certiorari) ማለት የበላይ የሆነ ፍርድ ቤት ለሥር ፍርድ ቤት ወይም አስተዳደር ፍርድ ብሎም ሌላ ውሳኔ ሰጭ አካል ውሳኔ የተሰጠበትን መዝገብ እንዲልክለት የሚያስገድድበትና በመቀጠልም ውሳኔው ህጋዊ ስርዓት ተከትሎ በህግ በተፈቀደ የስልጣን ወይም ክልል ውስጥ መሰጠቱ የሚመረመርበት፣ ከስልጣን በላይ ሆኖ በተገኘ ጊዜም የሚሻርበትና ዋጋ የሚያጣበት የመፍትሄ አይነት ነው፡፡a ከትርጉሙ መረዳት እንደምንችለው የመሻሪያ መፍትሄ በሁለት ደረጃዎች የተከፈለ ነው፡፡
የመጀመሪያው ደረጃ የውሳኔውን ሂደት የሚያሳየውን መዝገብ እንዲላክለት የበላይ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ትዕዛዝ ነው፡፡ ይህ ከተሟላ በኋላ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ይተላለፋል፡፡ የበላይ ፍርድ ቤት መዝቡንና ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ከስልጣን ውጭ ወይም በስልጣን አለአግባብ መገልገል መፈጸሙን ካረጋገጠ እንዲሻር ውሳኔ ያስተላልፋል፡፡ ውሳኔው ይሻራል ሲባል ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ የመሻሪያ ትዕዛዝ ከስልጣን በላይ (Ultra vires) ወይም ከዳኝት ስልጣን ክልል ውጭ (Jurisdication error) የተፈጸም ተግባር የሚሻርበትና ዋጋ የሚያጣበትን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ውጤቱ ጥያቄ የተነሳበትን ተግባር እስከመሻር ድረስ ብቻ ነው፡፡ የበላይ ፍርድ ቤት ከዚህ አልፎ በጉዳዩ ይዘት ወይም በፍሬ ነገሩ ላይ ውሳኔ አያስተላልፍም፡፡ በሌላ አነጋገር የበላይ ፍርድ ቤቱ በተሻረው ውሳኔ ፈንታ የራሱን ፍርድ አይሰጥም፡፡
የክልከላ ትዕዛዝን ያየን እንደሆነ አፈጻጸሙ ከመሻሪያ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ውጤቱ ግን ከስልጣን በላይ ወይም ከዳኝት ስልጣን ክልል ውጭ የሆነ ድርጊት ወይም ውሳኔ ለወደፊት እንዳይሰጥ፣ ተጀምሮ ከሆነም ባለበት እንዲቆም ያደርጋል፡፡b ስለሆነም በፍትሐብሔር ሕግ ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነት ላይ ከተቀመጠው የዕግድ ትዕዛዝ ጋር ይመሳሰላል፡፡ በመሻሪያ እና ክልከላ መካከል ያለው ልዩነት የጊዜ ልዩነት ነው፡፡ ይህም ማለት የመሻሪያ ትዕዛዝ የተፈጸመውን አስተዳደራዊ ተግባር ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ ስለሚያስቆጥረው የተፈጸሙ ተግባራት ወደ ቀድሞው ቦታቸው ይመለሳሉ፡፡ በአንጻሩ የክልከላ ትዕዛዝ አንድ ድርጊት ወደፊት እዳይፈጸም የተጀመረ ካለም እንዳይቀጥል በዚህም ነገሮች ባሉበት እንዲረጉ ያደርጋል፡፡
ሁለቱም የፍትሐብሔር መፍትሄዎች ባለመሆናቸው ራሱን በቻለ ዝርዝር የአጣሪ ዳኝነት የስነ-ስርዓት አካሄድ መሰረት ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡ መፍትሄዎቹ የሚሰጡበት የህግ መሰረት እና የሥነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ከአገር አገር የተለያዩ ቢሆንም ሁለቱም በአንድ አቤቱታ በአማራጭ ወይም በማዳበል ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ ታሪካዊ አመጣጣቸው ሲታይ በእንግሊዝ የበላይ ፍ/ቤቶች የስር ፍ/ቤቶችን እና የአስተዳደር ጉባዔዎችን ከመቆጣጠር ስልጣናቸው የመነጩ ናቸው፡፡ ኋላ ላይ ግን በአስተዳደር ውሳኔ ሰጭ አካላት ላይም ተፈጻሚ ተደርገዋል፡፡
የመፍትሄዎቹ መኖር የፖሊሲ መሰረቱ ማንኛውም ውሳኔ ሰጭ አካል በህግ አውጭው ከተሰጠው የሥልጣን ወይም የዳኝነት ስልጣን ክልል አልፎ የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ውሳኔ መስጠት ወይም ድርጊት መፈፀም የለበትም የሚለው የህግ የበላይነት ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ አንደኛው የህግ የበላይነት መርህ ህጋዊነት ነው፡፡ ህጋዊነት የሚረጋገጠው ማንኛው በህግ ስልጣን የተሰጠው አካል በህግና በህጉ መሰረት ብቻ ውሳኔ መስጠቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በህግ ከተፈቀደው የሥልጣን ገደብ በላይ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች የግለሰቦችን መብት መጣሳቸው አይቀርም፡፡ ስለሆነም ፍ/ቤቶች ጣልቃ በመግባት ህገ ወጥ የሆነውን ድርጊት መሻር ብሎም ሊፈፀም እርግጥ የሆነው ደግሞ አንዳይፈጸም የመከልከል ዳኝነታዊ ግዴታ አለባቸው፡፡
ክልከላን በተመለከተ አመልካቹ ማሳየት የሚጠበቅበት ውሳኔ ሰጭው አካል ከስልጣኑ በላይ አንድ ድርጊት መፈጸም መጀመሩን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቀድሞውኑ ከስልጣን በላይ በሆነ ውሳኔ ላይ ተመስርቶ አፈጻጸም እንደቀጠለ ማሳየትም በቂ ሊሆን ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ከስራ ማስወጣትን የተመለከቱ የሥራ ክርክሮችን ማየትና የዳኝነት መስጠት አይችልም፡፡ እንበልና ይህ የክልከላ መፍትሄ በአገራችን የአስተዳደር ህግ ውስጥ ቢኖር ቦርዱ በሰራተኛ የቀረበ ከስራ የማስወጣት የክስ አቤቱታ ተቀብሎ መጥሪያ ለተከሳሹ በላከበት ደረጃ ላይ በበላይ ፍ/ቤቱ የክልከላ ትዕዛዝ ሊሰጥበት ይችላል፡፡ ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተ ማከራከር በጀመረበት በማንኛውም ደረጃ ላይም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ቦርዱ ውሳኔ የሰጠ እንደሆነ በበላይ ፍ/ቤት ሊሰጥ የሚችለው መፍትሄ ክልከላ ሳይሆን የመሻሪያ ትዕዛዝ ነው፡፡ ውጤቱም የቦርዱን ውሳኔ ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ እንዲቆጠር ያደርገዋል፡፡


No comments:

Post a Comment

Popular Posts

DOCUMENTS

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd

Files

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ 2/ 2006 PDF-Revised Federal Supereme Court s No 2/2006 by ሕግ እና ፍትህ on Scribd