የአስተዳደር ጉባዔዎች የዳኝነት የስልጣን ክልል (Judicial Jurisdiction) ጠባብና በህግ ተለይተው በተጠቀመጡ ውሱን ጉዳዮች ላይ ብቻ የተገደበ ነው፡፡ በአንጻሩ መደበኛ ፍ/ቤቶች እርስ በርሳቸው የይዘት ቅርበትና ዝምድና የሌላቸውን የተለያዩ የህግ ክፍሎችን የሚመለከቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ስልጣን አላቸው፡፡ ጠባብ የሆነው የዳኝነት ስልጣን ልዩ እውቀትን በማጐልበት ረገድ የጐላ አሰተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ለምሳሌ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የዳኝነት ስልጣን በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በሚነሱ የወል የስራ ክርክሮች ላይ ብቻ ነው፡፡a የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እንዲሁ የግብር አሰባሰብና ጉምሩክን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ብቻ የሚያይ ሲሆን የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ከጡረታ መብትና ጥቅም ጋር በተያያዘ የዳኝነት ስልጣን አለው፡፡
ምንም እንኳን የጉባዔዎች የዳኝነት ስልጣን በጥቅሉ ሲቀመጥ ጠባብ ቢመስልም በስራቸው ከሚወድቁት ጉዳዮች ብዛትና ከሚነሱት ጭብጦች ዓይነት አንጻር ስልጣናቸው ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ምንም እንኳን የስልጣኑ ክልል የጡረታ መብትና ጥቅም የሚመለከቱ ጉዳዮች ቢሆንም ጉባዔው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ጡረተኛ የሚያቀርበውን ይግባኝ ስለሚሰማ በአይነት ሆነ በቁጥር በርካታ ጉዳዮችን ያስተናግዳል፡፡
ከዳኝነት ስልጣን በተጨማሪ በክርክሩ ሂደት የሚኖረው ስልጣን ከባህርያቱ አንጻር መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የአስተዳደር ጉባዔ ከፊል የዳኝነት አካል እንደ መሆኑ ከሞላ ጐደል መደበኛ ፍርድ ቤት የሚኖሩትን ስልጣንና ተግባራት ይጋራል፡፡ ስለሆነም በማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ተለይቶ በግልፅ ቢመለከትም ባይመለከትም እንደ ማንኛውም ፍ/ቤት ተከራካሪ ወገኖችና ምስክሮች እንዲቀርቡ ወይም ቃላቸውን እንዲሰጡ የማድረግ፣ የመሀላ ወይም የማረጋገጫ ቃል የመቀበል፣ ለክርክሩ በማስረጃነት አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ከሚመለከተው ሰው ወይም ድርጅት እንዲቀርቡ የማድረግ ብሎም በማናቸውም ድርጅት ውስጥ ገብቶ አስፈላጊ መረጃዎችን የመሰብሰብና ምስክሮችን የመስማት የመሳሰሉ ተግባራትን ለማከናወን ስልጣን አለው፡፡ በተጨማሪም በክርክሩ ወቅት የሚያስተላልፋቸው ትእዛዞችና ውሳኔዎች አስገዳጅ ተፈጻሚነት አላቸው፡፡
የእነዚህ ባህሪያት መኖር ከመደበኛ ፍ/ቤት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ሁለት ጭብጦች የጠራ መልስ ይሰጠናል፡፡ የመጀመሪያው በክርክር ሂደት ፍ/ቤት የመድፈር ውጤትን ይመለከታል፡፡ የአስተዳደር ጉባዔ በያዘው ጉዳይ ላይ በክርክር ወቅት የፍ/ቤት መድፈር ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ እንደ መደበኛ ፍርድ ቤት ወዲያውኑ ቅጣት ማስተላለፍ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ዳኝነታዊ የሆነው ባህርዩ አዎንታዊ መልስ ይሰጠናል፡፡ በወንጀል ህግ አንቀጽ 449 ላይ የተመለከተው ፍ/ቤትን የመድፈር ወንጀል ከሚያቋቁሙት ህጋዊ ክፍሎች መካከል በድንጋጌው ላይ ከተመለከቱት ድርጊቶች መኖር በተጨማሪ ድርጊቱ በፍ/ቤት፣ ምርመራ ወይም የዳኝነት ስራ በሚከናወንበት ወቅት መሆን አለበት፡፡ የአስተዳደር ጉባዔ በከፊልም ቢሆን ዳኝነታዊ ስልጣን ያለው የዳኝነት አካል እንደመሆኑ የጉባዔው ዳኛ ላይ ማፌዝ፣ መዛት፣ መሳደብ ወይም በማናቸውም መንገድ ስራውን ማወክ የፍ/ቤት የመድፈር ወንጀል ነው፡፡ ስለሆነም ድርጊቱ በተፈፀመ ጊዜ ዳኛው ወዲያውኑ በጥፋተኛው ላይ ቅጣት ሊወስንበት ይችላል፡፡
በሁለተኛነት ተያይዞ የሚነሳው ጭብጥ በጉባዔ ፊት ሀሰተኛ ቃል ወይም ምስክርነት መስጠት በወንጀል የማስቀጣቱ ሁኔታ ነው፡፡ በወንጀል ህግ አንቀጽ 425 እና 453 ላይ ተከራካሪ ወገን የሚሰጠው ሀሰተኛ ቃል እና ሀሰተኛ የምስክርነት ቃል፣ አስተያየት ወይም ትርጉም በመደበኛ ፍ/ቤት ፊት ብቻ ሳይሆን የዳኝነት ነክ ስልጣን ባለው አካል ፊት የተፈፀመ ከሆነ በወንጀል ያስቀጣል፡፡ ምንም እንኳን የወንጀል ህጉ በግልፅ ስለ አስተዳደር ጉባዔ ባያወራም ‘የዳኝነት ነክ ስልጣን ያለው አካል’ ከፊል የዳኝነት ስልጣን ያለውን የአስተዳደር ጉባዔን እንደሚጨምር ግልፅ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment