Search This Blog

Oct 24, 2020

የማስገደጃ ትዕዛዝ

የማስገደጃ ትዕዛዝ
ከመንግስት ባለስልጣናት ህገ ወጥ እርምጃዎች ባልተናነሰ በህግ የተጣለባቸውን ግዴታ ባለመወጣት በግለሰቦች መብትና ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ አንድን ተግባር የመፈጸም የህግ ግዴታ የተጣለበት አካል ግዴታውን በአግባቡ ሊወጣ ይገደዳል፡፡ የማስገደጃ መንገድ በሌለበት ግዴታን ከውዴታ ነጥሎ ማየት ይከብዳል፡፡
የማስገደጃ ትዕዛዝ (mandamus) ማለት አንድ በህግ ግዴታ የተጣለበት አካል ግዴታውን እንዲወጣ የሚታዘዝበትና የሚገደድበት የመፍትሄ አይነት ነው፡፡a ‘ግዴታ’ የሚለው የአማርኛ ቃል በተለይ በእንግሊዘኛው በሁለት መልኩ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው Duty ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፈቃደ ስልጣን (Discretion) ነው፡፡ የመጀመሪያው ከመፈፀም ውጭ አማራጭ የሌለውን ግዴታ ይወክላል፡፡ ለምሳሌ ህጋዊ ሁኔታዎች ከተሟሉ የባለቤትነት ስመ ሀብት ማዛወር ግዴታ የተጣለበት አካል የማዛወሩን ተግባር ከመፈጸም ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ፈቃደ ስልጣንን (Discretion) ያየን እንደሆነ ግን የአስተዳደር ተቋሙ ግዴታ በዝርዝር የተቀመጡ ወይም ያልተቀመጡ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ጉዳዩን መመርመርና በመጨረሻ ላይም ውሳኔ ላይ መድረስ ብቻ ነው፡፡
የንግድ ፍቃድ የሚሰጥ የአስተዳደር መስሪያ ቤት ማመልከቻውን ላቀረበ ሁሉ ፈቃድ የመስጠት ግዴታ የለበትም፡፡ ሆኖም ግን ማመልከቻው በተገቢው ሁኔታ በቀረበለት ጊዜ በህጉ ከተቀመጡት መስፈርቶች አንጻር መርምሮ ውሳኔ ላይ የመድረስ ግዴታ አለበት፡፡ ለአመልካቹ ፈቃድ የመስጠት ወይም ያለመስጠት ውሳኔ ካስተላለፈ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡ የማስገደጃ ትዕዛዝ የሚሰጠው ለግል አመልካቹ ሆኖ የግዴታው አለመፈጸም በመብቱና በጥቅሙ ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ሆኖም አንዳንዴ ግዴታው በቀጥታ ለአመልካቹ ብቻ ሳይሆን ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል መፈጸም ያለበት ህዝባዊ ግዴታ በሆነ ጊዜም ትዕዛዙ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህን አስመልክቶ በተለይ በህንድ አገር በተሰጠ አንድ ፍርድ ከተማዋን የማጽዳት ግዴታ ለጠቅላላው ህዝብ ቢሆንም ልዩ ጉዳት ያልደረሰበት ግሰለብ ክስ አቅርቦ የማስገደጃ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤቱ ለማግኘት ችሏል፡፡
የማስገደጃ ትዕዛዝ የመንግስት ባለስልጣናትና የአስተዳደር አካላት በህግ የተጣለባቸውን ግዴታ ባልተወጡ ጊዜ ለዜጋው በቅርብ ያለ መሳሪያ ነው፡፡ ትዕዛዙ እንዲሰጥለት የሚፈልግ ወገን በቅድመ ሁኔታነት ሁለት ነገሮችን ማሳየት አለበት፡፡ በመጀመሪያው አመልካቹ ግዴታው እንዲፈጸምለት የሚፈልግ መሆኑን ገልጾ በቃል ወይም በጽሑፍ ግዴታው ላለበት አካል ማቅረብ አለበት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ጥያቄው የቀረበለት አካል በግልጽ ወይም በዝምታ ግዴታውን ለመፈጸም ፍቃደኛ አለመሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ጥያቄ ቀርቦ የአስተዳደር ተቋሙ እምቢተኛ መሆኑ ሳይረጋገጥ በፊት በቀጥታ ወደ ፍ/ቤት መሄዱ ተገቢነት የለውም፡፡ ይሁን እንጂ የግዴታው መፈጸም በህግ በተቀመጠ ጊዜ ገደብ ውስጥ ከሆነና ጊዜው ማለፉ ከተረጋገጠ ለተቋሙ ጥያቄ ማቅረቡ ሆነ እንቢታን ማሳየቱ አስፈላጊ አይሆንም፡፡
ጥያቄ የሚቀርብለት ፍ/ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ትዕዛዙን ላይሰጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል የጊዜ ማለፍ ትዕዛዙን ዋጋ ያሳጣዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግዴታው አለመፈጸም ግዙፍ ጉዳት የማይደርስ ከሆነ፣ ግዴታው ቢፈጸም የባሰ ጉዳት በ3ኛ ወገኖች ላይ የሚያስከትል ከሆነ፣ የአመልካቹ ክፉ ልቦና ወዘተ… የማስገደጃ ትዕዛዝ ላለመስጠት በተለያየ አገራት እንደ ምክንያት ይወሰዳሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከግዴታው ስፋት አንፃር የማስገደጃ ትዕዛዝ ቢሰጥም ዝርዝር አፈፃጸሙን መከታተል ለፍ/ቤቱ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ተገቢ ክትትል ማድረግ በማይቻልበት ሁኔታ ትዕዛዙ በተላለፈበት አካል መከበሩን ለመወሰንና ካላከበረም በፍ/ቤት ንቀት ተገቢውን ቅጣት ለመቅጣት ተጨባጭ ችግር ይፈጥራል፡፡ የማስገደጃ ትዕዛዝ በህግ ዕውቅና ባገኘባቸው አገራት ክትትል ማድረግ በሚያስቸግርባቸው ሁኔታዎች ትዕዛዙን ውጤት አልባ ስለሚያደርገው ፍ/ቤቶች ዳኝት ከመስጠት ይቆጠባሉ፡፡
በተግባር ተመሳሳይ ችግር ከሚፈጠርባቸው ሁኔታዎች አንዱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች አፈፃፀም ነው፡፡ የእነዚህ መብቶች በፍርድ የመፈጸማቸው ሁኔታ በተለያዩ ወገኖች የመከራከሪያ ርዕሰ ቢሆንም በፍርድ ይዳኛሉ ቢባል እንኳን አፈፃፀማቸውን መከታተል ከአንድ ፍርድ ቤት አቅም ጊዜና እውቀት በላይ ነው፡፡ በህግ መንግስቱ አንቀጽ 41/4/ መሰረት መንግስት የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎቶች ለህዝብ ለማቅረብ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሀብት ይመድባል፡፡ ቀጣዩ ንዑስ አንቀጽ 5 አንዲሁ መንግስት አእምሮና አካል ጉዳተኞችን ያላሳዳጊ የቀሩ ህፃናትን ለመርዳት የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ፍርድ ቤት እነዚህ ግዴታዎች እንዲፈጸሙ የማስገደጃ ትዕዛዝ ቢሰጥ ግዴታው በትዕዛዙ መሰረት እየተፈጸመ መሆኑን በየጊዜው ለመከታተል ከቶ አይታሰብም፡፡
ይህ ቀርቶ መንግስት የተወሰነ አገልግሎት ለአንድ የህብረተሰብ ክፍል እንዲያቀርብ ለምሳሌ በአንድ ወረዳ ውስጥ የጤና ጣቢያ እንዲያቋቁም ቢገደድ ከቤቱ ግንባታ ጀምሮ እስከ ባለሙያ ቅጥርና በተግባር የአገልግሎት መስጠት ድረስ ቁጥጥርና ክትትል አድርጎ ትዕዛዙ ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም? ብሎም ለመደምደም የሚያስችል ብቃት የለውም፡፡ ስለሆነም ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች በፍርድ ሊዳኙ የሚችሉ ጉዳዮች መሆናቸውን በተመለከተ የሚደረጉ ክርክሮች በዋነኛነት ማጠንጠን ያለባቸው በእርግጥ ፍ/ቤት ውጤታማ መፍትሄ የመስጠት ብቃት አለውን በሚለው ጥያቄ ላይ መሆን አለበት፡፡
በትዕዛዙ መሰረት አንድ ግዴታ ለመፈጸም ገንዘብ አለመኖሩ ሌላ ተጨማሪ ችግር ነው፡፡ እንደ እንግሊዝ ባሉ ያደጉ አገራት ምናልባት ቀድሞውኑ የማይፈጸምና በቂ በጀት ባልተመደበበት ሁኔታ ግዴታን በህግ ስለማያስቀምጡ ግዴታውን ላለመወጣት የገንዘብ እጥረት በቂ ምክንያት አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ደሃ አገራት ግን የገንዘብ መኖርና አለመኖር የግዴታውን መፈፀምና አለመፈጸም በእጅጉ ይወስናል፡፡ ኢኮኖሚ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች አፈጻጸም በኢትዮጵያ ከዚህ አንጻርም መቃኘት ይኖርበታል፡፡


No comments:

Post a Comment

Popular Posts

DOCUMENTS

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd

Files

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ 2/ 2006 PDF-Revised Federal Supereme Court s No 2/2006 by ሕግ እና ፍትህ on Scribd