የመንግስት የህግ ተጠያቂነትና የመፍትሔ ዓይነቶች
ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ’ የሚለው አባባል አጠቃላዩን የመንግስት ተጠያቂነት (Accountablity) ከመግለጽ አንጻር አሁንም ድረስ የአንጻራዊ እውነት ነጸብራቅነቱ ባይካድም የመንግስትን የህግ ተጠያቂነት በአግባቡ አይወክልም። ቀደም ባለው ጊዜ የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታ በተመለከተ ታሪካዊ ጥናት ቢጠይቅም የፍትሐብሔር ህግ ከታወጀበት ከ1952 ዓ.ም. ወዲህ መንግስት በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት ስርዓት ተዘርግቷል። በተለይም አዲስ የወጣው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ የመንግስትን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ረገድ የተሟላ ሊባል የሚችል ስርዓት ዘርግቷል። ስርዓቱ የዜጎችን በደል በመካስና መብታቸውን በማስጠበቅ ረገድ ውጤታማነቱና የተቀባይነት ደረጃው እንዲሁም ከፍትሐዊነትና (ከፍርድ ቤቶች) ገለልተኛነት አንጻር ተግባራዊ አፈጻጸሙ እስከምን ድረስ ዜጎችን ያረካል የሚለው ጥያቄ ራሱን በቻለ የጥናት ርዕስ ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ነው።
የዚህ ምዕራፍ ዋና ትኩረት የመንግስት አስተዳደር በህጋዊነት ማዕቀፍ ሳይከናወን ሲቀር ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በመደበኛ ፍርድ ቤት ጠይቀው ሊያገኙ ስለሚችሉት መፍትሄ ወይም ዳኝነት (remedy) ይሆናል። ከፍርድ ቤት ውጪ ያሉ የመፍትሄ መንገዶች ማለትም በተለያዩ የአስተዳደር ቅሬታ ሰሚ አካላት በግል ወይም በቡድን ቅሬታ የሚስተናገድበት ስርዓት በዚህ ምዕራፍ ስር አልተካተተም።
መፍትሄ ከተጠያቂነት ይመነጫል።
ተጠያቂነት በተራው ተጠያቂ በሚያደርገው የህግ ክፍል ይወሰናል። የፍትሐብሔር ተጠያቂነት ሲኖር ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ዳኝነት ተጠያቂ በሚያደርገው የህግ ክፍል ላይ በዝርዝር ተለይቶ ተቀምጧል። ከፍትሐብሔር በተለየ የአስተዳደር ህግ ተጠያቂነትና ከዚህ የሚመነጭ መፍትሄ (Public Law Remedy) በአገራችን ህግ በግልጽ አይታወቅም። የአገራችን የአስተዳደር ህግ ገና ከፍትሐብሔር እቅፍ አልወጣም። ይህ የህግ ክፍል ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ በቆመባቸው አገራት በህገ ወጥ አስተዳደራዊ ተግባር ሳቢያ በዜጎች ላይ ለሚደርስ በደል ፍርድ ቤቶች በፍትሐብሔር እና በአስተዳደር ህግ የሚሰጡት መፍትሄ በተለያየ የህግ ማዕቀፍ ይመራል።
የፍትሐብሔር መፍትሔዎች
የፍትሐብሔር መፍትሔ መደበኛ ፍ/ቤቶች የፍትሐብሄር ህግጋትን ተፈፃሚ በማድረግ የሚሰጧቸውን ትዕዛዛትንና ውሳኔዎችን ይመለከታል። በፍትሐብሔር መብቱን ለማስከበር የሚሻ ተከራካሪ የሥነ-ስርዓት ህጉን በመከተል ማለትም የክስ ምክንያት ባለው ጉዳይ የክስ አቤቱታ በማቅረብ ተገቢውን ክፍያ ከፍሎ ዳኝነት መጠየቅ አለበት። በዚህ መልኩ በመንግስት ላይ የሚቀርብ ክስ በአንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት ላይ ከሚቀርበው ክስ አይለይም።
በፍትሐብሔር የሚሰጥ ዳኝነት አንዱ ጠቀሜታ በአስተዳደር ህግ የተቀመጡትን የሥነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ማለትም የትዕዛዝ አቤቱታ በማቅረብ ውሳኔ ሰጪው አስተዳደራዊ ተቋም ስለመሆኑ፣ ውሳኔውም መብትና ጥቅም የሚነካ ዳኝነታዊ እንጂ ተራ አስተዳደራዊ ውሳኔ አለመሆኑን፣ አስተዳደራዊ መፍትሄ ማሟጠጥ ወዘተ… በቅድሚያ ማስረዳት አያስፈልግም።
ከፍትሐብሔር መፍትሄዎች መካከል ከውል ወይም ከውል ውጪ በሚደርስ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡት የዕግድ ትዕዛዝ፣ የጉዳት ካሳ ፣ የንብረት ማስመለስa እንዲሁም በንብረት ህጉ የተመለከቱት የሁከት ማስወገድና የመፋለም ክሶች ዋነኞቹ ናቸው። የመግለጫ ትዕዛዝ (ውሳኔ) በፍትሐብሔር ውስጥ የሚካተት ቢሆንም በአገራችን እንዲህ ዓይነቱ ዳኝነት ራሱን ችሎ የቆመ የክስ ምክንያት አይደለም።
የዕግድ ትዕዛዝ
ዕግድ በፍትሐብሔር ክርክሮች ላይ ራሱን ችሎ እንደ ውሳኔ ወይም በክርክሩ መሀል እንደ ጊዜያዊ ትዕዛዝ ይሰጣል። ዕግድ በውጤቱ ተከሳሹ ወይም ተጠሪው አንድ ድርጊት ከመፈፀም እንዲታቀብ እንዲሁም የዕግዱ ትዕዛዝ አስገዳጅ ከሆነ አንድን ድርጊት በተወሰነ አይነት መንገድ እንዲፈጽም ያስገድደዋል። በኢትዮጵያ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት ሕግ ውስጥ የእግድ ትዕዛዝ የተፈፃሚነት ወሰኑ ተከሳሹ ጉዳት የሚያመጣ ነገር እንዳይሰራ በመስራት ላይ ቢገኝ እንዳይቀጥል ወይም እንደገና እንዳይጀመር ማገጃ እንጂ አንድ ተግባር እንዲፈጸም ማስገደጃ እንዳልሆነ ከፍ/ሕ/ቁ 2121(1) ድንጋጌ እንረዳለን።
ዕግድ ማገጃ እና ማስገደጃ ትዕዛዛትን አጠቃሎ ሲይዝ ህገ ወጥ አስተዳደራዊ ተግባራትን ብቻ ሳይሆን በቸልተኝነት ግዴታን ባለመወጣት የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎችን ለመቅረፍ የሚያስችል ውጤታማ መሳሪያ ነው።
ተፈፃሚነቱ ደረቅና ፍፁም ሳይሆን ተስማሚ ባልሆኑ ሁኔታዎች ሁሉ ዳኛው ትዕዛዙን ላለመስጠት ሰፊ ስልጣን አለው። በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2021/2/ እንደተመለከተው በሁለት ሁኔታዎች ትዕዛዙ ላይሰጥ ይችላል። ይኸውም ጥያቄ የተነሳበት ድርጊት በከሳሹ ላይ ጉዳት እንደሚያመጣ አሳማኝ ምክንያት ከሌለና እንዲሁም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ኪሳራውን በመክፈል ለመካስ ከተቻለ ፍርድ ቤት ዳኝነት ለመንፈግ ሰፊ ስልጣን አለው።
የዕግድ ትዕዛዝ ራሱን የቻለ ውሳኔ እንደመሆኑ ክርክሩ ታይቶ ፍ/ቤቱ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ጊዜያዊ የዕግድ ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 154 መሰረት ሊሰጥ ይችላል። ይህ በባህሪዩ ዘላቂ መፍትሄ ሳይሆን ውሳኔ እስከ ውሳኔ ቀን ሊደርስ የሚችልና የማይመለስ ጉዳት እንዳይደርስ በጊዜያዊነት የሚሰጥ ከለላ ነው። ትዕዛዙ የተላለፈለት ተከራካሪ ዕግዱን ባያከብር ድርጊቱ እንደ ፍርድ ቤት ንቀት ተቆጥሮ ቅጣት ይጣልበታል። በተመሳሳይ መልኩ በፍ/ሕ/ቁ 2121 መሰረት በቋሚነት የሚሰጥ የዕግድ ትዕዛዝ ተጨማሪ የአፈፃፀም ማመልከቻ ሳያስፈልግ ወዲያውኑ ተፈፃሚነት ሊኖረውና በተከሳሹ ሊከበር ይገባዋል። ይህ ባልሆነበት ጊዜ ፍ/ቤቱ በወንጀል ህጉ የተመለከተውን የፍርድ ቤት ንቀት ድንጋጌ በመጥቀስ ተገቢውን ቅጣት ይወስንበታል።
የዕግድ ትዕዛዝ የሚጠይቅ አመልካች ወይም ከሳሽ በድርጊቱ ምክንያት በንብረቱ ወይም በመብቱ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እንደሚደርስበትና በጉዳዩ ጥቅም ያለው መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል። ስለሆነም ድርጊቱ ከስልጣን በላይ ወይም አላግባብ በስልጣን መገልገል መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም። በሌሎች አገሮች ግን ይህን የጠበቀ የከሳሽነት ብቃት (standing) በማላላት የተለየ ልዩ ጉዳት በአመልካቹ ላይ ባይደርስም ከማንም ሰው ጋር በሚጋራው ህዝባዊ መብቱ ላይ ጠቅላላ ጉዳት ሲደርስበት የዕግድ አቤቱታ የማቅረብ መብት ይኖረዋል።
ካሳ እና ንብረት ማስመለስ
የመንግስት ተቋም በግል ወይም በመንግስታዊ ተግባሩ ላደረሰው ጉዳት ካሳ ሊከፍል ይገደዳል። ተቋሙ ስልጣኑን በመጠቀም የሚፈጽማቸው ተግባራት መንግስታዊ ሲሆኑ የተቀሩት ግን ግላዊ ናቸው። ባለቤትነቱ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተመዘገበ መኪና በንብረት ወይም በአካል ላይ ጉዳት ሲያደርስ ድርጊቱ ህግ በማስከበር ሂደት የተከሰተ አይደለም። ስለሆነም ግላዊ ነው። ኃላፊነቱ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 2126/2/ ይወሰናል። ድንጋጌው መንግስት ኃላፊነት የሚሸከመው ጉዳቱ የደረሰው ሰራተኛው ወይም ሹመኛው የመንግስት ስራ ሲሰራ የደረሰ እንደሆነ ነው። ለምሳሌ የባለስልጣኑ አሽከርካሪ ጉዳት ያደረሰው የግብር ገማች ኮሚቴ አባላትን ለስራ ይዞ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ከሆነ ባለስልጣኑ ተጎጂውን የመካስ ኃላፊነት ይኖርበታል። የመኪና አደጋ በሌላ የመንገስት ተቀጣሪ ባልሆነ ግለሰብም ሊደርስ ይችላል። ስለሆነም ከባለስልጣኑ አንጻር ተግባሩ ግላዊ ነው።
መንግስታዊ የሚባለው ተግባር ደግሞ አንድ የመንግስት ተቋም በህግ የተቋቋመለትን ዓላማ በማከናወን ሂደት ስልጣኑን በመገልገል የሚፈጽመው ድርጊት ነው። ለምሳሌ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኗል በሚል የያዘውን መኪና ተገቢውን ማጣራት ካደረገ በኋላ በስህተት መሆኑን ሲረዳ መኪናውን መልቀቅ ይኖርበታል። የማይለቅ ከሆነ ግን የመኪናው ባለቤት ንብረቱን የማስመለስ እና ለደረሰበት ጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት አለው። የባለስልጣኑ ተግባር ህገ ወጥ መሆኑ ከተረጋገጠ ጥያቄው በፍርድ ቤት ተቀባይነት ያገኛል። ህጋዊነትን በማጣራት ሂደት የአስተዳደር ህግ ጥያቄዎች ይነሳሉ። መኪናው ለባለቤቱ እንዲመለስ እንዲሁም ለተቋረጥበት ጥቅም እንዲካስ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ባለስልጣኑ ከስልጣኑ በላይ አሳልፎ ስለመስራቱ ወይም አለአግባብ በስልጣን ስለመገልገሉ በጭብጥነት ይያዛል። ይህም ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነት ህግ አንደኛው የስልጣን መቆጣጠሪያ መንገድ እንደሆነ ያሳየናል።
በሰ/መ/ቁ. 47935b ተጠሪ ወደ አገር ውስጥ ይዘውት የገቡትን ዶላር ለጉምሩክ ካስመዘገቡ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ መቶ ሰማንያ ቀናት አሳልፈው ከአገር ሲወጡ አመልካች ገንዘቡን ከልክሏቸዋል። አመልካች ለክልከላው ምክንያት ያደረገው የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ሲሆን በመመሪያው መመሰረት በጊዜያዊነት ለጉብኝት ወይም ለንግድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሰዎች ለጊዜው በእጃቸው የያዙትን የውጭ ምንዛሬ ለጉምሩክ አስመዝግበው ማስረጃ ከያዙ ከአንድ መቶ ሰማኒያ ሶስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ይዘውት የመጡትን የውጭ ምንዛሬ ይዘው ለመውጣት ፈቃድ አያስፈልጋቸውም። ተጠሪ ገንዘቡ እንዲመለስላቸው ክስ ሲያቀርቡ የክሱ ምክንያት ከውል ውጭ ኃላፊነት ህግ ውስጥ የሚመደብ የንብረት ማስመለስ ጥያቄ ነው። ጥያቄውን ለመመለስ ፍርድ ቤቱ የአመልካችን ድርጊት ህጋዊነት መወሰን ይኖርበታል። በሌላ አነጋገር አመልካች ገንዘቡን የመውረስ ስልጣን እንዳለውና እንደሌለው በጭብጥነት ተይዞ ሊጣራ ይገባዋል። የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ተመዝግቦ የገባ የውጭ የምንዛሪ የሚወጣበትን ጊዜ ገደብ ከመደንገግ ውጭ የጊዜውን ማለፍ ህጋዊ ውጤት አይናገርም። አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች የበታች ህጎች እንደመሆናቸው በግልጽ ካልተደነገገ በቀር የግለሰቦችን መብት እንደሚያሳጡ ተደርገው መተርጎም የለባቸውም። ስለሆነም የመመሪያው ዝምታ የተጠሪ መብት የማሳጣት ውጤት የለውም። በሌላ በኩል አመልካች የውጭ ምንዛሪውን እንዲወስዱ መፍቀዱ የጊዜ ገደቡን ትርጉም ያሳጣዋል።
የስር ፍርድ ቤቶችና የሰበር ችሎት የተከተሉት የህግ አተረጓጎም የመመሪውን ገደብ ከአመልካችን መብት ጋር ያስታርቃል። ይኸውም አመልካች ያስመዘገቡትን የውጭ ምንዛሪ በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ እንዲወስዱ ተፈቅዶላቸዋል። የውሳኔውን ይዘት በአስተዳደር ህግ መነጽር ስናየው አመልካች የውጭ ምንዛሪውን የማስቀረት ስልጣን ባይኖረውም በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ እንዲከፈል ማድረግ ይችላል።
የአስተዳደር ህግ መፍትሔዎች
የአስተዳደር ህግ መፍትሔ (Public Law Remedy) የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ዳኞች በአጣሪ ዳኝነት ስልጣናቸው ለአቤቱታ አቅራቢው መስጠት የሚችሉትን ዳኝነት ይመለከታል።
የመሻሪያና የክልከላ ትዕዛዝ
የመሻሪያ ትዕዛዝ (Certiorari) ማለት የበላይ የሆነ ፍርድ ቤት ለሥር ፍርድ ቤት ወይም አስተዳደር ፍርድ ብሎም ሌላ ውሳኔ ሰጭ አካል ውሳኔ የተሰጠበትን መዝገብ እንዲልክለት የሚያስገድድበትና በመቀጠልም ውሳኔው ህጋዊ ስርዓት ተከትሎ በህግ በተፈቀደ የስልጣን ወይም ክልል ውስጥ መሰጠቱ የሚመረመርበት፣ ከስልጣን በላይ ሆኖ በተገኘ ጊዜም የሚሻርበትና ዋጋ የሚያጣበት የመፍትሄ አይነት ነው።c ከትርጉሙ መረዳት እንደምንችለው የመሻሪያ መፍትሄ በሁለት ደረጃዎች የተከፈለ ነው።
የመጀመሪያው ደረጃ የውሳኔውን ሂደት የሚያሳየውን መዝገብ እንዲላክለት የበላይ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ትዕዛዝ ነው። ይህ ከተሟላ በኋላ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ይተላለፋል። የበላይ ፍርድ ቤት መዝቡንና ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ከስልጣን ውጭ ወይም በስልጣን አለአግባብ መገልገል መፈጸሙን ካረጋገጠ እንዲሻር ውሳኔ ያስተላልፋል። ውሳኔው ይሻራል ሲባል ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ ይቆጠራል ማለት ነው። በአጭር አገላለጽ የመሻሪያ ትዕዛዝ ከስልጣን በላይ (Ultra vires) ወይም ከዳኝት ስልጣን ክልል ውጭ (Jurisdication error) የተፈጸም ተግባር የሚሻርበትና ዋጋ የሚያጣበትን ሁኔታ ያመለክታል። ውጤቱ ጥያቄ የተነሳበትን ተግባር እስከመሻር ድረስ ብቻ ነው። የበላይ ፍርድ ቤት ከዚህ አልፎ በጉዳዩ ይዘት ወይም በፍሬ ነገሩ ላይ ውሳኔ አያስተላልፍም። በሌላ አነጋገር የበላይ ፍርድ ቤቱ በተሻረው ውሳኔ ፈንታ የራሱን ፍርድ አይሰጥም።
የክልከላ ትዕዛዝን ያየን እንደሆነ አፈጻጸሙ ከመሻሪያ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ውጤቱ ግን ከስልጣን በላይ ወይም ከዳኝት ስልጣን ክልል ውጭ የሆነ ድርጊት ወይም ውሳኔ ለወደፊት እንዳይሰጥ፣ ተጀምሮ ከሆነም ባለበት እንዲቆም ያደርጋል።d ስለሆነም በፍትሐብሔር ሕግ ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነት ላይ ከተቀመጠው የዕግድ ትዕዛዝ ጋር ይመሳሰላል። በመሻሪያ እና ክልከላ መካከል ያለው ልዩነት የጊዜ ልዩነት ነው። ይህም ማለት የመሻሪያ ትዕዛዝ የተፈጸመውን አስተዳደራዊ ተግባር ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ ስለሚያስቆጥረው የተፈጸሙ ተግባራት ወደ ቀድሞው ቦታቸው ይመለሳሉ። በአንጻሩ የክልከላ ትዕዛዝ አንድ ድርጊት ወደፊት እዳይፈጸም የተጀመረ ካለም እንዳይቀጥል በዚህም ነገሮች ባሉበት እንዲረጉ ያደርጋል።
ሁለቱም የፍትሐብሔር መፍትሄዎች ባለመሆናቸው ራሱን በቻለ ዝርዝር የአጣሪ ዳኝነት የስነ-ስርዓት አካሄድ መሰረት ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል። መፍትሄዎቹ የሚሰጡበት የህግ መሰረት እና የሥነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ከአገር አገር የተለያዩ ቢሆንም ሁለቱም በአንድ አቤቱታ በአማራጭ ወይም በማዳበል ሊጠየቁ ይችላሉ። ታሪካዊ አመጣጣቸው ሲታይ በእንግሊዝ የበላይ ፍ/ቤቶች የስር ፍ/ቤቶችን እና የአስተዳደር ጉባዔዎችን ከመቆጣጠር ስልጣናቸው የመነጩ ናቸው። ኋላ ላይ ግን በአስተዳደር ውሳኔ ሰጭ አካላት ላይም ተፈጻሚ ተደርገዋል።
የመፍትሄዎቹ መኖር የፖሊሲ መሰረቱ ማንኛውም ውሳኔ ሰጭ አካል በህግ አውጭው ከተሰጠው የሥልጣን ወይም የዳኝነት ስልጣን ክልል አልፎ የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ውሳኔ መስጠት ወይም ድርጊት መፈፀም የለበትም የሚለው የህግ የበላይነት ጽንሰ ሃሳብ ነው። አንደኛው የህግ የበላይነት መርህ ህጋዊነት ነው። ህጋዊነት የሚረጋገጠው ማንኛው በህግ ስልጣን የተሰጠው አካል በህግና በህጉ መሰረት ብቻ ውሳኔ መስጠቱ ሲረጋገጥ ነው። በህግ ከተፈቀደው የሥልጣን ገደብ በላይ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች የግለሰቦችን መብት መጣሳቸው አይቀርም። ስለሆነም ፍ/ቤቶች ጣልቃ በመግባት ህገ ወጥ የሆነውን ድርጊት መሻር ብሎም ሊፈፀም እርግጥ የሆነው አንዳይፈጸም የመከልከል ዳኝነታዊ ግዴታ አለባቸው።
ክልከላን በተመለከተ አመልካቹ ማሳየት የሚጠበቅበት ውሳኔ ሰጭው አካል ከስልጣኑ በላይ አንድ ድርጊት መፈጸም መጀመሩን ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቀድሞውኑ ከስልጣን በላይ በሆነ ውሳኔ ላይ ተመስርቶ አፈጻጸም እንደቀጠለ ማሳየትም በቂ ሊሆን ይቻላል። ለምሳሌ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ከስራ ማስወጣትን የተመለከቱ የሥራ ክርክሮችን ማየትና የዳኝነት መስጠት አይችልም። እንበልና ይህ የክልከላ መፍትሄ በአገራችን የአስተዳደር ህግ ውስጥ ቢኖር ቦርዱ በሰራተኛ የቀረበ ከስራ የማስወጣት የክስ አቤቱታ ተቀብሎ መጥሪያ ለተከሳሹ በላከበት ደረጃ ላይ በበላይ ፍ/ቤቱ የክልከላ ትዕዛዝ ሊሰጥበት ይችላል። ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተ ማከራከር በጀመረበት በማንኛውም ደረጃ ላይም ሊሰጥ ይችላል። ይሁን እንጂ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ቦርዱ ውሳኔ የሰጠ እንደሆነ በበላይ ፍ/ቤት ሊሰጥ የሚችለው መፍትሄ ክልከላ ሳይሆን የመሻሪያ ትዕዛዝ ነው። ውጤቱም የቦርዱን ውሳኔ ዋጋ አልባና እንዳልተሰጠ እንዲቆጠር ያደርገዋል።
የማስገደጃ ትዕዛዝ
ከመንግስት ባለስልጣናት ህገ ወጥ እርምጃዎች ባልተናነሰ በህግ የተጣለባቸውን ግዴታ ባለመወጣት በግለሰቦች መብትና ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ። አንድን ተግባር የመፈጸም የህግ ግዴታ የተጣለበት አካል ግዴታውን በአግባቡ ሊወጣ ይገደዳል። የማስገደጃ መንገድ በሌለበት ግዴታን ከውዴታ ነጥሎ ማየት ይከብዳል።
የማስገደጃ ትዕዛዝ (mandamus) ማለት አንድ በህግ ግዴታ የተጣለበት አካል ግዴታውን እንዲወጣ የሚታዘዝበትና የሚገደድበት የመፍትሄ አይነት ነው።e ‘ግዴታ’ የሚለው የአማርኛ ቃል በተለይ በእንግሊዘኛው በሁለት መልኩ ሊገለጽ ይችላል። የመጀመሪያው Duty ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፈቃደ ስልጣን (Discretion) ነው። የመጀመሪያው ከመፈፀም ውጭ አማራጭ የሌለውን ግዴታ ይወክላል። ለምሳሌ ህጋዊ ሁኔታዎች ከተሟሉ የባለቤትነት ስመ ሀብት ማዛወር ግዴታ የተጣለበት አካል የማዛወሩን ተግባር ከመፈጸም ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም። ፈቃደ ስልጣንን (Discretion) ያየን እንደሆነ ግን የአስተዳደር ተቋሙ ግዴታ በዝርዝር የተቀመጡ ወይም ያልተቀመጡ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ጉዳዩን መመርመርና በመጨረሻ ላይም ውሳኔ ላይ መድረስ ብቻ ነው።
የንግድ ፍቃድ የሚሰጥ የአስተዳደር መስሪያ ቤት ማመልከቻውን ላቀረበ ሁሉ ፈቃድ የመስጠት ግዴታ የለበትም። ሆኖም ግን ማመልከቻው በተገቢው ሁኔታ በቀረበለት ጊዜ በህጉ ከተቀመጡት መስፈርቶች አንጻር መርምሮ ውሳኔ ላይ የመድረስ ግዴታ አለበት። ለአመልካቹ ፈቃድ የመስጠት ወይም ያለመስጠት ውሳኔ ካስተላለፈ ግዴታውን ተወጥቷል። የማስገደጃ ትዕዛዝ የሚሰጠው ለግል አመልካቹ ሆኖ የግዴታው አለመፈጸም በመብቱና በጥቅሙ ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ማሳየት ይጠበቅበታል። ሆኖም አንዳንዴ ግዴታው በቀጥታ ለአመልካቹ ብቻ ሳይሆን ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል መፈጸም ያለበት ህዝባዊ ግዴታ በሆነ ጊዜም ትዕዛዙ ሊሰጥ ይችላል። ይህን አስመልክቶ በተለይ በህንድ አገር በተሰጠ አንድ ፍርድ ከተማዋን የማጽዳት ግዴታ ለጠቅላላው ህዝብ ቢሆንም ልዩ ጉዳት ያልደረሰበት ግሰለብ ክስ አቅርቦ የማስገደጃ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤቱ ለማግኘት ችሏል።
የማስገደጃ ትዕዛዝ የመንግስት ባለስልጣናትና የአስተዳደር አካላት በህግ የተጣለባቸውን ግዴታ ባልተወጡ ጊዜ ለዜጋው በቅርብ ያለ መሳሪያ ነው። ትዕዛዙ እንዲሰጥለት የሚፈልግ ወገን በቅድመ ሁኔታነት ሁለት ነገሮችን ማሳየት አለበት። በመጀመሪያው አመልካቹ ግዴታው እንዲፈጸምለት የሚፈልግ መሆኑን ገልጾ በቃል ወይም በጽሑፍ ግዴታው ላለበት አካል ማቅረብ አለበት። በሁለተኛ ደረጃ ጥያቄው የቀረበለት አካል በግልጽ ወይም በዝምታ ግዴታውን ለመፈጸም ፍቃደኛ አለመሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል። ጥያቄ ቀርቦ የአስተዳደር ተቋሙ እምቢተኛ መሆኑ ሳይረጋገጥ በፊት በቀጥታ ወደ ፍ/ቤት መሄዱ ተገቢነት የለውም። ይሁን እንጂ የግዴታው መፈጸም በህግ በተቀመጠ ጊዜ ገደብ ውስጥ ከሆነና ጊዜው ማለፉ ከተረጋገጠ ለተቋሙ ጥያቄ ማቅረቡ ሆነ እንቢታን ማሳየቱ አስፈላጊ አይሆንም።
ጥያቄ የሚቀርብለት ፍ/ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ትዕዛዙን ላይሰጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የጊዜ ማለፍ ትዕዛዙን ዋጋ ያሳጣዋል። ከዚህ በተጨማሪ በግዴታው አለመፈጸም ግዙፍ ጉዳት የማይደርስ ከሆነ፣ ግዴታው ቢፈጸም የባሰ ጉዳት በ3ኛ ወገኖች ላይ የሚያስከትል ከሆነ፣ የአመልካቹ ክፉ ልቦና ወዘተ… የማስገደጃ ትዕዛዝ ላለመስጠት በተለያየ አገራት እንደ ምክንያት ይወሰዳሉ። አንዳንድ ጊዜ ከግዴታው ስፋት አንፃር የማስገደጃ ትዕዛዝ ቢሰጥም ዝርዝር አፈፃጸሙን መከታተል ለፍ/ቤቱ አስቸጋሪ ይሆናል። ተገቢ ክትትል ማድረግ በማይቻልበት ሁኔታ ትዕዛዙ በተላለፈበት አካል መከበሩን ለመወሰንና ካላከበረም በፍ/ቤት ንቀት ተገቢውን ቅጣት ለመቅጣት ተጨባጭ ችግር ይፈጥራል። የማስገደጃ ትዕዛዝ በህግ ዕውቅና ባገኘባቸው አገራት ክትትል ማድረግ በሚያስቸግርባቸው ሁኔታዎች ትዕዛዙን ውጤት አልባ ስለሚያደርገው ፍ/ቤቶች ዳኝት ከመስጠት ይቆጠባሉ።
በተግባር ተመሳሳይ ችግር ከሚፈጠርባቸው ሁኔታዎች አንዱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች አፈፃፀም ነው። የእነዚህ መብቶች በፍርድ የመፈጸማቸው ሁኔታ በተለያዩ ወገኖች የመከራከሪያ ርዕሰ ቢሆንም በፍርድ ይዳኛሉ ቢባል እንኳን አፈፃፀማቸውን መከታተል ከአንድ ፍርድ ቤት አቅም ጊዜና እውቀት በላይ ነው። በህግ መንግስቱ አንቀጽ 41/4/ መሰረት መንግስት የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎቶች ለህዝብ ለማቅረብ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሀብት ይመድባል። ቀጣዩ ንዑስ አንቀጽ 5 አንዲሁ መንግስት አእምሮና አካል ጉዳተኞችን ያላሳዳጊ የቀሩ ህፃናትን ለመርዳት የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ፍርድ ቤት እነዚህ ግዴታዎች እንዲፈጸሙ የማስገደጃ ትዕዛዝ ቢሰጥ ግዴታው በትዕዛዙ መሰረት እየተፈጸመ መሆኑን በየጊዜው ለመከታተል ከቶ አይታሰብም።
ይህ ቀርቶ መንግስት የተወሰነ አገልግሎት ለአንድ የህብረተሰብ ክፍል እንዲያቀርብ ለምሳሌ በአንድ ወረዳ ውስጥ የጤና ጣቢያ እንዲያቋቁም ቢገደድ ከቤቱ ግንባታ ጀምሮ እስከ ባለሙያ ቅጥርና በተግባር የአገልግሎት መስጠት ድረስ ቁጥጥርና ክትትል አድርጎ ትዕዛዙ ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም? ብሎም ለመደምደም የሚያስችል ብቃት የለውም። ስለሆነም ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች በፍርድ ሊዳኙ የሚችሉ ጉዳዮች መሆናቸውን በተመለከተ የሚደረጉ ክርክሮች በዋነኛነት ማጠንጠን ያለባቸው በእርግጥ ፍ/ቤት ውጤታማ መፍትሄ የመስጠት ብቃት አለውን በሚለው ጥያቄ ላይ መሆን አለበት።
በትዕዛዙ መሰረት አንድ ግዴታ ለመፈጸም ገንዘብ አለመኖሩ ሌላ ተጨማሪ ችግር ነው። እንደ እንግሊዝ ባሉ ያደጉ አገራት ምናልባት ቀድሞውኑ የማይፈጸምና በቂ በጀት ባልተመደበበት ሁኔታ ግዴታን በህግ ስለማያስቀምጡ ግዴታውን ላለመወጣት የገንዘብ እጥረት በቂ ምክንያት አይሆንም። ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ደሃ አገራት ግን የገንዘብ መኖርና አለመኖር የግዴታውን መፈፀምና አለመፈጸም በእጅጉ ይወስናል። ኢኮኖሚ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች አፈጻጸም በኢትዮጵያ ከዚህ አንጻርም መቃኘት ይኖርበታል።
የመግለጫ (ማስረገጫ) ትዕዛዝ
የመግለጫ ትዕዛዝ (declaration, or declaratory judgment) በሁለት ወገኖች መካከል ያለውን የህግ አቋም በተመለከተ ፍ/ቤቱ መግለጫ የሚሰጥበት የትዕዛዝ ወይም የውሳኔ ዓይነት ነው።f በይዘቱ ከህግ ትርጓሜ የሚመነጭ ግዴታ ወይም መብት ከማስረገጥ ወይም ህጋዊነትና ህገወጥነት ሁኔታ ወይም አቋም ከመደንገግ ወይም ከማስረገጥ ባለፈ አስገዳጅነት የለውም። ስለሆነም ትዕዛዙን አለማክበር በፍ/ቤት ንቀት ቅጣት አያስከትልም።
ከስልጣን በላይ ወይም ህገ ወጥ በሆነ ድርጊት ምክንያት አንድ ሰው ለወደፊት በንብረቱና በነፃነቱ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ለሚችል ውሳኔ ሊዳረግ ይችላል። ውሳኔው እንዳይሰጥ ከተፈለገ አንደኛው አማራጭ በክልከላ ወይም በዕግድ ትዕዛዝ ማስቆም ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱም የመፍትሄ አይነቶች የራሳቸው የሆነ ልዩ ቅድመ ሁኔታና የሥነ-ስርዓት ድንጋጌዎች አሏቸው። ቀላሉ መንገድ የመብቱን መኖርና አለመኖር፣ የድርጊቱን ከስልጣን በላይ መሆን አለመሆን ወይም ሌላ ህጋዊ አቋም በፍ/ቤቱ እንዲፀና ወይም መግለጫ እንዲሰጥበት ዳኝነት መጠየቅ ነው።
በዚህ መልኩ ጥያቄ ማቅረብ ተመራጭ የሚያደርገው አመልካቹ ሌሎች የአስተዳደር ህግ መፍትሄዎችን ለማግኘት ማሟላት ያለበት ዝርዝር ቅድመ ሁኔታ እንዲያሳይ አይጠበቅበትም። ፍ/ቤትም አብዛኛውን ጊዜ ትዕዛዙን ለመስጠት አያመነታም። በተጨማሪም በመግለጫ የሚረጋገጠው የህግ ሁኔታ ለቀጣይ መፍትሄ መሰረት ይጥላል። ሌላው ጠቀሜታው ደግሞ በአመልካቹና ጥያቄ በቀረበበት አካል መካከል የከረረ ሙግት ስለማይኖር ሰላማዊ የችግር መፍቻ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል።
የመግለጫ ትዕዛዝ እስከ ቅርቡ 20ኛው ክፍ ዘመን ድረስ የአስተዳደር ተቋማትን በፍ/ቤት የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ሆኖ ብቅ አላለም።i በአጣሪ ዳኝነት የመፍትሄ ማዕቀፍ ውስጥ ከተጠቃለለ ወዲህ ግን ከሌሎች የመፍትሄ አይነቶች እጅግ በጣም በፈጠነ መልኩ ተቀባይት አግኝቷል።
መግለጫ ራሱን እንደ ቻለ ውሳኔ በአገራችን አልተለመደም። በመደበኛው የፍትሐብሔር ጉዳይ ተቀራራቢ ይዘት ኖሮት ተፈጻሚነት ቢያገኝም በአስተዳደራዊ ክርክር ውስጥ ግን ጥያቄው የተነሳበት ሆኖ ትዕዛዙ የተሰጠበት አጋጣሚ የለም።
የወራሽነት ምስክር ወረቀት፣ የመጥፋት ውሳኔ መግለጫ እና የአባትነት ውሳኔ ፍርድ ቤት የመግለጫው ውሳኔ ከሚሰጥባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ግን የአስተዳደር ክርክር አይደለኡም።
በአስተዳደራዊ ክርክሮች በመግለጫ ብቻ ዳኝነት የሚሰጥባቸው የህግ ሁኔታዎች የሉም። መብት ለማረጋገጥ የሚቀርብ ክስ ከመነሻው የክስ ምክንያት ስለማይኖረው ውድቅ ይደረጋል። ለምሳሌ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 1156/2012 አንቀጽ 9 አንድ ሰራተኛ የውሉ ጊዜ በአንቀጽ 10 መሰረት ላልተወሰነ ጊዜ እንደተደረገ ቢቆጠርም በመብቱና በጥቅሙ ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ‘የሥራ ውሌ ላልተወሰነ ጊዜ እደተደረገ ይቆጠርልኝ’ የሚል ጥያቄ ሊያቀርብ ሆነ ውሳኔ ሊያገኝ አይችልም። ምክንያቱም የተጠየቀው ዳኝነት የክስ ምክንያት የለውም። የመግለጫ ትዕዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ሰራተኛው በጥቅምና በመብቱ ላይ ጉዳት እስሚደርስ ድረስ ሳይጠብቅ ህጋዊ አቋሙ ማለትም የሥራ ውሉ ላልተወሰነ ጊዜ እንደተደረገ እንዲቆጠርለት ማረጋገጫ ማግኘት ይችል ነበር። ውሳኔው የፍ/ባለመብት ባያደርገውም ቀጣይ የመብት ጥሰቶችን በቀላሉ ለመቃወም ያስችለዋል።
ትዕዛዙ በውጤቱ አስገዳጅነት የለውም። ቢሆንም የራሱ ጠቀሜታዎች አሉት። እንደ አንድ የዳኝነት ዓይነት ተቀባይነት ባገኘባቸው አገራት ፍርድ ቤት መብት፣ ግዴታ ወይም ህጋዊነት በማረጋገጥ የሚሰጠው ትዕዛዝ በውዴታ ይከበራል። አስተዳደራዊ በደልን ለመቅረፍ ከሙግት ይልቅ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ እንዲሉ በግለሰቡ መብትና ጥቅም ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የህግ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ማስረገጥ ከአስገዳጅ ፍርድ የበለጠ የጎላ ፋይዳ አለው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የመግለጫ ትዕዛዝ በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ የማይሰጥ ቢሆንም ባህርያቱን በሚከተለው መላምታዊ ምሳሌ ማየት እንችላለን። በባንክ ስራ አዋጅ ቁ. 592/2000 መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ መረጃዎች ከባንኮች እንዲቀርቡለት የማድረግ ስልጣን አለው። ሆኖም የባንክ ደንበኞችን ስም፣ የትዳር ሁኔታ ሆነ ሌላ ግላዊ መረጃ መጠየቅ አልተፈቀደለትም። እንበልና የብሔራዊ ባንክ ህግ ከፈቀደለት ስልጣን ውጪ እያንዳንዱ ባንክ የተበዳሪዎቹን ግላዊ ሁኔታ ከብድር መዝገብ እየለቀመ ወይም ተበዳሪዎችን በአካል እየጠየቀ በአምስት ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲልክ፣ የማይልክ ከሆነ ግን ፈቃዱ እንደሚሰረዝ በማሳሰብ ለባንኮች ጥያቄ አቀረበ። ይህንን በመቃወም ባንኮች ቅሬታ በማሰማታቸው ከዚያም አልፎ የብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ህገ ወጥ ተብሎ የመግለጫ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ለፍርድ ቤት አመልክተው ቢሳካላቸው ትዕዛዙ በራሱ አስገዳጅ ውጤት አያስከትልም። ባንኮቹ በታዘዙት መሰረት ሪፖርት ባይልኩ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እንዳይሰርዝ አያግደውም። ሆኖም የሪፖርት ጥያቄው ህጋዊነት ከወዲሁ ስለሚታወቅ የመሰረዝ እርምጃውን በፍርድ ለማሻር ቀላል ያደርገዋል። ምናልባትም ባንኩ የህዝብ ጥቅም ለማስከበር ከቆመ ከሚደርስበት ህዝባዊ ወቀሳ ለመዳን ፈቃድ ከመሰረዝ የሚታቀብበት አጋጣሚ ይፈጠራል።
ኩዋራንቶ
ኩዋራንቶ (quo warranto) ‘በየትኛው ስልጣን?’ እንደ ማለት ነው።j የኩዋራንቶ አቤቱታ የስልጣን ህጋዊነት የሚጠየቅበትና ከህግ ውጭ በስልጣን ተቀምጦ ያለ ግለሰብ የሚነሳበትና የሚወገድበት መንገድ ነው። የመንግስት ሹመኞችና ሌሎች ባለስልጣናት በአንድ የአስተዳደር ተቋም ውስጥ በኃላፊነት ቦታ የሚቀመጡበት መስፈርትና ስነ-ስርዓት ከሿሚው አካል ማንነት ጭምር በግልጽ በህግ ተደንግጎ ይቀመጣል። ይህ በሆነ ጊዜ ስልጣን አለኝ ብሎ በአንድ መስሪያ ቤት በስልጣን ወንበር ላይ የተቀመጠ ግለሰብ የድርጊቱ ብቃትና ህጋዊነት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ የሹመቱን ብቃትና ህጋዊነት በማረጋገጥ ነው። ለምሳሌ ያህል በፌዴራል ፍርድ ቤት የሚያስችል ማንኛውም ዳኛ ሹመቱ ዕውቅና የሚያገኘው በተወካዮች ም/ቤት ሲጸድቅ ብቻ ነው። ከዚህ በተጻራሪ ከጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የሹመት ደብዳቤ ቢሰጠውና እንደ ዳኛ ተቀምጦ ፍርድ ቢሰጥ ሹመቱ ህጋዊ ብቃት ይጎድለዋል። የኩዋራንቶ አቤቱታ የቀረበበት ሰው ከስልጣኑ እንዲወገድ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ከማስተላለፉ በፊት የስልጣኑን ብቃትና ህጋዊነት እንዲያሳይ እድል ይሰጠዋል። ተጠሪው ይህን ሳያረጋግጥ ከቀረ ከተቀመጠበት ስልጣን ቦታ እንዲወገድ ይደረጋል።
ፍርድ ቤቱ የኩዋራንቶ ትዕዛዝ ሲሰጥ በሁለት መንገድ አስተዳደሩን ይቆጣጠረዋል። በመጀመሪያ ሹመት የሰጠውን ወይም ያጸደቀውን አካል ድርጊት ህጋዊነት ይመረምራል። በሁለተኛነት ተገቢው ችሎታ፣ ብቃትና ልምድ ሳይኖራቸው በህዝብ ላይ በሰልጣን ‘ቂብ ያሉ ሀሳዊ ባለስልጣናትን’ ጠርጎ በማውጣት አስተዳደር ከእነዚህ ሰዎች የፀዳና የጠራ እንዲሆን ያደርጋል። አቤቱታው በመርህ ደረጃ መቅረብ ያለበት አላግባብ ስልጣን በያዘው ሰው ድርጊት ጉዳት ደርሶብኛል በሚለው ግለሰብ ቢሆንም ጉዳቱ አጠቃላዩን የህዝብ ጥቅም የሚመለከት ከሆነ ማንኛውም ሰው አቤቱታውን የማቅረብ መብት አለው።k
በአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጁ የተቀመጡ መፍትሄዎች
ከስነ ስርዓት ብሎም ከይዘት አንጻር ህጋዊነትን የጣሰ ውሳኔ ወይም መመሪያ በሰዎች መብት እና ጥቅም ላይ ጉዳት ሲያስከትል የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጁ ለተጎጂው ሁለት ዓይነት መፍትሄዎች ያጎናጽፈዋል። የመጀመሪያውና ከአዋጁ በቀጥታ የሚመነጨው አስተዳደራዊ መፍትሄ ሲሆን ከዚሁ በተደራቢነት ደግሞ የፍትሀብሄር መፍትሄ የማግኘት መብቱን በአንቀጽ 59 ላይ ጠብቆለታል። እዚህ ላይ በአንድ የክስ ምክንያት መፍትሄዎችን መነጣጠሉ ለተጎጂው እፎይታ ወይስ ተጨማሪ ጫና? ከመሆኑ አንጻር ተገቢ ጥያቄ ማንሳት ያስፈጋል።
በርካታ የክለሳ ስርዓት መሰናክሎችን አልፎ የአስተዳደር ውሳኔ እንዲሻር አቤቱታ አቅርቦ የተሳካለት ባለጉዳይ በህገ-ወጥ ውሳኔው ሳቢያ በንብረት መብቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመካስ እንደገና ሀ ብሎ የፍትሐብሔር ክርክር መጀመር ይኖርበታል። እንደሌሎች አገራት ሁሉ ከአንድ የክስ ምክንያት የሚመነጩ የአስተዳደር ህግ እና የፍትሐብሒር ጥያቄዎች ተዳብለው አንድ ላይ የሚቀርቡበትን ስርዓት እንደመዘርጋት አዋጁ የፍትሐብሔር ለብቻው ተነጥሎ እንዲቀርብ የተከተለው አቅጣጭ ለመፍትሔ ፈላጊዎች አድካሚ ብቻ ሳይሆን ተስፋ አስቆራጭ ነው።
የአዋጁ መፍትሔዎች ቁንጽልነት
በአንቀጽ 50 /2/ መሰረት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክለሳ አቤቱታ የቀረበበትን የአስተዳደር መመሪያ ወይም ዉሳኔ ሊያፀና ወይም በሙሉ ወይም በከፊል ሊሽር ይችላል። የመሻሩ ውጤት የክለሳ አቤቱታ የቀረበበትን መመሪያ ወይም ውሳኔ ሕጋዊ ኃይል በሙሉ ወይም በከፊል ያስቀራል። የአስተዳደር በደል እና የህጋዊነት ጥሰት የሚገለጽባቸው መንገዶች በርካታ ቢሆኑም የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጁ በ ’ማድረግ’ (commission) ተግባራት ላይ ብቻ ተገድቧል። ቀጥተኛ ውጤት ከሚከተላቸው ‘አስተዳደራዊ እርምጃዎች’ ውጭ በአስተዳደሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመብቱ ላይ ጉዳይ የደረሰበት ሰው ከአዋጁ ጠብ የሚልለት ፍሬ የለም።
ለምሳሌ አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረና በህግ የሌላ አገር ያገኘ ሰው የኢትዮጵያ ዜግነት መልሶ ለማግኘት ማመልከቻ ሲያቀርብ በህግ ከተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ተጨማሪ በህግ ያልተጻፈ ሁኔታ በመጥቅስ በደፈናው ሁኔታዎቹ አልተሟሉም በሚል ምክንያት ማመልከቻው ተቀባይነት አጣ። የአስተዳደር ተቋሙ በህግ የሌለ ቅድመ ሁኔታ ለውሳኔው መሰረት የማድረግ ስልጣን የለውም። ስለሆነም የስልጣኑን ገደብ አልፏል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱን ከስልጣን በላይ የሆነ የአስተዳደር ውሳኔ በማሻር ውሳኔ ማስተካከል አይቻልም።
በአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጁ ላይ አንድ የአስተዳደር ተቋም ግዴታውን እንዲወጣ ለማስገደድ የሚቻልበት መንገድ የለም። ስለሆነም በህግ ተለይቶ የተቀመጠ መብት፤ ክፍያ፤ ጥቅም /entitlement/ ለማግኘት ያለው ብቸኛ አማራጭ የፍትሐብሔር መፍትሔዎችን መጠቀም ይሆናል። ግዴታን ከመፈጸም ጋር የተያያዙ አቤቱታዎች ምን እንደሚመስሉ ለመረዳት በሰ/መ/ቁ. 153527 የነበረውን ክርክር እንመልከት።l
አመልካች ከቀረጥ ነጻ የገቡ ማሽነሪዎች አለአግባብ ለሶስተኛ ወገን መተላለፋቸውን ጥቆማ የሰጠ መሆኑን በመግለጽ የሕገወጥ ዕቃዎች መረጃ አሠጣጥ፤ አያያዝ እና አመዘጋገብ እና የወሮታ ክፍያዎችን ለመወሰን ተሻሽሎ በወጣው መመሪያ ቁጥር 78/2004 መሰረት ክፍያ እንዲፈጸምለት ያቀረበው ክስ በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ስለተደረገበት ውሳኔዎቹ እንዲታረሙ የሰበር ችሎቱን ጠይቋል። ተጠሪም በሰጠው መልስ ንብረቶቹ የተላለፉለት ድርጅት ከባንክ ጋር ለፈጸመው የብድር ውል ማሽነሪዎቹን በዋስትና ያስያዘ መሆኑን፤ ተበዳሪው ድርጅት ከባንኩ የተበደረውን ገንዘብ መክፈል ስላቃተው ባንኩ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን ንብረቶቹን በጨረታ ለቅን ልቦና ለ3ኛ ወገን ያስተላለፋቸው በመሆኑ ንብረቶቹ ላይ ቀረጥ እና ታክስ ሳይሰበሰብ ክፍያ ሊፈጽም እንደማይገደድ ተከራክሯል። ምንም እንኳን ችሎቱ የአመልካችን አቤቱታ ባይቀበለውም እንዲህ ዓይነት ክርክሮችን ለመፍታት የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጁ የዘረጋው ስርዓት አለመኖሩ ግን ልብ ሊባል ይገባል።
በአጠቃላይ የአስተዳደር ተቋሙ በግዴታው መሰረት እንዲፈጽም የሚገደድበት፤ ህገ-ወጥ በሆነ ውሳኔ የአቤት ባዩን የንብረት መብት በመጋፋት የወሰደውን ንብረት የሚመልስበት፤ ተቋሙ ህገ-ወጥ ተግባር ከመፈጸም እንዲታቀብ የዕግድ ትዕዛዝ የሚሰጠበት እና መሰል የመፍትሔ ዓይነቶች በአዋጁ አልተካተቱም።
Search This Blog
Nov 17, 2020
የመንግሥት የህግ ተጠያቂነትና የመፍትሔ ዓይነቶች።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Popular Posts
-
የመግለጫ (ማስረገጫ) ትዕዛዝ የመግለጫ ትዕዛዝ (declaration, or declaratory judgment) በሁለት ወገኖች መካከል ያለውን የህግ አቋም በተመለከተ ፍ/ቤቱ መግለጫ የሚሰጥበት የትዕዛዝ ወይም የውሳኔ ዓይነ...
-
የህግ ፍልስፍና ታሪክ (የምዕራባውያን የሥነ-ሕግ እና ሞራል ፍልስፍናዎች አጭር ዳሰሳ) ክብር አቶ ---__________ አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ ማውጫ ጥንታዊ የግሪክ ፈላስፎች እና የሕግና ፍትሕ ፅንሰ ሃሳብ የህግ...
-
የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኢትዮጵያ ያለው የእንባ ጠባቂ ተቋም ህገ መንግስታዊ እውቅና አግኝቷል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በግልጽ እንደሚደነግገው የተወካዮች ም/ቤት የእንባ ጠባቂ ተቋምንና የሰብ...
-
Procedure in Cases of Petty Offences Art.167-Summoning of accused . (1) Where a petty offence has been committed, the public or private pr...
-
የስልጣን ባህርይ እና መገለጫው በአስተዳደር ህግ ውስጥ ስልጣን (power) የሚለው ጽንስ ሀሳብ ከአንድ አስተዳደራዊ ድርጊት በስተጀርባ ህጋዊ ብቃት መኖሩን ያመለክታል፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች ወይም ...
-
Procedure in Case of Default Art 160-Principle. (1) The provisions of this Chapter shall apply where the accused fails to appea...
-
The genocidal campaign against the civil society of the people of Tigray has continued with the war and the plundering of the Tigr...
-
ስልጣንና ተግባር የአስተዳደር ጉባዔዎች የዳኝነት የስልጣን ክልል (Judicial Jurisdiction) ጠባብና በህግ ተለይተው በተጠቀመጡ ውሱን ጉዳዮች ላይ ብቻ የተገደበ ነ...
-
የኢ-አድሎአዊነት መርህ ከአድልኦ የፀዳ ፍርድ (The rule against bias) የሚለው መርህ በኮመን ሎው አገራት በስፋት የዳበረ መሰረተ ሀሳብ ሲሆን በአጭሩ ሲገለጽ አንድ ሰው በራሱ ጉዳይ ራሱ ከሳ...
DOCUMENTS
Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd
No comments:
Post a Comment