Search This Blog

Dec 23, 2020

አተርፍባይ አጉዳይ


አተርፍ ባይ አጉዳይ





የሚቀጥለው ትረካ አንዳንድ ከሳሾችና ተከሳሾች ነገሩ እውነት ነው ሲሉ ቢደመጥም እውነተኛነቱ በገለልተኛ ጠበቃ አልተረጋገጠም፡፡ አሜሪካ ውስጥ አንድ ጠበቃ በዓለም ገበያ ላይ ብዙም የማይገኝ ውድ ሲጋራ ከገዛ በኋላ ለንብረቱ በጣም በመሳሳት የእሳት አደጋ ኢንሹራንስ ይገባለታል፡፡ የኢንሹራንስ ፖሊሲ በገዛ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያ ዙር አረቦን (ፕሪሚየም) እንኳን ሳይከፍል ኢንሹራንስ የተገባላቸውን ሃያ አራቱንም ሲጋራዎች ሁሉ በየቀኑ እያጨሰ ጨረሳቸው፡፡





የመጨረሻዋን ሲጋራ እንደማገ በቀጥታ ወደ መድን ድርጅቱ በማምራት በፖሊሲው መሠረት ካሳ እንዲከፈለው ጠየቀ፡፡ ጠበቃው ለድርጅቱ በፃፈው የክፍያ አቤቱታ ላይ ሲጋራዎቹ ‘ተከታታይነት ባላቸው ትናንሽ እሳቶች’ እንደወደሙ በመግለጽ ክፍያ ቢጠይቅም የመድን ድርጅቱ ግን ጠበቃው መድን የተገባለትን ሲጋራ ራሱ በማጨስ መደበኛ ለሆነው አገልግሎት ያዋለው በመሆኑ ተጠያቂ አይደለሁም በማለት ለመክፈል ፍቃደኛ ሳይሆን ይቀራል፡፡ መቼም ቀጥሎ ምን እንደሚከተል ግልጽ ነው፡፡ ጠበቃው መድን ድርጅቱን ፍርድ ቤት ገተረው፡፡ ገትሮትም አልቀረ ረታው፡፡ ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ መጀመሪያ የመድን ድርጅቱ ያቀረበውን ክርክር በመደገፍ ክሱ “ተልካሻና የማይረባ” መሆኑን በሐተታቸው ላይ ካሰፈሩ በኋላ እንዳሉት፤





“…ይሁን እንጂ ከሳሹ ጠበቃ ከተከሳሹ የመድን ፖሊሲ ገዝቷል፡፡ ተከሳሹም ሲጋራዎቹ መድን ሊገባላቸው እንደሚቻል በማረጋገጥ በእሳት ከወደሙ ክፍያ ሊፈጽም ዋስትና ሰጥቷል፡፡ በኢንሹራንስ ፖሊሲው ላይ ተቀባይነት የሌለው እሳት ወይም ሽፋን የማይሰጠው የእሳት አደጋ የትኛው እንደሆነ በግልፅ አልሰፈረም፡፡ ስለሆነም በውላቸው መሠረት ተከሳሽ ክፍያ ሊፈጽም ይገደዳል፡፡”





በነገሩ የበሸቀው ተከሳሽ ድርጅት እንደገና ይግባኝ ጠይቆ ለተጨማሪ ክርክርና ወጪ ከመዳረግ ይልቅ ውሳኔውን እንዳለ መቀበል ስለመረጠ 15,000 ዶላር ለጠበቃው ከፍሏል፡፡ ታሪኩ ግን በዚህ አያበቃም፡፡ ጠበቃው ልክ ገንዘቡን ሲቀበል ወዲያውኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የኢንሹራንስ ክፍያ ለማግኘት ሲል ኢንሹራንስ የተገባለትን ዕቃ ራሱ በማውደሙ በማጭበርበር የኢንሹንስ ክፍያ በመቀበል ለፈጸመው ወንጀል በመድን ድርጅቱ ክስ ቀርቦበት ነው፡፡ በመቀጠል ጠበቃው ላጨሳቸው 24 ሲጋራዎች ለእያንዳንዱ 24 የወንጀል ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ24 ወራት እስራት እና የ24,000 ዶላር የገንዘብ መቀጮ ቅጣት ተወስኖበታል፡፡




No comments:

Post a Comment

Popular Posts

DOCUMENTS

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd

Files

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ 2/ 2006 PDF-Revised Federal Supereme Court s No 2/2006 by ሕግ እና ፍትህ on Scribd