Search This Blog

Nov 19, 2020

የኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ


የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም





በኢትዮጵያ ያለው የእንባ ጠባቂ ተቋም ህገ መንግስታዊ እውቅና አግኝቷል፡፡

 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በግልጽ እንደሚደነግገው የተወካዮች ም/ቤት የእንባ ጠባቂ ተቋምንና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን በህግ የማቋቋም ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

በዚሁ መሰረት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ገ መንግስት ከታወጀ ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁ. 211/1992፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ በአዋጅ ቁ. 210/1992 በተወካዮች ም/ቤት ተቋቁመዋል፡፡

ዓላማ ስልጣንና ተግባር





የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ተልእኮ ስልጣንን ከፍትህ ጋር ማስታረቅ እንደመሆኑ የመንግስት ስልጣንን የመቆጣጠር ዓላማና ግብም የተልእኮው ነፀብራቅ ሊሆን ይገባል፡፡

የእንባ ጠባቂ ተቋምም ሆነ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚቋቋሙበት ዓይነተኛ ዓላማ ውጤታማ አስተዳደር እና ፍትህ ሚዛናቸውን ጠብቀው ጐን ለጐን እንዲሄዱ በማስቻል የህግ የበላይነት፣

የአስተዳደር ፍትህ እና መልካምና ውጤታማ አስተዳደር እንዲሰፍን ከማድረግ የዘለለ መሆን የለበትም፡፡

ከዚህ አንፃር የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በማቋቋሚያ አዋጁ መግቢያ እና አላማውን በሚያስቀምጠው ድንጋጌ ላይ ውጤታማ አስተዳደርን ከዜጐች መብትና ነፃነት ጋር የማጣጣም እና የማስታረቅ ተልእኮ ተሰጥቶታል፡፡





የአዋጁ መግቢያ እያደገና እየሰፋ የመጣው የመንግስት ስልጣንና ተግባር በዜጐች መብትና ጥቅም ላይ የሚያሳድረውን እንድምታ በመጠቆም የመንግስት አስፈፃሚ አካላትና ባለስልጣናት ድርጊትና እርምጃዎች ከዜጋው መብትና ጥቅም አንጻር ፍትሀዊነታቸው መረጋገጥ እንዳለበት ብሎም የአስተዳደር በደል ከተፈጸመ ፈጣን ፍትህ ማግኘት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡

ስለሆነም የተቋሙ መቋቋም መነሻ ምክንያት የመንግስት ስልጣን መለጠጥና የዜጐች ፍትህ መሻት የፈጠረው ቅራኔ እንደሆነ እናያለን፡፡ በሌላ አገላለጽ የተቋሙ መድረሻ ግብ ይህ ቅራኔ የሚፈታበትን ቀልጣፋ አሰራር በተግባር ማዋል ነው፡፡





ይኸው ሀሳብ የተቋሙ ዓላማ በተገለጸበት የአዋጁ ድንጋጌ ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተቋቋመበት ዋና ዓላማ፤





በህግ የተደነገጉ የዜጐች መብቶች እና ጥቅሞች

በአስፈፃሚው አካል መከበራቸውን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍና ግልጽነት ያለው የመንግስት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡





በሌላ በኩል በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በማነጣጠር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዓላማ ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥን ጨምሮ ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ መጠበቅ፣ መብቶቹ ሳይሸራረፉ ሥራ ላይ እንዲውሉ እና ተጥሰው ሲገኙ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሆነ በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 5 ላይ ተመልክቷል፡፡ 

ሁለቱም ተቋማት በየራሳቸው የስልጣን ክልል ስር በሚወድቁ ጉዳዮች ዓላማቸውን ለማሳካት የሚረዱ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡

የእንባ ጠባቂ ተቋም ዋነኛ ተግባር አስፈፃሚ አካላት በዜጐች ላይ የሚያደርሱትን የአስተዳደር በደል አስመልክቶ በደል ከደረሰበት ወገን በሚቀርብለት አቤቱታ መነሻነት አሊያም በራሱ ተነሳሽነት የአስተዳደር በደል ስለመፈጸሙ ማጣራትና ምርመራ በማድርግ ተገቢውን መፍትሔ መሻት ሲሆን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተመሳሳይ መልኩ የሰብአዊ መብት መጣስ ሲፈጸም ተመሳሳይ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ እነዚህ ተቋማት ከአጣሪነት እና መርማሪነት ሚናቸው በተጨማሪ ጠቅለል ባለ መልኩ በስራ አስፈፃሚው ላይ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ፤ በነባር ህጐች ላይ የማሻሻያ ሀሳብ ያቀርባሉ፣ ህብረተሰቡን ያስተምራሉ እንዲሁም እና የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡








በስልጣኑ ስር የሚወድቁ ጉዳዮች





የእንባ ጠባቂ ተቋም እና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በየፊናቸው በተሰጣቸው ስልጣናት ስር የሚመረምሯቸው አካላትና ጉዳዮች የሁለቱም የማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 7 ላይ ተዘርዘረዋል።

አንቀጽ 7 ስለ ስልጣን ገደብ የሚያወራ ቢሆንም የገደቦቹ አይነትና ይዘት በጥልቀት ሲታይ የሁለቱም አካላት የስልጣን አድማስ ከሚጠበቀው በላይ ሰፍቷል፡፡ በገደቦች ያልታሰረ እንባ ጠባቂ ከዜጋው መብትና ነፃነት አንጻር ተቀባይነቱ ቢያዘነብልም ውስብስብ ከሆነው የአስተዳደር ስራ ባህርይ አንጻር ከፊል ጉዳዮችን ለራሱ ለአስተዳደሩ መተው ተመራጭም ተገቢም የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል፡፡





የእንባ ጠባቂ ተቋም በሚከተሉት ጉዳዮች ወይም ውሳኔዎች ላይ የምርመራ ስልጣን የለውም፡፡a





በህዝብ ምርጫ የተቋቋሙ ምክር ቤቶች በሕግ አውጭነታቸው የሚሰጧቸው ውሳኔዎች





በማንኛውም ፍርድ ቤት በየትኛውም ደረጃ በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዮች





በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በመታየት ላይ ያለ ጉዳዮች





በፀጥታ ኃይሎችና በመከላከያ ሰራዊት ክፍሎች የሚሰጡ የፀጥታ ወይም የሀገር መከላከል ጉዳዮችን በሚመለከት የሚሰጡ ውሳኔዎች





የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ በተወካዮች ም/ቤት፣ 

በፌዴሬሽን ም/ቤት፣ በክልል ም/ቤቶች እንዲሁም በማንኛውም ፍ/ቤት በየትኛውም ደረጃ በመታየት ላይ ካሉ ጉዳዮች በስተቀር የሰብዓዊ መብት መጣስ አስመልክቶ በማንኛውም ሰው እና የመንግስት ተቋማትት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የመመርመር ስልጣን አለው፡፡





የገደቦቹን ይዘት ለማየት እንደሚቻለው ከሁለቱም ተቋማት የምርመራ ስልጣን ውጭ የሆነ አንድም የመንግስት አካል የለም፡፡ የውሳኔው ይዘት እንጂ ውሳኔ ሰጭው ከተቋሙ ስልጣን ውጭ አልተደረገም፡፡

 የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከመንግስታዊ አካላት አልፎ በማንኛውም ሰው የሚፈፀም የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ ይመረምራል፡፡ 

በአዋጁ የትርጓሜ ክፍል እንደተመለከተው ‘ሰው’ የሚለው ቃል ማንኛውንም የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠውን አካል ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
ኮሚሽኑ በግለሰቦች ላይ የተሰጠው ስልጣን ከተግባራዊ አፈጻጸሙ አንጻር ከአስፈላጊነቱ ይልቅ አደናጋሪነቱ ይጐላል፡፡ ኮሚሽኑ ሆነ ተቋሙ መፍትሔ በመስጠት ረገድ ስልጣናቸው አንድን ጉዳይ መርምሮ አሳሪና ውጤት ያለው ውሳኔ ማስተላፍ ሳይሆን አቤቱታ ለቀረበበት ወገን የውሳኔውን ሀሳብ ማሳወቅ ወይም ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ማቅረብ ነው፡፡





የሰብዓዊ መብት መጣስ ሲፈፀም ኮሚሽኑ የምርመራውን ውጤት ከነአስተያየቱ ለሚመለከተው አካል የበላይ ኃላፊ እና ለአቤቱታ አቅራቢ በጽሁፍ ያሳውቃል፡፡

በተግባር ሲታይ አንድ ግለሰብ ወይም የግል ድርጅት የፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ ለራሱ የመፍትሔ ሀሳብ መልሶ መስጠት የሚያመጣው ፋይዳ አይኖርም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ አቤቱታ ለቀረበበት የመንግስት አካል የበላይ ኃላፊ የውሳኔ ሀሳብ ሲቀርብ የውሳኔ ሀሳቡን በፈቃደኝነት ተፈፃሚ የማድረግ አጋጣሚ በተለያዩ ምክንያቶች የሰፋ ነው፡፡ ለተቋማቱ የሚሰጠው ከፍተኛ ከበሬታና ተቀባይነት፣ በህዝብ አስተዳደር ውስጥ የህዝብ አቤቱታ አስፈላጊነት እና ከውሳኔ ሀሳቡ ጋር አለመስማማት ከህግ አውጭው ጋር የሚፈጥረው ፍጥጫ የውሳኔ ሀሳቡ በመንግስት አካላት አስገዳጅነት ሳይኖር ተቀባይነት ከሚያገኝባቸው ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡





ከዚህ በተቃራኒ ግለሰቦችንና የግል ድርጅቶችን አስመልክቶ የኮሚሽኑን የውሳኔ ሀሳብ ለመቀበል ሊጠቀስ የሚችል አሳማኝ ምክንያት የለም፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ ያለው ስልጣን ከአተገባበር ሆነ ከውጤትም አንጻር አያስኬድም፡፡





No comments:

Post a Comment

Popular Posts

DOCUMENTS

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd

Files

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ 2/ 2006 PDF-Revised Federal Supereme Court s No 2/2006 by ሕግ እና ፍትህ on Scribd