በክልሎች ላይ ያለው ስልጣን ህገ-መንግስታዊነ
በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅ
ቁ. 211/1992 አንቀጽ 4 መሰረት በፌደራል መንግስት የተቋቋመው እንባ ጠባቂ በክልል መንግስት ስራ አስፈፃሚ አካላትና ባለስልጣናት የሚፈፀሙ የአስተዳደር ጥፋቶችን ጭምር የመመርመር ስልጣን ደለው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 210/1992 አንቀጽ 4 አዋጁ በማንኛውም ክልል ውስጥ በሚፈፀሙ የሰብዓዊ መጣስ ጉዳዮችም ላይ ስልጣን እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡ የሁለቱም አዋጆች አንቀጽ 4 አፈላጊነት ሆነ ህገ-መንግስታዊነቱ በሚገባ የተመከረበትና የታሰበበት ካለመሆኑም በላይ በተግባር የክልሎችን የዲሞክራሲያዊ ተቋም ግንባታ ሂደት ከማዳከም በቀር ተጨባጭ ፍሬ አላስገኘም፡፡
እንባ ጠባቂ በክልል መንግስታት ላይ ስልጣን ሊኖረው ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለው ጥያቄ ተቋሙን ሆነ ኮሚሽኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በዝርዝር ህግ ለማቋቋም ከታሰበበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ገሃድ የወጣ ክርክርና ውይይት አልጋበዘም፡፡ በክልል መንግስታት ዘንድም ውስጥ ውስጡን የጉርምርምታ ምንጭ ቢሆንም ጉዳዩ በጭብጥነት ተመዞ የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን አልበቃም፡፡ ተቋሙንና ኮሚሽኑን ለማቋቋም በነበረው የህግ ማውጣት ሂደት እንደዚሁ ሁለቱም አካላት በክልሎች ላይ የሚኖራቸው ስልጣን ህገ-መንግስታዊነት በተመለከተ ህገ-መንግስቱን ተንተርሶ የተሰጠ ትንተና ሆነ ምክንያት አልነበረም፡፡
ከላይ እንደተጠቆመው የሁለቱም ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጆች በክልል መንግስት ስራ አስፈፃሚ አካላትና ባለስልጣናት የሚፈፀሙ የአስተዳደር ጥፋቶችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተቋሙና በኮሚሽኑ የስልጣን ክልል ስር እንደሚወድቁ ደንግገዋል፡፡ በዚህ ረገድ የተፈጠረው የተሳሳተ ግንዛቤ ምንጩ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 55 ንኡስ አንቀፅ 14 እና 15 ንባብ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ሁለቱም አንቀጾች የተወካዮች ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው አንቀፅ 55 ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ምክር ቤቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንንና የእንባ ጠባቂ ተቋምን እንደሚያቋቁም ብሎም ስልጣንና ተግባራቸውን በህግ እንደሚወሰን በማያሻማ አነጋገር ይደነገጋሉ፡፡
የአንቀጽ 55/14/ እና /15/ ድንጋጌዎችን ላይ ላዩን ለሚያነብ ሰው ሁለቱም ተቋማት በፌደራል መንግስት ስልጣን ስር ብቻ እንደሚካተቱ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ ሁለቱ ማቋቋሚያ አዋጆች በሚረቀቁበት ወቅት ተቋማቱን አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበ አንድ ሪፖርት ላይ ተቋማቱ በክልሎች ላይ ስልጣን ሊኖራቸው እንደሚገባ ለማሳመን የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 55 /14/እና /15/ ተጠቅሰዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማጥራት ያስፈልጋል፡፡
የእንባ ጠባቂ በየአገራቱ ዝብርቅርቅ መልክና ቅርጽ አለው፡፡ ሆኖም ከሚቋቋምበት መንገድ አንጻር ሲታይ በአንድ መንግስታዊ ተቋም ስር (ለምሳሌ የዩኒቨርስቲa እና የማረሚያ ቤት እንባጠባቂb)፣ በግሉ ዘርፍ (ለምሳሌ የባንኮች፣ የኃይል አቅርቦት፣ የኢንሹራንስ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን እንባጠባቂዎችc) እንዲሁም በጣም በሚታወቅበት መልኩ በአገር አቀፍ፣ በክልሎች፣ ግዛቶችና መስተዳድሮች ደረጃ ይቋቋማል፡፡
በግሉ ዘርፍ እና በተቋም ደረጃ የሚገኘውን ትተን በአገር ዓቀፍ ደረጃ የሚቋቋመውን እንባ ጠባቂ በጥቅል ስንመለከት የሚቋቋምበት መንገድ ሁለት ነው፡፡ ይኸውም አንደኛ አገሪቱ ባጸደቀችው ህገ መንግስት በግልጽ ዕውቅና የተሰጠው ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛ በህገ መንግስት ላይ በግልጽ ሳይካተት ፓርላማ በሚያወጣው ልዩ ህግ ሊቋቋም ይችላል፡፡ የተቋሙ የህልውና መሰረት ህገ መንግስት መሆኑ/አለመሆኑ አንድ መሰረታዊ ቁምነ ነገር ያስጨብጠናል፡፡ ይኸውም ህገ መንግስታዊ ዕውቅና ያለው እንባ ጠባቂ ተቋም የመቋቋሙ ዕጣ ፈንታ ለህግ አውጪው የተተወ አይደለም፡፡ ህግ አውጪው መዋቅርና አደረጃጀቱን በልዩ ህግ በመወሰን ተቋሙን የመመስረት ህጋዊ ግዴታ አለበት፡፡ በተቃራኒው የአንድ አገር ህገ መንግስት ስለተቋሙ በግልጽ ካልደነገገ እንደ ህግ አውጪው ፈቃድ እንባ ጠባቂ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ ህልውና የሚያገኘው አስፈላጊነቱና ጠቃሚነቱ ከታመነበት ብቻ ነው፡፡
የእንባ ጠባቂ ጽንሰ ሀሳብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ዕድገት በማሳየት ከሞላ ጎደል በሁሉም የዓለማችን አገራት ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ተቋሙ የመንግስትን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ብሎም አስተዳደራዊ ፍትሕ በማስፈን ሊጫወት የሚችለው ዴሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ ሚና መሰረታዊ ጥያቄ ባይነሳበትም የተወሰኑ አገራት እጃቸውን ዘርግተው አልተቀበሉትም፡፡ ሌሎች ደግሞ ትልቅ ቦታ ከመስጠታቸው የተነሳ ህልውናው በየምርጫ ዘመን በሚቀያየር ፓርላማ ላይ ጥገኛ እንዳይሆን በማሰብ ጠንካራ ህገ መንግስታዊ መሰረት እንዲኖረው አድርገውታል፡፡ የተቀሩት ደግሞ ህገ መንግስታዊ ዕውቅና እስከ መስጠት ደረጃ ባይደርሱም በልዩ ህግ በማቋቋም ህልውና እና ዕውቅና ሰጥተውታል፡፡ ስለሆነም ሲፈለግ ይኖራል፤ ከገዜ በኋላ ካልተፈለገ ይቀራል፡፡
አልባኒያ the People’s Advocate በመባል የሚጠራውን እንባ ጠባቂ ተቋም እ.ኤ.አ በ1998 ዓ.ም. ባጸደቀችው ህገ መንግስት ላይ የማቋቋሚያውን መሰረት ከጣለች በኋላ በቀጣዩ ዓመት በይፋ ህግ እንዲቋቋም አድርጋለች፡፡d ሆኖም የኦስትሪያ እንባ ጠባቂ ቦርድ ህገ መንግስታዊ መሰረት ስላልነበረው ተቋሙን የማቋቋም ሀሳብ መጀመሪያ ተቀባይነት ሳያገኝ ከጊዜ በኋላ በህግ ሊቋቋም ችሏል፡፡ የህጉ ረቂቅ ለፓርላማ የቀረበው እ.ኤ.አ በ1972 ዓ.ም. ቢሆንም ሶስት ዓመት ሙሉ ሲንከባለል ቆይቶ ሊጽድቅ አልቻለም፡፡ ሆኖም ከዚሁ ረቀቂ ይዘትና መንፈስ በመነሳት በድጋሚ የቀረበው ረቂቅ እ.ኤ.አ በ1977 ተቀባይነት በማግኘቱ ቦርዱ በህግ ተቋቁሟል፡፡e በአሜሪካ የፌደራል እንባ ጠባቂ የሚባል ተቋም የለም፡፡ ኮንግረስ ስራ አስፈፃሚውን መቆጣጠር ለራሱ ብቻ የተተወ ህገ መንግስታዊ ሚና እንደሆነ ጠንካራ አቋም በመያዙ ይህን ታሪካዊ ስልጣኑን አሳልፎ መስጠት አልፈቀደም፡፡f የዚህ አመለካከት ተጽዕኖ ተቋሙ ከጥቂት ግዛቶችg በስተቀር በአብዛኞቹ ተቀባይነት እንዳያገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣ ሁለቱም ተቋማት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 55/14/ እና /15/ ላይ መሰረታቸው ተጥሏል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ስልጣንና ተግባራቸውን በዝርዝር ህግ ከመወሰን ውጪ አስፈላጊነታቸውን ጥያቄ የሚያነሳበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለቱም ድንጋጌዎች በግልጽ የሚናገሩት ምክር ቤቱ ተቋማቱ ህጋዊ ሰውነት አግኝተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ህገ መንግስታዊ ግዴታ እንዳለበት ነው፡፡ ይሄ ግዴታ በሌሎች ሶስት ህግ መንግስታዊ መሰረት ባላቸው ተቋማትም ላይ ተፈጻሚነት አለው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ከአንቀጽ 111-113 ድረስ የተጠቀሱት የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፣ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እና የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን እንደ እንባ ጠባቂ ሁሉ ህገ መንግስታዊ ናቸው፡፡
የድንጋጌዎቹን ይዘት ከፌደራላዊ የስልጣን ክፍፍል ጋር ማምታታት የፌደራሊዝም ስርዓት ሀሁ ግንዛቤ የማጣት ያክል ነው፡፡ የአንቀጽ 55 ርዕስ ‘ስልጣንና ተግባር’ ስለሚል ብቻ ሁለቱም ተቋማት በፌደራል መንግስት የስልጣን ክልል ስር እንደሆኑ ማሰብ ትርጉም አለመስጠቱ ብቻ ሳይሆን ፌደራሊዝምን በአሀዳዊነት መነጽር የማየት ችግር ያንጸባርቃል፡፡
ለመሆኑ ‘እንባ ጠባቂ ተቋም እና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በፌደራል መንግስት ስልጣን ስር ናቸው ማለት ምን ማለት ነው?’ በፌደራል እና ክልል ስልጣን (jurisdiction)h ስር የሚወድቁ ጉዳዮች በአንቀጽ 51 እና 52 ስር ተለይተው ተዘርዝረዋል፡፡ ዝርዝሮቹ በሙሉ የሚናገሩት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ስር ስላሉ ጉዳዮች ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የክልል መንግስታት የራሳቸውን እንባ ጠባቂና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንደሚያቋቁሙ ሳይናገር በዝምታ ማለፉ ተገቢና ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም ውሳኔው ከመነሻው የክልሎቹ የራሳቸው ነው መሆን ያለበት፡፡ ሲፈልጉ በህገ መንግስታቸው ለተቋማቱ ዕውቅና መስጠት ይችላሉ፡፡ አሊያም ደግሞ በህገ መንግስታቸው ውስጥ ማካተቱን ትተው አስፈላጊ ሆኖ ባገኙት ጊዜ ህግ አውጥተው ማቋቋም (አሊያም እስከነጭራሹ አለማቋቋም) ይችላሉ፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 55 /14/ እና /15/ ድንጋጌዎች ይዘት የፌደራሉ እንባ ጠባቂ ህገ መንግስታዊ እንደሆነና የተወካዮች ምክር ቤት በዝርዝር ህግ ስልጣንና ተግባሩን በመወሰን ህጋዊ ሰውነት ኖሮት እንዲቋቋም የማድረግ ህገ መንግስታዊ ግዴታ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ሁለቱም ተቋማት በክልል መንግስታት ስራ አስፈፃሚ ላይ ስልጣን እንዳላቸው ከድንጋጌዎቹ በመነሳት የሚቀርብ ክርክር ፈር የሳተና የፌደራል ስርዓት ከሚያስነሳቸው ዘርፈ ብዙ ጭብጦች ውስጥ ሊካተት የማይችል፣ ጥልቀት ያነሰው፣ ‘ከላይ-በላይ ንባብ’ የሚመነጭ ክርክር ነው፡፡ ብዙ ባያስኬድም ከስልጣን ክፍፍል አንጻር ክርክር ከቀረበ መቅረብ ያለበት ተቋማቱ ከፌደራልና ከክልል በየትኛው ስልጣን ስር እንደሚወድቁ በመጠየቅ ሳይሆን ተቋማቱ የሚያከናውኑት ጉዳይ በማን ስልጣን ስር እንደሆነ ጥያቄ በማንሳት ነው፡፡ ስለሆነም ጥያቄው የሚከተለውን መልክ ይይዛል፡፡ ‘የክልል ስራ አስፈፃሚ አካላትንና ባለስልጣናትን ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ በክልሉ አስተዳደራዊ ፍትሕ ማስፈን፣ ለአስተዳደራዊ በደሎች መፍትሔ መስጠት፣ አስተዳደራዊ ጥፋትን የማረም ስልጣኑ የማን ነው? የራሱ የክልሉ ነው? ወይስ የፌደራል መንግስት? በክልል ጉዳይ የሚያገባው ማነው? የፌደራል ወይስ የክልሉ መንግስት?’
የጥያቄዎቹ ቀላልነት ሲታይ ምላሽ መስጠት መሰረታዊ ባልሆነ ጉዳይ መባከን ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከ500 በላይ አባላት ያቀፈ ፓርላማ ጥያቄውን በወጉ መመለስ ተስኖት ‘ፈተናውን የወደቀ’ እንደመሆኑ በቂ ማብራሪያ መስጠት ግድ ይላል፡፡
ራስን በራስ ማስተዳደር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ከሚደነግጋቸው ዐበይት መርሆዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ የፌደራል እና የክልል መንግስታት የስልጣን ክፍፍል ይህን መብት ባማከለ መልኩ ተዋቅሯል፡፡ የክልሎችን ስልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 52/2/ ሀ መሰረት ክልሎች ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ መስተዳድር ያዋቅራሉ፡፡ ማስተዳደር ማለት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስልጣንን በመጠቀም የህብረተሰቡን ጉዳይ መምራት ማለት ነው፡፡i ይህም በሁለት መልኩ በተግባር ይገለጣል፡፡ በአንድ በኩል ስልጣን የተረከበውና የማስተዳደሩን ሚና የወሰደው አካል የህብረተሰቡን ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ፕሮግራሞችንና ህጎችን በመቅረጽና ይህን የሚተገብሩ ተቋማት በመመስረትና በማጠናከር ተጨባጭ ለውጦች ማምጣት ይኖርበታል፡፡ ይህ ተግባር በባህርዩ አዎንታዊ ነው፡፡ ሆኖም ማስተዳደር በአዎንታዊ እርምጃና እንቅስቃሴ ብቻ አይገታም፡፡ ስለሆነም ሁለተኛው የማስተዳደር ገፅታ ስህተቶችንና ድክመቶችን በራስ የማረም መብትን ያካትታል፡፡
በሁለቱም ገፅታዎች ሲታይ ክልሎች የተጎናጸፉት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በራሳቸው የስልጣን ክልል የተፈጸሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ራሳቸው ባቆሙት ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ የመቅረፍና መፍትሔ ፈልጎ የመተግበር መብትና ስልጣን ያካትታል፡፡ የእያንዳንዱ ክልል ስራ አስፈፃሚና የአስተዳደር ተቋማት የክልሉ ም/ቤት ያወጣቸውን ህጎች ያስፈጽማሉ፡፡ በዚህ ሚናቸው ለህብረተሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያቀርባሉ፡፡ የንግድ እንቅስቃሴን ይቆጣጠራሉ፡፡ ቀረጥና ታክስ ይሰበስባሉ፡፡ የተሰበሰበውን ገንዘብ እንዲሁም ከፌደራል መንግስት የሚመደብላቸውን በጀት ያስተዳድራሉ፡፡ እነዚህን ተግባራት ሲያከናውኑ በየዕለቱ በክልሉ ውስጥ ከሚገኘው ነዋሪ ጋር ይገናኛሉ፡፡ ግንኙነቱ መልካም እንዲሆን አስተዳደሩ ውጤታማና ፍትሐዊ አስተዳደር ማስፈን በአንጻሩ ደግሞ ሙስናን እና የአስተዳደር በደል እንዳይንሰራፋ ጠንካራ ህጋዊና ተቋማዊ የስልጣን ቁጥጥር ማካሄድ ይኖርበታል፡፡ አስተዳደራዊ ችግሮችን መፍታት ክልሉን የሚያስተዳድረው መንግስት ሚና እንጂ የየፌደራል መንግስት ጣልቃ የሚገባበት ጉዳይ አይደለም፡፡
የእንባ ጠባቂ ተቋም ያነገበው ተልዕኮ የአስተዳደር በደሎችን መቅረፍ ነው፡፡ ሆኖም ተቋሙ በፌደራል ደረጃ ከተቋቋመ የስልጣን ወሰኑ ዜጎች በፌደራል አስፈፃሚ አካላት ለሚፈጸምባቸው አስተዳደራዊ በደል መፍትሔ ከመስጠት አያልፍም፡፡ በክልል የሚፈጸመውን አስተዳደራዊ በደል በተመለከተ የክልሉ እንባ ጠባቂ ወይም ሌላ ተቋም ይጨነቅበት፡፡ ህገ መንግስቱ ማዕከላዊ የአስተዳደር ችግር አፈታት ስልት አልዘረጋም፡፡ ሲጠቃለል ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የእንባ ጠባቂ ተቋም በክልሎች የዘረጋቸውን ረጃጅም እጆች ኢ-ህገ መንግስታዊ ያደርጋቸዋል፡፡

No comments:
Post a Comment