Search This Blog

Oct 24, 2020

የመግለጫ (ማስረገጫ) ትዕዛዝ

የመግለጫ (ማስረገጫ) ትዕዛዝ
የመግለጫ ትዕዛዝ (declaration, or declaratory judgment) በሁለት ወገኖች መካከል ያለውን የህግ አቋም በተመለከተ ፍ/ቤቱ መግለጫ የሚሰጥበት የትዕዛዝ ወይም የውሳኔ ዓይነት ነው፡፡a በይዘቱ ከህግ ትርጓሜ የሚመነጭ ግዴታ ወይም መብት ከማስረገጥ ወይም ህጋዊነትና ህገወጥነት ሁኔታ ወይም አቋም ከመደንገግ ወይም ከማስረገጥ ባለፈ አስገዳጅነት የለውም፡፡ ስለሆነም ትዕዛዙን አለማክበር በፍ/ቤት ንቀት ቅጣት አያስከትልም፡፡b
ከስልጣን በላይ ወይም ህገ ወጥ በሆነ ድርጊት ምክንያት አንድ ሰው ለወደፊት በንብረቱና በነፃነቱ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ለሚችል ውሳኔ ሊዳረግ ይችላል፡፡ ውሳኔው እንዳይሰጥ ከተፈለገ አንደኛው አማራጭ በክልከላ ወይም በዕግድ ትዕዛዝ ማስቆም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም የመፍትሄ አይነቶች የራሳቸው የሆነ ልዩ ቅድመ ሁኔታና የሥነ-ስርዓት ድንጋጌዎች አሏቸው፡፡ ቀላሉ መንገድ የመብቱን መኖርና አለመኖር፣ የድርጊቱን ከስልጣን በላይ መሆን አለመሆን ወይም ሌላ ህጋዊ አቋም በፍ/ቤቱ እንዲፀና ወይም መግለጫ እንዲሰጥበት ዳኝነት መጠየቅ ነው፡፡
በዚህ መልኩ ጥያቄ ማቅረብ ተመራጭ የሚያደርገው አመልካቹ ሌሎች የአስተዳደር ህግ መፍትሄዎችን ለማግኘት ማሟላት ያለበት ዝርዝር ቅድመ ሁኔታ እንዲያሳይ አይጠበቅበትም፡፡ ፍ/ቤትም አብዛኛውን ጊዜ ትዕዛዙን ለመስጠት አያመነታም፡፡ በተጨማሪም በመግለጫ የሚረጋገጠው የህግ ሁኔታ ለቀጣይ መፍትሄ መሰረት ይጥላል፡፡ ሌላው ጠቀሜታው ደግሞ በአመልካቹና ጥያቄ በቀረበበት አካል መካከል የከረረ ሙግት ስለማይኖር ሰላማዊ የችግር መፍቻ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡c
የመግለጫ ትዕዛዝ እስከ ቅርቡ 20ኛው ክፍ ዘመን ድረስ የአስተዳደር ተቋማትን በፍ/ቤት የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ሆኖ ብቅ አላለም፡፡d በአጣሪ ዳኝነት የመፍትሄ ማዕቀፍ ውስጥ ከተጠቃለለ ወዲህ ግን ከሌሎች የመፍትሄ አይነቶች እጅግ በጣም በፈጠነ መልኩ ተቀባይት አግኝቷል፡፡
መግለጫ ራሱን እንደ ቻለ ውሳኔ በአገራችን አልተለመደም፡፡ በመደበኛው የፍትሐብሔር ጉዳይ ተቀራራቢ ይዘት ኖሮት ተፈጻሚነት ቢያገኝም በአስተዳደራዊ ክርክር ውስጥ ግን ጥያቄው የተነሳበት ሆኖ ትዕዛዙ የተሰጠበት አጋጣሚ የለም፡፡ የወራሽነት ምስክር ወረቀት፣ የመጥፋት ውሳኔ መግለጫ እና የአባትነት ውሳኔ ፍርድ ቤት የመግለጫው ውሳኔ ከሚሰጥባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
በአስተዳደራዊ ክርክሮች በመግለጫ ብቻ ዳኝነት የሚሰጥባቸው የህግ ሁኔታዎች የሉም፡፡ መብት ለማረጋገጥ የሚቀርብ ክስ ከመነሻው የክስ ምክንያት ስለማይኖረው ውድቅ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 9 አንድ ሰራተኛ የውሉ ጊዜ በአንቀጽ 10 መሰረት ላልተወሰነ ጊዜ እንደተደረገ ቢቆጠርም በመብቱና በጥቅሙ ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ‘የሥራ ውሌ ላልተወሰነ ጊዜ እደተደረገ ይቆጠርልኝ’ የሚል ጥያቄ ሊያቀርብ ሆነ ውሳኔ ሊያገኝ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የተጠየቀው ዳኝነት የክስ ምክንያት የለውም፡፡ የመግለጫ ትዕዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ሰራተኛው በጥቅምና በመብቱ ላይ ጉዳት እስሚደርስ ድረስ ሳይጠብቅ ህጋዊ አቋሙ ማለትም የሥራ ውሉ ላልተወሰነ ጊዜ እንደተደረገ እንዲቆጠርለት ማረጋገጫ ይችል ነበር፡፡ ውሳኔው የፍ/ባለመብት ባያደርገውም ቀጣይ የመብት ጥሰቶችን በቀላሉ ለመቃወም ያስችለዋል፡፡
ትዕዛዙ በውጤቱ አስገዳጅነት የለውም፡፡ ቢሆንም የራሱ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ እንደ አንድ የዳኝነት ዓይነት ተቀባይነት ባገኘባቸው አገራት ፍርድ ቤት መብት፣ ግዴታ ወይም ህጋዊነት በማረጋገጥ የሚሰጠው ትዕዛዝ በውዴታ ይከበራል፡፡ አስተዳደራዊ በደልን ለመቅረፍ ከሙግት ይልቅ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ እንዲሉ በግለሰቡ መብትና ጥቅም ጉዳት ከመድረሱ በፊት የህግ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ማስረገጥ ከአስገዳጅ ፍርድ የበለጠ የጎላ ፋይዳ አለው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የመግለጫ ትዕዛዝ በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ የማይሰጥ ቢሆንም ባህርያቱን በሚከተለው መላምታዊ ምሳሌ ማየት እንችላለን፡፡ በባንክ ስራ አዋጅ ቁ. 592/2000 መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ መረጃዎች ከባንኮች እንዲቀርቡለት የማድረግ ስልጣን አለው፡፡ ሆኖም የየባንክ ደንበኞችን ስም፣ የትዳር ሁኔታ ሆነ ሌላ ግላዊ መረጃ መጠየቅ አልተፈቀደለትም፡፡ እንበልና የብሔራዊ ባንክ ህግ ከፈቀደለት ስልጣን ውጪ እያንዳንዱ ባንክ የተበዳሪዎቹን ግላዊ ሁኔታ ከብድር መዝገብ እየለቀመ ወይም ተበዳሪዎችን በአካል እየጠየቀ በአምስት ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲልክ፣ የማይልክ ከሆነ ግን ፈቃዱ እንደሚሰረዝ በማሳሰብ ለባንኮች ጥያቄ አቀረበ፡፡ ይህንን በመቃወም ባንኮች ቅሬታ በማሰማታቸው ከዚያም አልፎ የብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ህገ ወጥ ተብሎ የመግለጫ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ለፍርድ ቤት አመልክተው ቢሳካላቸው ትዕዛዙ በራሱ አስገዳጅ ውጤት አያስከትልም፡፡ ባንኮቹ በታዘዙት መሰረት ሪፖርት ባይልኩ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እንዳይሰርዝ አያግደውም፡፡ ሆኖም የሪፖርት ጥያቄው ህጋዊነት ከወዲሁ ስለሚታወቅ የመሰረዝ እርምጃውን በፍርድ ለማሻር ቀላል ያደርገዋል፡፡ ምናልባትም ባንኩ የህዝብ ጥቅም ለማስከበር ከቆመ ከሚደርስበት ህዝባዊ ወቀሳ ለመዳን ፈቃድ ከመሰረዝ የሚታቀብበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡


1 comment:

Popular Posts

DOCUMENTS

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd

Files

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ 2/ 2006 PDF-Revised Federal Supereme Court s No 2/2006 by ሕግ እና ፍትህ on Scribd